በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ስሜቴን መቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

“አንዳንድ ቀን ጥሩ ስሜት ይሰማኛል፤ በሌላ ቀን ደግሞ በሐዘን እዋጣለሁ። ትላንት እንደ ቀላል ያየሁት ጉዳይ ዛሬ ተራራ ይሆንብኛል።”—ካሪሳ

ስሜትህ በድንገት እየተለዋወጠብህ ተቸግረሃል? a ከሆነ ይህ ርዕስ ሊረዳህ ይችላል!

 ምክንያቱ ምንድን ነው?

 በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚያጋጥሙህ የተለመዱ ለውጦች መካከል አንዱ የስሜት መለዋወጥ ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ሆነህ እንኳ ስሜትህ በድንገት ሲለዋወጥ ተመልክተህ ይሆናል።

 ስሜቶችህ የሚለዋወጡት ለምን እንደሆነ ባለማወቅህ ግራ ተጋብተህ ሊሆን ይችላል። ይህ የሚያጋጥምህ ሆርሞኖችህ ላይ ለውጥ ስለሚኖር እንዲሁም በራስ አለመተማመን እና ጥርጣሬ ስለሚፈጠርብህ መሆኑን አስታውስ። ይህ ደግሞ የእድገትህ አንዱ ክፍል ነው። ደስ የሚለው ግን እነዚህን ስሜቶች መረዳት አልፎ ተርፎም መቆጣጠር ትችላለህ።

 የሕይወት እውነታ፦ ወጣት እያለህ ስሜቶችህን እንዴት መቆጣጠር እንደምትችል ማወቅህ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ይህን ችሎታ ትልቅ ሰው ስትሆን በሚያጋጥሙህ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ትጠቀምበታለህ።

አሉታዊ ስሜቶች መንገድ ላይ እንዳሉ ጉድጓዶች ናቸው። ጥሩ ችሎታ ካለህ፣ ጉድጓዶቹን በዘዴ በማለፍ ጉዞህ የተቃና እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ

 ማድረግ የምትችላቸው ሦስት ነገሮች

 ተናገር። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው” ይላል።—ምሳሌ 17:17

 “እንደ አክስቴ የማያት የቤተሰባችን ወዳጅ አለች። ስናገር በደንብ ስለምታዳምጠኝ ስሜቴን በነፃነት አውጥቼ እነግራታለሁ። አመለካከቴ ትክክል ሲሆን በጣም ትደሰትብኛለች፤ ስሳሳት ደግሞ እኔን ለማስተካከል አቅሟ የሚፈቅደውን ሁሉ ታደርጋለች።”—ዮላንዳ

 ጠቃሚ ምክር፦ እንዳንተው ስሜታቸውን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ካሉ እኩዮችህ ጋር ብቻ ከማውራት ይልቅ ከወላጆችህ ወይም ከምታምነው ትልቅ ሰው ጋር ተነጋገር።

 ጻፍ። መጽሐፍ ቅዱስ በጭንቀት ውስጥ የነበረው ኢዮብ “አንዳች ሳላስቀር ብሶቴን አሰማለሁ። በታላቅ ምሬት እናገራለሁ!” ብሎ እንደነበር ይናገራል። (ኢዮብ 10:1) የተሰማህን ስሜት በጽሑፍ ማስፈር፣ ለአንድ ሰው በቃል ከመንገር በተጨማሪ ስሜትህን አውጥተህ ‘መናገር’ የምትችልበት ሌላው መንገድ ነው።

 “ሁልጊዜ ትንሽ ማስታወሻ ደብተር እይዛለሁ። የሚያናድድ ነገር ሲያጋጥመኝ ስለ ሁኔታው እጽፋለሁ። ይህም ፍቱን መድኃኒት ሆኖልኛል።”—ኢሊያና

 ጠቃሚ ምክር፦ የሚሰሙህን ስሜቶች፣ መነሻቸው ምን እንደሆነ እንዲሁም እንዴት ልትቆጣጠራቸው እንደምትችል የምትጽፍበት ማስታወሻ ያዝ። ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዞ የተዘጋጀው የመልመጃ ሣጥን በዚህ ረገድ ሊረዳህ ይችላል።

 ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል። ጻድቁ እንዲወድቅ ፈጽሞ አይፈቅድም።”—መዝሙር 55:22

 “በምጨነቅበት ጊዜ ሳላቋርጥ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። የልቤን አውጥቼ ከነገርኩት በኋላ እረፍት ይሰማኛል።”—ጃስሚን

 ጠቃሚ ምክር፦ በጭንቀት ስሜት እንድትዋጥ ያደረገህ ነገር ቢኖርም እንኳ በሕይወትህ ውስጥ አመስጋኝ እንድትሆን የሚያደርጉህን ሦስት ነገሮች አስብ። ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ፤ ይህን ስታደርግ ግን ስላገኘሃቸው መልካም ነገሮች ማመስገን እንዳለብ አትዘንጋ።

a ይህ ርዕስ የሚናገረው በርካታ ወጣቶችን ሊያጋጥም ስለሚችል የተለመደ የስሜት መለዋጥ ነው። ባይፖላር ዲስኦርደር ወይም ሌላ ዓይነት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ካለብህ “የመንፈስ ጭንቀትን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።