በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ከራሴ ፍጽምና እጠብቃለሁ?

ከራሴ ፍጽምና እጠብቃለሁ?
  •   ሁሉንም ፈተናዎች መድፈን አለብኝ ብለህ የምታስብ ከሆነ

  •   ብሳሳትስ ብለህ በማሰብ አዳዲስ ነገሮችን መሞከር የምትፈራ ከሆነ

  •   የሚሰጡህን አስተያየቶች ሁሉ እንደ ትችት የምትመለከታቸው ከሆነ

 ከላይ ለተነሳው ጥያቄ የምትሰጠው መልስ አዎ የሚል ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ይህ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል?

ከራስህ ፍጽምና መጠበቅህ ስህተት ነው?

  አንድን ሥራ ለማከናወን የምትችለውን ሁሉ ማድረግህ ምንም ስህተት የለውም። ሆኖም ፐርፌክሽኒዝም—ዋትስ ባድ አባውት ቢንግ ቱ ጉድ? የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “ጥሩ ደረጃ ላይ ለመድረስ በሚደረግ ጥረትና ሊደረስበት የማይችል ግብ ላይ ለመድረስ በመጣጣር መካከል ሰፊ ልዩነት አለ።” መጽሐፉ አክሎም “ከራስ ፍጽምናን መጠበቅ ከባድ ችግር ያስከትላል፤ ምክንያቱም ሁላችንም ፍጹም እንዳልሆንን አምነን መቀበል ይኖርብናል” ብሏል።

 መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ሐሳብ ይደግፋል። እንዲህ ይላል፦ “ሁልጊዜ ጥሩ ነገር የሚያደርግ . . . ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም።” (መክብብ 7:20) ፍጹም ስላልሆንክ አንዳንድ ነገሮችን የምታከናውንበት መንገድ ያን ያህል የሚያስደምም ላይሆን ይችላል።

 ይህን እውነታ አምነህ መቀበል ይከብድሃል? እንደዚያ ከሆነ ከራስህ ፍጽምና መጠበቅህ በየትኞቹ አራት መንገዶች ሊጎዳህ እንደሚችል ተመልከት።

  1.   ራስህን የምትመለከትበት መንገድ። ከራሳቸው ፍጽምና የሚጠብቁ ሰዎች ሊያሟሏቸው የማይችሏቸውን የላቁ መሥፈርቶች ለራሳቸው ያወጣሉ፤ በዚህም የተነሳ ደስታቸውን ያጣሉ። አሊሻ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እንደ እውነቱ ከሆነ በሁሉም ነገር የተሳካልን መሆን አንችልም፤ ፍጹም ባለመሆናችን ሁልጊዜ ራሳችንን የምንወቅስ ከሆነ በራስ የመተማመን ስሜታችንን እናጣለን። ይህ ደግሞ ለጭንቀት ይዳርገናል።”

  2.   የተሰጠህን ጠቃሚ ምክር የምትመለከትበት መንገድ። ከራሳቸው ፍጽምና የሚጠብቁ ሰዎች የሚሰጣቸውን ገንቢ ምክር ሆን ተብሎ ስማቸውን ለማጥፋት እንደተሰነዘረባቸው ትችት አድርገው ይመለከቱታል። “እርማት ሲሰጠኝ ይደብረኛል” ሲል ጄረሚ የተባለ አንድ ወጣት ተናግሯል። አክሎም “ከራስህ ፍጽምና የምትጠብቅ ከሆነ ያሉብህን የአቅም ገደቦች አምነህ መቀበል ልትቸገር እንዲሁም የሚደረግልህን እርዳታ ሳትጠቀምበት ልትቀር ትችላለህ” ብሏል።

  3.   ሌሎችን የምትመለከትበት መንገድ። ከራሳቸው ፍጽምና የሚጠብቁ ሰዎች ሌሎችን መተቸት ይቀናቸዋል፤ ይህን የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ግልጽ ነው። የ18 ዓመቷ አና “ከራስህ ፍጽምና የምትጠብቅ ከሆነ ሌሎችም ያንኑ መሥፈርት እንዲያሟሉ ትጠብቃለህ። ሌሎች ያንን መሥፈርት ሳያሟሉ በቀሩ ቁጥር ደግሞ ትናደድባቸዋለህ” ብላለች።

  4.   ሌሎች አንተን የሚመለከቱበት መንገድ። ከሌሎች የምትጠብቀው ነገር ምክንያታዊነት የጎደለው ከሆነ ሰዎች ይርቁሃል! ቤት የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ፍጽምናን የሚጠብቁብህ ሰዎች የሚያወጧቸውን ከአቅም በላይ የሆኑ መሥፈርቶች ለማሟላት መጣር በጣም አድካሚ ነው። እንዲህ ካለው ሰው ጋር መሆን የሚፈልግ ማንም የለም።”

ምን ብታደርግ የተሻለ ነው?

  መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ይላል። (ፊልጵስዩስ 4:5) ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች ከራሳቸውም ሆነ ከሌሎች በሚጠብቁት ነገር ረገድ ሚዛናዊ ናቸው።

 “ሌሎች የሚያሳድሩብን ጫና ራሱ ከባድ ነው። ታዲያ ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች ፍጽምናን በመጠበቅ ለምን አላስፈላጊ ጫና እንጨምራለን? ይሄን ሁሉ መሸከም በጣም አዳጋች ነው!”—ናይላ

 መጽሐፍ ቅዱስ “ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር [ሂድ]” ይላል። (ሚክያስ 6:8) ልካቸውን የሚያውቁ ሰዎች ያለባቸውን የአቅም ገደብ ይገነዘባሉ። ከአቅማቸው በላይ የሆነ ኃላፊነት አይቀበሉም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ሥራ ላይ ከሚገባው በላይ ረጅም ሰዓት አያጠፉም።

 “የተሰጡኝን ኃላፊነቶች በአግባቡ እየተወጣሁ እንዳለሁ እንዲሰማኝ ከፈለግኩ ለመሥራት ፈቃደኛ የምሆነው የምችለውን ያህል ብቻ ነው። በቃ መሥራት የምችለው ያንን ነው።”—ሄሊ

 መጽሐፍ ቅዱስ “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኃይልህ አከናውን” ይላል። (መክብብ 9:10) ስለዚህ ከራስህ ፍጽምና የመጠበቅ ችግር ካለብህ መፍትሔው ስንፍና ወይም ቸልተኝነት ሳይሆን በትጋት መሥራት ነው፤ ሆኖም ከላይ እንደተገለጸው ምክንያታዊ መሆንና ልክን ማወቅ ያስፈልጋል።

 “የተሰጠኝን ሥራ የምችለውን ያህል ጥሩ አድርጌ ለመሥራት እሞክራለሁ። ምንም እንከን የማይወጣለት ሥራ ማከናወን እንደማልችል ተገንዝቤያለሁ፤ ሆኖም የምችለውን ሁሉ ማድረጌ ያስደስተኛል።”—ጆሹዋ