በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

በርቀት ትምህርት ስኬታማ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

በርቀት ትምህርት ስኬታማ መሆን የምችለው እንዴት ነው?

 በአሁኑ ወቅት ብዙ ተማሪዎች እየተማሩ ያሉት ትምህርት ቤት ሄደው ሳይሆን ቤታቸው ውስጥ ሆነው ነው። አንተም የምትማረው በርቀት ከሆነ ስኬታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ከዚህ በታች አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል። a

 ስኬታማ ለመሆን የሚረዱ አምስት ጠቃሚ ሐሳቦች

  •   ፕሮግራም አውጣ። ትምህርት ቤት ብትሄድ ኖሮ እንደምታደርገው ቋሚ ፕሮግራም ለማውጣት ጥረት አድርግ። ለትምህርት፣ ለቤት ውስጥ ሥራና ለሌሎች አስፈላጊ ሥራዎች ጊዜ መድብ። እንደ አስፈላጊነቱ ፕሮግራምህን ማስተካከል ትችላለህ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን።”—1 ቆሮንቶስ 14:40

     “ትምህርት ቤት እንደሚሄድ ሰው ፕሮግራምህን አደራጅ። ሥራዎችህን በተወሰነ ሰዓት ማከናወን አለብህ።”—ኬቲ

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ፕሮግራምህን በጽሑፍ ማስፈርና በቀላሉ በሚታይ ቦታ ማስቀመጥ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

  •   ራስህን ግዛ። አንዱ የእድገት ክፍል ተነሳሽነት በማይኖርህ ጊዜም ጭምር ሥራህን ማከናወን እንዳለብህ ማወቅ ነው። ዛሬ ነገ አትበል!

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ታታሪዎች ሁኑ እንጂ አትስነፉ።”—ሮም 12:11

     “ከባዱ ነገር ራስን መግዛት ነው። ሰበብ ማቅረብና ‘የትምህርት ቤት ሥራዬን በኋላ እሠራዋለሁ’ ብሎ ማሰብ ቀላል ነው። ግን በኋላም ሳትሠራው ትቀራለህ፤ በመጨረሻም ሥራው ይከመርብሃል።”—አሌክሳንድራ

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የትምህርት ቤት ሥራህን በየቀኑ በተመሳሳይ ጊዜና በተመሳሳይ ቦታ መሥራትህ ራስህን ለመግዛት የሚረዳህ እንዴት ነው?

  •   የምታጠናበት ቦታ መድብ። የሚያስፈልጉህን መሣሪያዎች አዘጋጅ። የምትማርበት ቦታ ምቹ እንዲሆን አድርግ፤ ግን ከልክ በላይ አትመቻች። የተቀመጥከው ልትማር እንጂ ልትተኛ አይደለም! ለትምህርት የሚሆን ቦታ መመደብ ካልቻልክ በትምህርት ሰዓት ኩሽናውን ወይም መኝታ ቤትህን እንደ መማርያ ክፍል አድርገህ ልትጠቀምበት ትችላለህ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።”—ምሳሌ 21:5

     “ኳስህንና የቪዲዮ ጌሞችህን ከአካባቢው አርቅ፤ የስልክህን ድምፅ አጥፋ፤ እንዲሁም ጊታሩን ወደ ማስቀመጫው መልስ። ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች በአቅራቢያህ ሊኖሩ አይገባም።”—ኤሊዛቤት

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የምታጠናበት ቦታ ለትምህርት የተመቻቸ እንዲሆን ምን ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችላለህ?

  •   ትኩረትህን ሰብስብ። በትምህርትህ ላይ ብቻ አተኩር። በአንድ ጊዜ ብዙ ነገር ለመሥራት የምትሞክር ከሆነ ስህተት መሥራትህ አይቀርም፤ እንዲሁም ሥራህን ለመጨረስ ብዙ ጊዜ ይፈጅብሃል።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌሶን 5:16

     “ስልኬ አጠገቤ ሆኖ ትኩረቴን መሰብሰብ በጣም ይከብደኝ ነበር። አላስፈላጊ ነገር በመሥራት ብዙ ጊዜ አጠፋ ነበር።”—ኦሊቪያ

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ትኩረትህ ሳይከፋፈል አንድን ትምህርት ማጥናት የምትችልበትን ሰዓት ቀስ በቀስ ማሳደግ ትችል ይሆን?

  •   እረፍት አድርግ። በእግርህ ተንሸራሸር፣ ብስክሌት ንዳ ወይም ስፖርት ሥራ። የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያም ዘና ሊያደርግህ ይችላል። ሆኖም ስኩል ፓወር የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “በመጀመሪያ ሥራህን አጠናቅቅ። የቀረህ ሥራ እንደሌለ ማወቅህ እረፍትህ እውነተኛ እረፍት እንዲሆን ያደርገዋል።”

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል።”—መክብብ 4:6

     “ትምህርት ቤት ውስጥ ስንማር የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ወይም ሥዕል መሣልም እንማራለን። እነዚህ ነገሮች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ የገባኝ ሲቀሩብኝ ነው። ከትምህርት ጎን ለጎን የፈጠራ ችሎታን የሚያሳድጉ አዝናኝ ነገሮችንም ማድረግ ጠቃሚ ነው።”—ቴይለር

     ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ስታጠና አእምሮህን ለማደስ የሚያስችልህ ምን ዓይነት እረፍት ነው?

a የተለያዩ ዓይነት የርቀት ትምህርት አማራጮች አሉ። በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡትን ሐሳቦች ከአንተ ሁኔታ ጋር በሚስማማ መንገድ ተግባራዊ ልታደርጋቸው ትችላለህ።