በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር መሥራት ጠቃሚ ነው?

በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር መሥራት ጠቃሚ ነው?

 በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር መሥራት ትችላለህ?

 በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር መሥራት እንደምትችል ይሰማሃል? ብዙዎች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከልጅነታቸው አንስቶ ሲጠቀሙ ያደጉ ሰዎች አዋቂ ከሆኑ በኋላ መጠቀም ከጀመሩ ሰዎች ይልቅ በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር የመሥራት ችሎታ እንዳላቸው ይሰማቸዋል። ግን ይህ ሐሳብ እውነት ነው?

 እውነት ወይም ሐሰት

  •   በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር መሥራት ሥራህን ቶሎ ለመጨረስ ይረዳሃል።

  •   በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር የመሥራት ችሎታ በልምድ ይዳብራል።

  •   ወጣቶች ከትላልቅ ሰዎች ይልቅ በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር የመሥራት ችሎታ አላቸው።

 ከላይ ከተጠቀሱት ሐሳቦች መካከል ለአንዱም ቢሆን “እውነት” የሚል መልስ ከሰጠህ በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ስለ መሥራት ያለህ አመለካከት የተሳሳተ ነው ማለት ነው።

 በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር መሥራት ጉዳት አለው

 በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር መሥራት እንደምትችል ይሰማሃል? አንዳንድ ነገሮችን ትኩረትህ ሳይከፋፈል በአንድ ጊዜ ማከናወን ትችል ይሆናል። ለምሳሌ ሙዚቃ እያዳመጥክ ቤት ማጽዳት አይከብድህ ይሆናል።

 ሆኖም ትኩረት የሚጠይቁ ሁለት ነገሮችን በአንድ ጊዜ ለማከናወን ከሞከርክ ሁለቱንም ማበላሸትህ አይቀርም። በመሆኑም ካትሪን የተባለች አንዲት ወጣት እንደተናገረችው በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ለመሥራት መሞከር ማለት “በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ማበላሸት” ማለት ነው።

 “ከአንድ ልጅ ጋር እየተነጋገርኩ ሳለ የጽሑፍ መልእክት ደረሰኝ። ለጽሑፍ መልእክቱ መልስ እየሰጠሁ ከልጁ ጋር መነጋገሬን ለመቀጠል ሞከርኩ። በዚህም ምክንያት ልጁ የተናገረውን አብዛኛውን ነገር አልሰማሁትም፤ የላክሁት የጽሑፍ መልእክትም በተሳሳቱ ፊደላት የተሞላ ነበር።”—ካሌብ

 የቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆኑት ሼሪ ተርክል እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ብዙ ነገር ለማከናወን በሞከርን መጠን ለእያንዳንዱ ነገር የምንሰጠው ትኩረት እየቀነሰ ይመጣል። በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ለማከናወን ስንሞክር አንጎላችን ስለሚነቃቃ ሥራችንን በተሻለ መንገድ እንዳከናወንን ይሰማናል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሥራውን በአግባቡ እየሠራነው አይደለም።” a

 “አንዳንድ ጊዜ ከአንድ ሰው ጋር የጽሑፍ መልእክት እየተላላክሁ ከሌላ ሰው ጋር ማውራት ምንም እንደማይቸግረኝ ይሰማኛል፤ ከዚያ ግን በጽሑፍ ልልክ ያሰብኩትን ነገር ጮክ ብዬ እንደተናገርኩ፣ ልናገር ያሰብኩትን ነገር ደግሞ እንደጻፍኩ አስተውላለሁ።”—ታማራ

 በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ለመሥራት የሚሞክሩ ሰዎች ሳያስፈልግ ሕይወታቸውን ያወሳስባሉ። ለምሳሌ የቤት ሥራቸውን ለመጨረስ ረጅም ጊዜ ይፈጅባቸው ይሆናል። ወይም ደግሞ እንደጨረሱት ያሰቡትን ሥራ በድጋሚ መሥራት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ያም ሆነ ይህ በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ለመሥራት የሚሞክሩ ሰዎች የፈለጉትን ነገር ለማድረግ የሚያስችል በቂ ጊዜ አያገኙም።

 የሥነ ልቦና ባለሙያና የተማሪዎች አማካሪ የሆኑት ቶማስ ከርስቲንግ እንደተናገሩት ‘በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር የመሥራት ልማድ ያላቸው ሰዎች አንጎላቸው ከተመሰቃቀለ መዝገብ ቤት ጋር ይመሳሰላል።’ b

 “በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ለመሥራት በሞከርክ መጠን አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን ሳታስተውል ታልፋለህ። በውጤቱም ጊዜ ማትረፍህ ቀርቶ በራስህ ላይ ሥራ ልትጨምር ትችላለህ።”—ተሪሳ

በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ለመሥራት መሞከር በአንድ ጊዜ በሁለት መንገዶች ላይ እንደመንዳት ነው

 የተሻለ ዘዴ

  •   በአንድ ጊዜ አንድ ነገር ላይ ብቻ ለማተኮር ጥረት አድርግ። በተለይ በአንድ ጊዜ የተለያዩ ነገሮችን የማከናወን ልማድ ካለህ እንዲህ ማድረግ ከባድ ሊሆንብህ ይችላል፤ ለምሳሌ እያጠናህ የጽሑፍ መልእክት የመላላክ ልማድ ይኖርህ ይሆናል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” የሚል ምክር ይሰጠናል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ሁሉም ሥራ ያለው አስፈላጊነት እኩል አይደለም። ስለዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ሥራ የቱ እንደሆነ ከወሰንክ በኋላ ያንን ሥራ እስክትጨርስ ድረስ በዚያ ላይ ብቻ አተኩር።

     “በአንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ የማይችል አእምሮ ልክ እንደ ሕፃን ልጅ ነው፤ እንደፈለገው እንዲሆን መተው የሚቀል ቢመስልም አንዳንድ ጊዜ መከልከል ያስፈልጋል።” —ማሪያ

  •   ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን አስወግድ። በምታጠናበት ጊዜ ስልክህን ለማየት ትፈተናለህ? ስልክህን ሌላ ክፍል ውስጥ አስቀምጠው። ቴሌቪዥን አጥፋ፤ እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያ አትጠቀም። መጽሐፍ ቅዱስ “ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ [ተጠቀሙበት]” በማለት ይመክረናል።—ቆላስይስ 4:5

     “በአንድ ጊዜ አንድ ነገር ላይ ብቻ ማተኮር በጣም የተሻለ እንደሆነ አስተውያለሁ። በዚህ መንገድ በፕሮግራሜ ላይ ካሉት ሥራዎች መካከል አንዱን አጠናቅቄ ወደ ቀጣዩ ስሄድ ይበልጥ እደሰታለሁ። ይህ እርካታ ይሰጠኛል።”—ኦንያ

  •   ከሰዎች ጋር ስትነጋገር ሙሉ ትኩረትህን ለሰዎቹ ስጥ። ከአንድ ሰው ጋር እየተነጋገርክ ስልክህን የምትነካካ ከሆነ ውይይቱን በደንብ ማዳመጥ የማትችል ከመሆኑም ሌላ ለግለሰቡ አክብሮት የሌለህ ሊመስል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎች እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር እኛም እንድናደርግላቸው ያሳስበናል።—ማቴዎስ 7:12

     “አንዳንድ ጊዜ እህቴ እኔ እያነጋገርኳት በስልኳ የጽሑፍ መልእክት ትላላካለች ወይም ሌላ ሥራ ትሠራለች። እንዲህ ስታደርግ በጣም ያበሳጨኛል! እውነቱን ለመናገር ግን እኔም አንዳንዴ ተመሳሳይ ነገር አደርጋለሁ።”—ዴቪድ

a ሪክሌይሚንግ ኮንቨርሴሽን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።

b ዲስኮኔክትድ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።