መክብብ 7:1-29

  • ጥሩ ስምና የሞት ቀን (1-4)

  • የጥበበኛ ሰው ወቀሳ (5-7)

  • “የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል” (8-10)

  • ጥበብ የሚያስገኘው ጥቅም (11, 12)

  • ጥሩ ቀንና መጥፎ ቀን (13-15)

  • ከልኩ አትለፍ (16-22)

  • ሰብሳቢው ያስተዋላቸው ነገሮች (23-29)

7  ጥሩ ስም* ከጥሩ ዘይት፣+ የሞትም ቀን ከልደት ቀን ይሻላል።  ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል፤+ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ሞት ነውና፤ በሕይወት ያለ ሰውም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል።  ከሳቅ ትካዜ ይሻላል፤+ የፊት ሐዘን ለልብ መልካም ነውና።+  የጥበበኞች ልብ በሐዘን ቤት ነው፤ የሞኞች ልብ ግን በደስታ* ቤት ነው።+  የሞኞችን መዝሙር ከመስማት ይልቅ የጥበበኛን ወቀሳ መስማት ይሻላል።+  የሞኝ ሳቅ ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ የእሾህ ማገዶ ነው፤+ ይህም ቢሆን ከንቱ ነው።  ግፍ ጥበበኛውን ሊያሳብደው ይችላል፤ ጉቦም ልብን ያበላሻል።+  የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል። ትዕቢተኛ ከመሆን ይልቅ ታጋሽ መሆን ይሻላል።+  የሞኞች ቁጣ በጉያቸው ውስጥ ስለሆነ*+ ለቁጣ አትቸኩል።*+ 10  “የቀድሞው ዘመን ከአሁኑ ዘመን ለምን ተሻለ?” አትበል፤ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ጥበብ አይደለምና።+ 11  ጥበብ ከውርስ ጋር መልካም ነገር ናት፤ የቀን ብርሃን ለሚያዩ ሰዎችም* ጠቃሚ ነች። 12  ገንዘብ ጥበቃ እንደሚያስገኝ+ ሁሉ ጥበብም ጥበቃ ታስገኛለችና፤+ የእውቀት ብልጫ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት ጠብቃ ማቆየት መቻሏ ነው።+ 13  እውነተኛው አምላክ ያከናወነውን ሥራ ልብ በል፤ እሱ ያጣመመውን ማን ሊያቃና ይችላል?+ 14  በጥሩ ቀን አንተም ይህን ጥሩነት መልሰህ አንጸባርቅ፤+ በአስቸጋሪ* ቀን ግን ይሄኛውንም ሆነ ያኛውን ያደረገው አምላክ እንደሆነ አስተውል፤+ ይህም የሆነው ሰዎች ወደፊት የሚደርስባቸውን ማንኛውንም ነገር በተመለከተ እርግጠኞች መሆን* እንዳይችሉ ነው።+ 15  ከንቱ በሆነው የሕይወት ዘመኔ+ ሁሉንም ነገር አይቻለሁ፤ ጻድቁ ሰው በጽድቁ ሲጠፋ፣+ ክፉው ሰው ደግሞ ክፉ ቢሆንም ረጅም ዘመን ሲኖር ተመልክቻለሁ።+ 16  ከልክ በላይ ጻድቅ አትሁን፤+ እጅግም ጥበበኛ መስለህ ለመታየት አትሞክር።+ በራስህ ላይ ለምን ጥፋት ታመጣለህ?+ 17  እጅግ ክፉ አትሁን፤ ሞኝም አትሁን።+ ያለጊዜህ ለምን በሞት ትቀጫለህ?+ 18  አንደኛውን ማስጠንቀቂያ ሳትተው ሌላኛውንም አጥብቀህ መያዝህ የተሻለ ነው፤+ አምላክን የሚፈራ ሰው ሁለቱንም ይሰማልና። 19  ጥበብ ጥበበኛውን ሰው፣ በአንድ ከተማ ካሉ አሥር ብርቱ ሰዎች ይበልጥ ኃያል ታደርገዋለች።+ 20  ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኃጢአት የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለምና።+ 21  በተጨማሪም ሰዎች የሚናገሩትን ነገር ሁሉ ትኩረት ሰጥተህ አትከታተል፤+ አለዚያ አገልጋይህ ስለ አንተ መጥፎ ነገር ሲናገር* ልትሰማ ትችላለህ፤ 22  አንተ ራስህ ስለ ሌሎች ብዙ ጊዜ መጥፎ ነገር እንደተናገርክ ልብህ በሚገባ ያውቃልና።+ 23  ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንኩ፤ እኔም “ጥበበኛ እሆናለሁ” አልኩ። ይህ ግን ከአቅሜ በላይ ነበር። 24  የተከናወነው ነገር ሁሉ ሊደረስበት የማይቻል ከመሆኑም ሌላ እጅግ ጥልቅ ነው። ማንስ ሊረዳው ይችላል?+ 25  እኔም ጥበብንና የነገሮችን መንስኤ ለመረዳት፣ ለመመርመርና ለማጥናት እንዲሁም የሞኝነትን ክፋትና የእብደትን ቂልነት ለመገንዘብ ልቤን አዘነበልኩ።+ 26  ከዚያም የሚከተለውን ነገር ተገነዘብኩ፦ እንደ አዳኝ ወጥመድ የሆነች ደግሞም እንደ መረብ ያለ ልብ፣ እንደ እስር ቤት ሰንሰለትም ያሉ እጆች ያሏት ሴት ከሞት እጅግ የመረረች ናት። እውነተኛውን አምላክ የሚያስደስት ሰው ከእሷ ያመልጣል፤+ ኃጢአተኛ ግን በእሷ ይያዛል።+ 27  ሰብሳቢው+ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ መርምሬ ያገኘሁት ነገር ይህ ነው። አንድ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እያንዳንዱን ነገር በሚገባ አጠናሁ፤ 28  ሆኖም ስፈልገው* የነበረውን ነገር ላገኘው አልቻልኩም። ከሺህ መካከል አንድ ወንድ* አገኘሁ፤ ከእነዚህ ሁሉ መካከል ግን አንዲትም ሴት አላገኘሁም። 29  ይህን አንድ ነገር ብቻ አገኘሁ፦ እውነተኛው አምላክ የሰውን ልጆች ቅን አድርጎ ሠራቸው፤+ እነሱ ግን ሌላ ብዙ ዕቅድ አወጡ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መልካም ዝና።” ቃል በቃል “ስም።”
ወይም “ፈንጠዝያ ባለበት።”
ቃል በቃል “በመንፈስህ ለቁጣ አትቸኩል።”
“ቁጣ የሞኝ ሰው መለያ ስለሆነ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
በሕይወት ያሉትን ያመለክታል።
ወይም “ማወቅ።”
ወይም “በክፉ።”
ቃል በቃል “ሲረግምህ።”
ወይም “ነፍሴ ስትፈልገው።”
ወይም “ቅን ወንድ።”