በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ማሽኮርመም ምንም ጉዳት የለውም?

ማሽኮርመም ምንም ጉዳት የለውም?

 ማሽኮርመም ምንድን ነው?

 አንዳንድ ሰዎች ማሽኮርመም ማለት ለተቃራኒ ፆታ የፍቅር ስሜት እንዳለን የሚያስመስል ነገር መናገር ወይም ማድረግ ነው ይላሉ። ታዲያ ለአንድ ሰው የፍቅር ስሜት ማሳየት ስህተት ነው? ላይሆን ይችላል። አን የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የፍቅር ግንኙነት መመሥረት የምትችሉበት ዕድሜ ላይ ከደረሳችሁና የምትወዱት ሰው ካለ ግለሰቡ ለእናንተ ተመሳሳይ ስሜት እንዳለው ወይም እንደሌለው ማወቅ የሚቻልበት ሌላ ምን መንገድ አለ?”

 በዚህ ርዕስ ውስጥ የምንመለከተው ግን ለሚወዱት ሰው የፍቅር ስሜት ስለማሳየት ሳይሆን ከግለሰቡ ጋር የፍቅር ግንኙነት የመመሥረት ሐሳብ ሳይዙ ለግለሰቡ የፍቅር ስሜት እንዳለን የሚያስመስል ነገር ማድረግ የሚያስከተለውን መዘዝ ነው።

 “ከአንድ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት በማሰብ ለግለሰቡ ለየት ያለ ትኩረት መስጠት እና ለአንድ ሰው የፍቅር ስሜት ያላችሁ የሚያስመስል ነገር ስታደርጉ ከቆያችሁ በኋላ ድንገት ከእሱ ጋር ምንም ነገር የመመሥረት ሐሳብ እንደሌላችሁ በመናገር ግለሰቡን መጉዳት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።”—ዲያና

 አንዳንድ ሰዎች የሚያሽኮረምሙት ለምንድን ነው?

 አንዳንድ ሰዎች የሚያሽኮረምሙት ተወዳጅ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ለማድረግ ብለው ብቻ ነው። ሄይሊ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “በዚህ መንገድ የሰዎችን ትኩረት መሳብ እንደምትችሉ ስትገነዘቡ በድርጊታችሁ ለመቀጠል ልትነሳሱ ትችላላችሁ።”

 ነገር ግን ለአንድ ሰው የፍቅር ስሜት ሳይኖረን ግለሰቡ እንዲህ እንዲያስብ የሚያደርግ ነገር ማድረግ ለግለሰቡ ስሜት ጨርሶ ደንታ እንደሌለን የሚያሳይ ነው። ይህን የምናደርገው ተወዳጅ እንደሆንን እንዲሰማን ለማድረግ ብለን ብቻ ከሆነ ደግሞ የማመዛዘን ችሎታችን ራሱ ጥያቄ ላይ ይወድቃል። መጽሐፍ ቅዱስ “ማስተዋል የጎደለው ሰው ሞኝነት ያስደስተዋል” ይላል።—ምሳሌ 15:21

 ሄይሊ እንደተናገረችው “ማሽኮርመም መጀመሪያ ላይ ምንም ጉዳት የሌለው ይመስል ይሆናል፤ አብዛኛውን ጊዜ ግን መጨረሻው አያምርም።”

 ማሽኮርመም ምን አደጋዎች አሉት?

  •   ማሽኮርመም መልካም ስምህን ያበላሻል።

     “አንዲት ሴት የምታሽኮረምም ከሆነ ይህ በራሷ እንደማትተማመንና ብስለት እንደሚጎድላት ያሳያል። ለአንተ እውነተኛ ስሜት እንደሌላትና የምትፈልገው መጠቀሚያ ልታደርግህ ብቻ እንደሆነ እንዲሰማህ ያደርጋል።”—ጄረሚ

     መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

     ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ በሌሎች ዘንድ ‘የሚያሽኮረምም ሰው’ የሚል ስም ሊያሰጥህ የሚችለው ምን ዓይነት ነገር መናገርህ ወይም ማድረግህ ነው?

  •   ማሽኮርመም የምታሽኮረምመውን ሰው ይጎዳል።

     “ከሚያሽኮረምም ሰው ጋር አብሬ መሆን አልፈልግም። ከእኔ ጋር የሚያወራው ሴት ስለሆንኩ ብቻ እንደሆነ ይሰማኛል! የሚያሽኮረምሙ ሰዎች ስለ እኔ ግድ የላቸውም፤ የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ስሜት ብቻ ነው።”—ጃክሊን

     መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዱ ሰው ምንጊዜም የራሱን ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም ይፈልግ።”—1 ቆሮንቶስ 10:24

     ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ አንዲት ሴት ለአንተ የፍቅር ስሜት እንዳላት ተሰምቶህ በኋላ ግን እንደተሳሳትክ የተገነዘብክበት ወቅት አለ? ከሆነ በዚያ ጊዜ ምን ተሰማህ? አንተም በዚህ መንገድ ሌላን ሰው ላለመጉዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?

  •   ማሽኮርመም እውነተኛ የፍቅር ግንኙነት የመመሥረት አጋጣሚህን ያበላሽብሃል።

     “የሚያሽኮረምም ሰው እንኳን ለጋብቻ ለፍቅር ጓደኝነት እንኳ የሚፈልገው የለም። አስመሳይ ሰው ከሆነ እውነተኛ ማንነቱን ማወቅም ሆነ እሱን ማመን በጣም ከባድ ነው።”—ኦሊቪያ

     መዝሙራዊው ዳዊት ‘ማንነታቸውን ከሚደብቁ ሰዎች እርቃለሁ’ በማለት የተናገረው ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል።—መዝሙር 26:4

     ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች፦ አንድ ሰው የሚያሽኮረምም ከሆነ የሚስበው የምን ዓይነት ሰዎችን ትኩረት ነው? አንተ እንዲህ ያሉ ሰዎችን ትኩረት መሳብ ትፈልጋለህ?