በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

እርማት ሲሰጠኝ ምን ላድርግ?

እርማት ሲሰጠኝ ምን ላድርግ?

 ራስህን ገምግም

 እርማት የማያስፈልገው ማንም የለም፤ እርማት በሥራችንም ሆነ በአመለካከታችን ላይ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንድናደርግ ይረዳናል። ይህን በአእምሮህ በመያዝ ከዚህ በታች ለተጠቀሱት ሁኔታዎች የምትሰጠውን ምላሽ ለማሰብ ሞክር።

  1.   አስተማሪህ የተሰጠህን ፕሮጀክት በችኮላ እንደሠራኸውና ተጨማሪ ጊዜ መድበህ ምርምር ማድረግ እንደነበረብህ ነገረህ።

     ለዚህ እርማት ምን ምላሽ ትሰጣለህ?

    1.  ሀ. አልቀበለውም። (‘አስተማሪው ስለማይወደኝ ነው።’)

    2.  ለ. እቀበለዋለሁ። (‘ምክሩን ለቀጣዩ ፕሮጀክቴ እጠቀምበታለሁ።’)

  2.   ክፍልህን ካጸዳኸው በኋላ እናትህ ክፍልህ እንደተዝረከረከ ነገረችህ።

     ለዚህ እርማት ምን ምላሽ ትሰጣለህ?

    1.  ሀ. አልቀበለውም። (‘እሷ ደግሞ በቀላሉ አትረካም።’)

    2.  ለ. እቀበለዋለሁ። (‘ልክ ነው፤ በደንብ አላጸዳሁትም ነበር።’)

  3.   ታናሽ እህትህ ትእዛዝ እንደምታበዛ ነገረችህ።

     ለዚህ እርማት ምን ምላሽ ትሰጣለህ?

    1.  ሀ. አልቀበለውም። (‘እሷ ማን ሆና ነው እንዲህ የምትለኝ!’)

    2.  ለ. እቀበለዋለሁ። (‘በደግነት ልይዛት ይገባ ነበር።’)

 አንዳንድ ልጆች ትንሽ እርማት ሲሰጣቸው ቅስማቸው ወዲያው ይሰበራል። አንተስ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ አለህ? ከሆነ ትልቅ አጋጣሚ እያመለጠህ ነው! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እርማት መቀበል ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ሕይወትህ የሚጠቅምህ አስፈላጊ ክህሎት ነው።

መስማት ስላልፈለግክ ብቻ መስማት ያለብህ ነገር እንዳያመልጥህ

 እርማት የሚያስፈልገኝ ለምንድን ነው?

  •   ፍጹም ስላልሆንክ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን” ይላል። (ያዕቆብ 3:2 የግርጌ ማስታወሻ) በመሆኑም ሁሉም ሰው እርማት ያስፈልገዋል።

     “ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን ስህተት መሥራት የሕይወታችን ክፍል እንደሆነ ለማስታወስ እሞክራለሁ። ስለዚህ እርማት ሲሰጠኝ ምክሩን ለመቀበልና ያንን ስህተት ላለመድገም ጥረት አደርጋለሁ።”—ዴቪድ

  •   ማሻሻያ ማድረግ ስለሚያስፈልግህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበበኛን ሰው አስተምረው፤ ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል” ይላል። (ምሳሌ 9:9) የሚሰጥህን እርማት ከተቀበልክ በእጅጉ ትጠቀማለህ።

     “ቀደም ሲል ለእርማት ተገቢው አመለካከት አልነበረኝም። እርማት የተሰጠኝ መሆኑ ሌሎች ለእኔ ጥሩ አመለካከት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ ይመስለኝ ነበር። አሁን ግን የሚሰጠኝን እርማት እቀበላለሁ፤ እንዲያውም ሰዎች እርማት እንዲሰጡኝ እጠይቃለሁ። ማሻሻል የምችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ።”—ሰሊና

 እርግጥ ጠይቀን እርማት ሲሰጠን ብዙም አይከብደን ይሆናል። ግለሰቡ በራሱ ተነሳስቶ እርማት ሲሰጠን ግን ምክሩን መቀበል ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ናታሊ በአንድ ወቅት አንድ ሰው ፖስት ካርድ ላይ ምክር ጽፎ ሰጥቷት ነበር፤ በዚህ ወቅት ምን እንደተሰማት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ፍርሃትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰማኝ። ይህን ሁሉ ጥረት እያደረግኩም ምክር የተሰጠኝ መሆኑ በጣም አሳዘነኝ።”

 አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

 እርማት መቀበል የምችለው እንዴት ነው?

  •   አዳምጥ።

     መጽሐፍ ቅዱስ “አዋቂ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው፤ ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰውም የተረጋጋ ነው” ይላል። (ምሳሌ 17:27) ግለሰቡ ሲናገር አታቋርጠው። እንዲሁም በችኮላ መልስ አትስጥ፤ ምክንያቱም በኋላ የሚያስቆጭህን ነገር ልትናገር ትችላለህ።

     “እርማት ሲሰጠኝ ሰበብ መደርደር ይቀናኛል። ከዚህ ይልቅ እርማቱን ተቀብዬ ለቀጣዩ ጊዜ ባሻሽል ይሻለኝ ነበር።”—ሣራ

  •   በመካሪው ላይ ሳይሆን በምክሩ ላይ አተኩር።

     ምክር የሰጠህ ሰው ባሉበት ድክመቶች ላይ ለማተኮር ትፈተን ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመስማት የፈጠንን፣ ለመናገር የዘገየንና ለቁጣ የዘገየን እንድንሆን’ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ ማድረግህ የተሻለ ነው። (ያዕቆብ 1:19) አብዛኛውን ጊዜ እርማት ያለምክንያት አይሰጥም። መስማት ስላልፈለግክ ብቻ መስማት ያለብህ ነገር እንዳያመልጥህ።

     “ወላጆቼ እርማት ሲሰጡኝ በብስጭት ‘አውቃለሁ፣ እሱ መቼ ጠፋኝ’ እል ነበር። ሆኖም በጥሞና ሳዳምጣቸውና ምክሩን በሥራ ላይ ሳውል የተሻለ ውጤት አገኛለሁ።”—ኤድዋርድ

  •   ለራስህ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ።

     እርማት ተሰጠህ ማለት ምንም የሚሳካልህ ነገር የለም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እርማት የተሰጠህ እንደ ማንኛውም ሰው ድክመት ስላለብህ ነው። እርማት የሰጠህ ሰውም እንኳ አልፎ አልፎ ምክር እንደሚያስፈልገው ጥያቄ የለውም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግ . . . ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም” ይላል።—መክብብ 7:20

     “በአንድ ወቅት ጓደኛዬ፣ ይመለከተኛል ብዬ ያላሰብኩትን እርማት ሰጥታኝ ነበር። ስለ ሐቀኝነቷ አመሰገንኳት፤ ግን ስሜቴ ተጎድቶ ነበር። በኋላ ግን እርማቱ የተወሰነ እውነታነት እንዳለው ተገነዘብኩ። እሷ ያንን ምክር ባትሰጠኝ ኖሮ አላስተውለውም ነበር፤ አሁን ግን ማሻሻል ያለብኝን ነገር ማስተዋል ችያለሁ።”—ሶፊያ

  •   ማሻሻያ ለማድረግ ግብ አውጣ።

     መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ . . . እርማትን ይቀበላል” ይላል። (ምሳሌ 15:5) የተሰጠህን እርማት ከተቀበልክ በስሜትህ ላይ ከማተኮር ይልቅ ማሻሻያ በማድረግ ላይ ማተኮር ትችላለህ። ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ አውጣ፤ ከዚያም በቀጣዮቹ ወራት ያደረግከውን ማሻሻያ ገምግም።

     “እርማት መቀበል ከሐቀኝነት ጋር ግንኙነት አለው፤ ምክንያቱም ስህተትህን አምነህ ለመቀበል፣ ይቅርታ ለመጠየቅና ማሻሻያ ለማድረግ ለራስህ ሐቀኛ መሆን ይጠይቃል።”—ኤማ

 ዋናው ነጥብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል” ይላል። (ምሳሌ 27:17) እርማት አሁንም ሆነ ትልቅ ሰው ስትሆን ሊስልህ የሚችል ግሩም መሣሪያ ነው።