በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

መሳደብ ያን ያህል መጥፎ ነገር ነው?

መሳደብ ያን ያህል መጥፎ ነገር ነው?

“ስድብ መስማት እጅግ ከመልመዴ የተነሳ አሁን አሁን ምንም አይሰቀጥጠኝም። ለእኔ ስድብ የተለመደ ነገር ሆኗል።”—ክሪስቶፈር፣ 17

“ወጣት እያለሁ ብዙ ጊዜ እሳደብ ነበር። ስድብ ለመልመድ ቀላል ለመተው ግን ከባድ የሆነ ልማድ ነው።”—ሬቤካ፣ 19

 ጥያቄ

  •   ሌሎች ሲሳደቡ ስትሰማ ምን ይሰማሃል?

    •  ልብ እንኳ አልለውም—ምንም አይመስለኝም።

    •  ትንሽ ይረብሸኛል—ሆኖም ብዙም አይሰቀጥጠኝም።

    •  ይሰቀጥጠኛል—ልለምደው አልቻልኩም።

  •   ተሳድበህ ታውቃለህ?

    •  አላውቅም

    •  አንዳንዴ

    •  ብዙ ጊዜ

  •   መጥፎ ቃላት ስለ መጠቀም ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?

    •  ምንም ማለት አይደለም

    •  ከባድ ጉዳይ ነው

 ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

 መሳደብ ከባድ ነገር እንደሆነ ይሰማሃል? ‘አይሰማኝም’ ትል ይሆናል። ‘ደግሞም ስንት የሚያስጨንቅ ጉዳይ እያለ ይህ ምን ያሳስባል? ሁሉም ሰው አይደል እንዴ የሚሳደበው!’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ታዲያ ይህ እውነት ነው?

 ብታምንም ባታምንም መጥፎ ቃላት ከመጠቀም የሚቆጠቡ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች የሚያውቁት ሌሎች ግን የማያውቋቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣

  •  መሳደብ እንዲያው መጥፎ ቃላት የማውጣት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የምትናገረው ነገር ውስጣዊ ማንነትህን ይገልጻል። እንግዲያው መጥፎ ቃላት መጠቀምህ ለሌሎች ስሜት ግድ እንደሌለህ ሊጠቁም ይችላል። በእርግጥ አንተ እንዲህ ዓይነት ሰው ነህ?

     መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከአፍ የሚወጣ ሁሉ ከልብ ይወጣል።”—ማቴዎስ 15:18

    አስጸያፊ ቃላት ብክለት ያስከትላል። ታዲያ ሌሎችንም ሆነ ራስህን ለምን ትበክላለህ?

  •  መሳደብ ሌሎች አንተን በአሉታዊ መንገድ እንዲያስቡህ ሊያደርግ ይችላል። ካስ ኮንትሮል (ስድብን ማስወገድ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የምንናገርበት መንገድ ለጓደኝነት በሚመርጡን ሰዎች፣ ከቤተሰባችንም ሆነ አብረውን ከሚሠሩ ሰዎች ዘንድ በምናተርፈው አክብሮት፣ ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት፣ በሌሎች ዘንድ ባለን ተሰሚነት፣ ሥራ ወይም እድገት በማግኘታችን አልፎ ተርፎም የማያውቁን ሰዎች ለእኛ ባላቸው አመለካከት ረገድ ለውጥ ያመጣል።” አክሎም “‘ባልሳደብ ኖሮ ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ይበልጥ የተሻለ ይሆን ነበር?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ” ብሏል።

     መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ስድብ ሁሉ . . . ከእናንተ መካከል ይወገድ።”—ኤፌሶን 4:31

  •  መሳደብ አንተ እንደምታስበው አሪፍ አያስብልህም። ሃው ሩድ! በተባለው መጽሐፍ ላይ ዶክተር አሌክስ ፓከር “ሁልጊዜ የሚሳደቡ ሰዎችን መስማት አሰልቺ ነው” በማለት ተናግረዋል። አክለውም አስጸያፊ ቃላት የሚናገር ሰው “አስተዋይ፣ ለዛ ያለው፣ አዋቂ ወይም አዛኝ ሊሆን አይችልም። የምትናገረው ነገር ዋዛ የሞላበት፣ የማይጨበጥና ፍሬከርስኪ ከሆነ አስተሳሰብህም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ምንም ጥያቄ የለውም” ብለዋል።

     መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የበሰበሰ ቃል ከቶ ከአፋችሁ አይውጣ።”—ኤፌሶን 4:29

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

  •  ግብ አውጣ። በአንድ ወር ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ መጥፎ ቃላትን ለማስወገድ ለምን ጥረት አታደርግም? የምታደርገውን መሻሻል በሰንጠረዥ ወይም በቀን መቁጠሪያ ላይ ማስፈር ትችላለህ። በውሳኔህ ለመጽናት ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ ሊያስፈልግህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፦

  •  አእምሮህ በመጥፎ ቃላት እንዲሞላ ከሚያደርጉ መዝናኛዎች ራቅ። መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት ጥሩውን ሥነ ምግባር ያበላሻል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33 የግርጌ ማስታወሻ) “ጓደኝነት” ሰዎችን ብቻ ሳይሆን የምትዝናናበትን ማለትም የምትመለከተውን ፊልም፣ የምትጫወተውን የቪዲዮ ጌም፣ የምትሰማውን ሙዚቃ ይጨምራል። የ17 ዓመቱ ኬኔት እንዲህ ይላል፦ “አንድ ዘፈን ምቱ ስለማረከህ ብቻ ግጥሙ ስድብ እንዳለው እንኳ ሳታስተውል አብረህ ልትዘፍን ትችላለህ።”

  •  ብስለት ያለው ሰው መሆንህን አሳይ። አንዳንድ ሰዎች አስጸያፊ ስድብ የሚሳደቡት የትልቅ ሰው መገለጫ እንደሆነ ስለሚሰማቸው ነው። እውነታው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የጎለመሱ ሰዎች “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን” እንደሚያሠለጥኑ ይናገራል። (ዕብራውያን 5:14) የጎለመሱ ሰዎች ደግሞ ሌሎችን “ለማስደመም” ሲሉ አቋማቸውን አያላሉም።

 በእርግጥም፣ መጥፎ ንግግር አእምሮን በመጥፎ ሐሳቦች ከመበከል (አካባቢንም ይበክላል) ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም። ይህ ዓለም ደግሞ ቀድሞውን ቢሆን ተበክሏል! ካስ ኮንትሮል የተባለው መጽሐፍ “የሞላው ላይ አንተ ደግሞ አትጨምር” ይላል። “በመጥፎ ንግግር የተበከለውን አካባቢህን ለማጽዳት የበኩልህን አድርግ። እንዲህ ካደረግህ ለራስህ ጥሩ ግምት ይኖርሃል፤ ሌሎችም ስለ አንተ ጥሩ አመለካከት ይኖራቸዋል።”