በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | የወጣቶች ጥያቄ

የሚሰጥህን እርማት እንዴት ልትቀበል ይገባል?

የሚሰጥህን እርማት እንዴት ልትቀበል ይገባል?

ተፈታታኙ ነገር

“በመሠረቱ አንድ ሰው እርማት ሲሰጥህ አንድ የተሳሳተ ነገር እንዳደረግክ እየነገረህ ነው፤ መቼም ‘ተሳስተሃል ስባል ደስ ይለኛል’ የሚል ሰው ያለ አይመስለኝም።”—ኤሚ፣ ዕድሜ 17 *

እርማት የማይቀበል ሰው፣ ከበረራ መቆጣጠሪያ ክፍል የሚሰጠውን መመሪያ አልቀበልም እንደሚል የአውሮፕላን አብራሪ ነው። መዘዙ በጣም አስከፊ ይሆናል።

ወላጆችህ፣ አስተማሪዎችህና ሌሎች ትላልቅ ሰዎች እርማት ሲሰጡህ መቀበል ይከብድሃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ይረዳሃል።

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

ሁሉም ሰው እርማት ያሰፈልገዋል።

“ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።”—ያዕቆብ 3:2

“ተሳስተህ እርማት ቢሰጥህ ምንም አያሳፍርም።”—ጄሲካ

እርማት የተሰጠህ መጥፎ ልጅ ስለሆንክ አይደለም።

“አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወደውን ይገሥጻል።”—ምሳሌ 3:12

“ሰዎች እርማት በሚሰጡኝ ጊዜ ይህን ማድረግ ለእነሱ ምን ያህል ከባድ እንደሚሆንባቸውና ይህን ያደረጉት በጣም ቢወዱኝ እንደሆነ ለማሰብ እሞክራለሁ።”—ታማራ

እርማት የተሻልክ ሰው እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል።

“ምክሬን አድምጡ፤ ጥበበኞች ሁኑ።”—ምሳሌ 8:33

“በሳል ሰው እንድትሆን እርማት ያስፈልግሃል። እርማት ሌሎች አንተን የሚመለከቱህ እንዴት እንደሆነ እንድታስተውል የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ በራስህ ላይ መኖሩን ያላስተዋልከውን መጥፎ ጠባይ እንድታሻሽል ይረዳሃል።”—ዲያን

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

ምክንያታዊ ሆነህ አስብ። እርማት ሲሰጥህ ቶሎ ልትከፋ ትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ስሜታዊ አትሁን። እንዲህ ለማድረግ እንዲረዳህ ለጊዜው የአንተን ሁኔታ ተወት አድርግና የተሰጠህን እርማት ለሌላ ሰው ምናልባትም ለታናሽ ወንድምህ እንደምትሰጥ አድርገህ አስብ። ታዲያ ምክሩ ተገቢ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ታየህ? አሁን ደግሞ ወደ አንተ ሁኔታ ተመልሰህ ጉዳዩን በተመሳሳይ መንገድ ለማየት ሞክር።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መክብብ 7:9

“አንዳንድ ጊዜ በተሰጠህ እርማት በጣም ከመበሳጨትህ የተነሳ ግለሰቡ ምክር የሰጠህ ስሜትህን ለመጉዳት ብሎ ሳይሆን የተሻልክ ሰው እንድትሆን ለመርዳት አስቦ እንደሆነ ትረሳለህ።”—ቴሬሳ

ትሑት ሁን። ኩራት እርማት ከመቀበል እንዲያግድህ አትፍቀድ። በሌላ በኩል ደግሞ ልታሻሽለው የሚገባህ ነገር መኖሩ በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንድትዋጥ ሊያደርግህ አይገባም። ወደ ሁለቱም ጽንፍ እንዳትሄድ የሚረዳህ ትሕትና ነው። በጣም እንደጎዳህ የተሰማህ እርማት እንዲያውም በጣም የሚያስፈልግህ ሊሆን ይችላል። ምክንያትህ ምንም ይሁን ምን እርማቱን ካልተቀበልክ በሳል ሰው እንድትሆን የሚረዳህ አንድ ግሩም አጋጣሚ ያመልጥሃል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 16:18

በጣም እንደጎዳህ የተሰማህ እርማት እንዲያውም በጣም የሚያስፈልግህ ሊሆን ይችላል

“እርማት መቀበል አንድ ሰው ብስለት ያለው አዋቂ መሆኑ ከሚታይበት ወሳኝ መንገዶች አንዱ ነው። እርማት የመቀበል ልማድ ካላዳበርንና ለውጥ ለማድረግ የማንነሳሳ ከሆነ የኋላ ኋላ የምንጎዳው እኛው ነን።”—ሊና

አመስጋኝ ሁን። እርማቱን መቀበል ቢከብድህም እንኳ እርማቱን የሰጠህን ሰው ለምን አታመሰግነውም? ምክንያቱም ግለሰቡ ከልብ እንደሚያስብልህና ከሁሉ የተሻለውን እንደሚመኝልህ የታወቀ ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መዝሙር 141:5

“በተለይ ምክሩ የሚያስፈልግህ ከሆነ ‘አመሰግናለሁ’ ብትል ምንም የሚጎዳህ ነገር የለም። ምክሩ ባያስፈልግህ እንኳ ግለሰቡ አንተን ለማናገር ጥረት በማድረጉ ልታመሰግነው ትችላለህ።”—ካርላ

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።