በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ፍቅር ነው ጓደኝነት?​—ክፍል 1፦ እያስተላለፈልኝ ያለው ምን ዓይነት መልእክት ነው?

ፍቅር ነው ጓደኝነት?​—ክፍል 1፦ እያስተላለፈልኝ ያለው ምን ዓይነት መልእክት ነው?

 ልጁን በጣም ትወጅዋለሽ፤ a እሱም እንደ አንቺ እንደሚሰማው እርግጠኛ ነሽ። ምክንያቱም ሁልጊዜ የስልክ መልእክት ትለዋወጣላችሁ፤ ሌሎች ሰዎች ባሉበትም እንኳ ሁለታችሁ ብቻችሁን ነጠል ብላችሁ ታወራላችሁ፤ . . . የሚልካቸው አንዳንድ መልእክቶች ደግሞ ለአንቺ የፍቅር ስሜት እንዳለው በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው።

 በመሆኑም ቅርርባችሁ ወደ ፍቅር ጓደኝነት ሊያድግ ይችል እንደሆነና እሱም ተመሳሳይ ስሜት እንዳለው ለማረጋገጥ ስትዪ ልታናግሪው ትወስኛለሽ። ታዲያ ምን ምላሽ ሰጠሽ? “እኔ እንደ ጓደኛ እንጂ ከዚያ በተለየ መንገድ አላይሽም” አለሽ።

 ምን ስሜት ይፈጥራል?

 “በእሱም ሆነ በራሴ በጣም ተበሳጨሁ! በየቀኑ መልእክት እንላላክ ነበር፤ ደግሞም ልዩ ትኩረት ሰጥቶኝ ነበር። ስለዚህ ሳላስበው እየወደድኩት መጣሁ።”—ጃዝሚን

 “እኔና አንዲት ልጅ፣ የሆኑ ሰዎች ሲጠናኑ አብረናቸው እንሄድ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ፣ ጥንድ ጥንድ ሆነን እየተጠናናን ያለን ነበር የሚመስለው። ሁለታችን ብዙ እናወራ ነበር፤ በኋላም አዘውትረን የስልክ መልእክት መላላክ ጀመርን። ልጅቷ ለእኔ ከጓደኝነት ያለፈ ስሜት እንደሌላት እንዲያውም የወንድ ጓደኛ እንዳላት ስትነግረኝ ነገሩን ለመቀበል በጣም ነበር የተቸገርኩት።”—ሪቻርድ

 “አንድ ልጅ በየቀኑ መልእክት ይልክልኝ ነበር፤ ሁለታችንም የፍቅር ስሜት እንዳለን የሚያሳይ ነገር የምናደርግበት ጊዜም ነበር። እንደምወደው ስነግረው ግን ሳቅ አለና ‘በአሁኑ ጊዜ ከማንም ጋር የፍቅር ጓደኝነት መጀመር አልፈልግም!’ አለኝ። አልቅሼ ሊወጣልኝ አልቻለም።”—ታማራ

 ዋናው ነጥብ፦ ከአንድ ሰው ጋር ያላችሁ ቅርርብ ለየት ያለ እንደሆነ ታስቡ ይሆናል፤ ግለሰቡ እንደ እናንተ ዓይነት ስሜት እንደሌለው ስታውቁ ብትበሳጩ፣ ብታፍሩ አልፎ ተርፎም እንደተታለላችሁ ቢሰማችሁ አያስገርምም። ስቲቨን የተባለ አንድ ወጣት “እንዲህ ዓይነት ነገር ባጋጠመኝ ጊዜ በጣም ነው ያዘንኩት፤ ስሜቴ ተጎድቶ ነበር። ከዚያ ወዲህ ሰው ለማመን ረጅም ጊዜ ወስዶብኛል” በማለት ተናግሯል።

 ይህ የሚያጋጥመው ለምንድን ነው?

 የጽሑፍ መልእክትና ማህበራዊ ድረ ገጽ ለአንቺ ምንም የፍቅር ስሜት ለሌለው ሰው በቀላሉ የፍቅር ስሜት እንድታዳብሪ ሊያደርግሽ ይችላል። አንዳንድ ወጣቶች የሚሉትን ተመልከቺ፦

 “አንድ ሰው መልእክት የሚልክላችሁ ሥራ ስለፈታ ይሆናል፤ እናንተ ግን ልዩ ትኩረት እንደሰጣችሁ ሊሰማችሁ ይችላል። መልእክት የሚልክላችሁ በየቀኑ ከሆነ ደግሞ ለእናንተ ለየት ያለ ስሜት እንዳለው አድርጋችሁ ታስባላችሁ።”—ጄኒፈር

 “አንደኛው ወገን የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ይፈልግ ይሆናል፤ ሌላኛው ግን እንዲሁ የሚያዋራው ሰው ለማግኘት ወይም ደግሞ ተፈላጊ እንደሆነ እንዲሰማው ስለፈለገ ብቻ ሊሆን ይችላል።”—ጄምስ

 “‘መልካም ምሽት’ የሚለው የተለመደ መልእክት እንኳ የፍቅር ስሜት እንደሚያስተላልፍ የሚሰማው ሰው ይኖራል፤ መልእክቱን የላከው ሰው ግን ለዚያ ግለሰብ ምንም የፍቅር ስሜት ላይኖረው ይችላል።”—ሄይሊ

 “ስማይሊ ፌስ [:-)] ብልክ ተቀባዩ፣ እንዲሁ ደስ የሚል ነገር እንደላክሁለት አሊያም ደግሞ የፍቅር መልእክት እያስተላለፍኩ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ፣ መልእክቱ የተላከለት ሰው ሌላኛው ወገን ለእሱ የፍቅር ስሜት እንዳለው ሊያስብ ይችላል።”—አሊስያ

 ዋናው ነጥብ፦ አንድ ሰው ትኩረት ሰጠሽ ማለት ይወድሻል ማለት እንዳልሆነ አስታውሺ።

 እርግጥ ይህን ማድረግ የመናገሩን ያህል ቀላል አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም” ይላል። (ኤርምያስ 17:9) ልብሽ ሊያታልልሽና አንድ ሰው እንደወደደሽ አድርገሽ ልታስቢ ትችያለሽ፤ ይሁንና በአሸዋ እንደተገነባ ቤት ሁሉ፣ በአእምሮሽ የሳልሽው የፍቅር ግንኙነትም እውነታውን ስታውቂ እንዳልነበር ይሆናል።

 ምን ማድረግ ትችያለሽ?

  •   ስሜታዊ አትሁኚ። ቆም ብለሽ ስለ ግንኙነታችሁ አስቢ። ‘ይህ ሰው ከሌሎች የተለየ ትኩረት ይሰጠኛል ብዬ እንዳስብ የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት አለኝ?’ ብለሽ ራስሽን ጠይቂ። ስሜትሽ ‘የማሰብ ችሎታሽን’ እንዲጋርደው አትፍቀጂ።—ሮም 12:1

  •   አስተዋይ ሁኚ። ቅርርባችሁ ከጓደኝነት ያለፈ እንደሆነ እንድታስቢ ከሚያደርጉሽ ምክንያቶች ይልቅ ይህን እንድትጠራጠሪ በሚያደርጉሽ ምክንያቶች ላይ የበለጠ ትኩረት አድርጊ። አንቺ ለዚያ ሰው የፍቅር ስሜት ስላለሽ ብቻ እሱም ተመሳሳይ ስሜት ይኖረዋል ብለሽ አትደምድሚ።

  •   ታጋሽ ሁኚ። ሌላኛው ወገን በመካከላችሁ ያለው ቅርርብ ከተራ ጓደኝነት ያለፈ እንዲሆን የሚፈልግ መሆኑን በቀጥታ እስካልነገረሽ ድረስ ለግለሰቡ የፍቅር ስሜት ላለማዳበር ተጠንቀቂ።

  •   ግልጽ ሁኚ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመናገር ጊዜ አለው’ ይላል። (መክብብ 3:7) አንድ ሰው ለአንቺ ከጓደኝነት ያለፈ ስሜት እንዳለው ማወቅ ከፈለግሽ ግለሰቡን አነጋግሪው። ቫለሪ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እሱም እንደ አንቺ ዓይነት ስሜት ከሌለው፣ ይህን ከጊዜ በኋላ ከማወቅ ይልቅ አሁኑኑ ቁርጡን ማወቅሽ የሚደርስብሽን ጉዳት ይቀንሰዋል።”

 ዋናው ነጥብ፦ ምሳሌ 4:23 “ልብህን ጠብቅ” ይላል። ለአንድ ሰው የፍቅር ስሜት እያዳበርሽ ከሆነ እሱም እንደ አንቺ ዓይነት ስሜት ያለው መሆኑን ለማወቅ ሞክሪ። ይህን ከማወቅሽ በፊት በልብሽ ፍቅር ማዳበር፣ ድንጋይ ላይ ተክል እንደ መትከል ነው።

 የምትወጂው ልጅ ለአንቺ የፍቅር ስሜት እንዳለው ካወቅሽ እንዲሁም የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዕድሜሽ ከደረሰና ዝግጁ ከሆንሽ ግንኙነቱን የመጀመር ያለመጀመሩ ጉዳይ የአንቺ ውሳኔ ነው። ጠንካራ ትዳር፣ ተመሳሳይ መንፈሳዊ ግብ ያላቸው እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ግልጽና ሐቀኛ የሆኑ ሰዎች ጥምረት መሆኑን አስታውሺ። (1 ቆሮንቶስ 7:39) እነዚህ ሰዎች የፍቅር ግንኙነት ከመጀመራቸው በፊት ጥሩ ጓደኛሞች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ከተጋቡም በኋላ ጓደኝነታቸው ይቀጥላል።—ምሳሌ 5:18

a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በሴት ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።