በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ስለ ሴክስቲንግ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ስለ ሴክስቲንግ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

 ሴክስቲንግ ምንድን ነው?

 “ሴክስቲንግ” እርቃንን የሚያሳዩ ወይም ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ፎቶግራፎችን፣ ቪዲዮዎችን እንዲሁም የጽሑፍ መልእክቶችን በሞባይል አማካኝነት መላክ ማለት ነው። “እንዲህ ዓይነቱ ነገር በጣም የተለመደ እየሆነ መጥቷል” በማለት አንድ ሰው ተናግሯል። “ከአንድ ሰው ጋር ጥቂት የጽሑፍ መልእክቶችን ከተላላክህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እርቃንን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን መለዋወጥ ትጀምራለህ።”

 ሰዎች እንዲህ ዓይነት ነገሮችን የሚላላኩት ለምንድን ነው? አንድ ተሞክሮ ያካበተ የሕግ ባለሙያ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ለተባለው ጋዜጣ እንደተናገረው ወጣቶች “የፍቅረኛቸውን እርቃን የሚያሳይ ፎቶግራፍ በሞባይል ስልካቸው ላይ መያዛቸው ወሲብ እንደሚፈጽሙ ለሌሎች ለማሳወቅ ያስችላቸዋል።” እንዲያውም በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ አንዲት ወጣት “አደጋ የማያስከትል ወሲብ” በማለት ጠርታዋለች። አክላም “ያልተፈለገ እርግዝና አይመጣባችሁም፤ እንዲሁም የአባለዘር በሽታዎች አይይዟችሁም” ብላለች።

 ወጣቶች እንዲህ ዓይነት መልእክት የሚልኩባቸው ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፦

  •   የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት የሚፈልጉትን ሰው ለማባበል።

  •   አንድ ሰው እንዲህ ያለ ፎቶግራፍ ሲልክላቸው ‘ውለታውን ለመመለስ’።

 ሴክስቲንግ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው?

 አንድ ፎቶ በሞባይል ልከሽ ከእጅሽ ከወጣ በኋላ መመለስ አትችዪም፤ የላክሽለት ሰው ፎቶግራፉን የሚጠቀምበትን መንገድ መቆጣጠር አትችዪም። ምናልባት ግለሰቡ በፎቶግራፉ ተጠቅሞ ያደረገው ነገር ስምሽ እንዲጠፋ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። በፒው የምርምር ማዕከል ውስጥ ተመራማሪ የሆነችውና ስለ ሴክስቲንግ ጽሑፍ ያዘጋጀችው አማንዳ ሌንሃርት እንዲህ ብላለች፦ “የሌሎች ስህተትና ጥፋት በቀላሉ እንዲታወቅና ለብዙ ጊዜ ሌሎች ዘንድ እንዲቀመጥ የሚያደርግ ሌላ ነገር የለም።”

 አንዳንድ ጊዜ ደግሞ

  •    እርቃን የሚያሳይ ፎቶግራፍ የተላከለት ሰው ጓደኞቹን ለማዝናናት ሲል ፎቶውን ለብዙ ሰዎች ያሰራጨዋል።

  •    ከሴት ጓደኛቸው ጋር የተለያዩ ወንዶች፣ እሷን ለመበቀል ሲሉ እንዲህ ያለውን ፎቶግራፍ ያሰራጫሉ።

 ይህን ታውቂ ነበር? እርቃንን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን መላክ ልጆችን እንደ ማስነወር ወይም የልጆች ፖርኖግራፊን እንደ ማሰራጨት ሊቆጠር ይችላል። እንዲያውም እንዲህ ዓይነት መልእክት የሚልኩ አንዳንድ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ሌሎችን በፆታ በማስነወር ወንጀል ተከስሰዋል።

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ በትዳር ውስጥ የፆታ ፍላጎትን ማርካት ተገቢ እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 5:18) ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸሙ ወሲባዊ ድርጊቶችን ግን በግልጽ ያወግዛል። የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንደ ምሳሌ እንውሰድ፦

  •   “ዝሙትና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ፤ አሳፋሪ ምግባር፣ የማይረባ ንግግርም ሆነ ጸያፍ ቀልድ የማይገቡ ነገሮች ናቸው።”​—ኤፌሶን 5:3, 4

  •   “በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና . . . መጎምጀት ናቸው።”​—ቆላስይስ 3:5

 እነዚህ ጥቅሶች የሚያስጠነቅቁት ‘ከዝሙት’ (ከትዳር ውጪ ከሚፈጸም የፆታ ግንኙነት) ብቻ ሳይሆን እንደ “ርኩሰት” (ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናን የሚያጎድሉ ድርጊቶችን በሙሉ ያመለክታል) እና “የፆታ ምኞት” (ተፈጥሯዊ የሆነውንና አንድ ሰው በትዳር ውስጥ ሊያገኘው የሚችለውን ዓይነት ሳይሆን ተገቢ ወዳልሆነ ድርጊት ሊመራ የሚችለውን ስሜት ያመለክታል) ካሉ ነገሮች እንድንርቅ ጭምር ነው።

 ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ፦

  •   እርቃንን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን መላክ “ርኩሰት” የሆነው እንዴት ነው?

  •   ተገቢ ያልሆነን “የፆታ ምኞት” የሚያቀጣጥለውስ እንዴት ነው?

  •   እርቃንን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን የመመልከት ወይም የማሰራጨት ፍላጎት “መጥፎ” የሆነው ለምንድን ነው?

 እንዲያውም የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሴክስቲንግ መጥፎ የሆነበትን ሌላ አሳማኝ ምክንያት ይገልጻሉ።

  •   “ራስህን ተቀባይነት እንዳለውና ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ አድርገህ በአምላክ ፊት ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።”​—2 ጢሞቴዎስ 2:15

  •    “ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል!”​—2 ጴጥሮስ 3:11

 እነዚህ ጥቅሶች መልካም ሥነ ምግባር ያለውን ጥቅም ያሳያሉ። ጥሩ ሥነ ምግባር ካለሽ ዛሬ የምታደርጊያቸው ነገሮች ነገ የምትቆጪባቸው አይሆኑም።​—ገላትያ 6:7

 ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ፦

  •    ምን ዓይነት ሰው ነኝ?

  •    የሌሎችን ስም ላለማጥፋት እጠነቀቃለሁ?

  •    ሌሎችን በሚጎዳ ነገር ለመዝናናት መፈለግ ተገቢ ነው?

  •    ሴክስቲንግ በሌሎች ዘንድ ያተረፍኩትን ስም የሚነካው እንዴት ነው?

  •    ሴክስቲንግ ወላጆቼ በእኔ ላይ ያላቸውን እምነት የሚነካው እንዴት ነው?

 እውነተኛ ታሪክ “አንድ ጓደኛዬ፣ ከአንድ ወንድ ጋር በሚስጥር የፍቅር ጓደኝነት መሥርታ ነበር። አንድ ቀን፣ እርቃኗን የተነሳችውን ፎቶ ላከችለት፤ እሱም የራሱን ፎቶ ላከላት። ይህ ከሆነ 48 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አባቷ ስልኳን ከፍቶ ተመለከተ። የተላላከቻቸውን ነገሮች ሲያይ በጣም አዘነ። ስለ ጉዳዩ ሲጠይቃት ሁሉንም ነገር አመነች። ልጅቷ ባደረገችው ነገር ተጸጽታለች፤ ያም ቢሆን ወላጆቿ በሁኔታው እጅግ ከመደንገጣቸውም ሌላ በጣም ተበሳጭተው ነበር! ከዚያ በኋላ በእሷ ላይ እምነት መጣል አቃታቸው!”

 የሕይወት እውነታ፦ ሴክስቲንግ ላኪውንም ሆነ ተቀባዩን የሚያዋርድ ተግባር ነው። የወንድ ጓደኛዋ፣ እርቃን የሚያሳይ ፎቶግራፍ እንድትልክለት ጫና ያደርግባት የነበረች አንዲት ወጣት “ራሴን እንድጠላውና እንድጸየፈው አድርጎኛል” ብላለች።

 ሴክስቲንግ ከሥነ ምግባር አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከሕግ አንጻር መዘዝ ያስከትላል፤ በመሆኑም የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ተግባራዊ ማድረጋችን ተገቢ ነው፦

  •   “ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ምኞቶች ሽሽ።”​—2 ጢሞቴዎስ 2:22

  •   “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ።”​—መዝሙር 119:37

 አንቺ ብትሆኚ ምን ታደርጊያለሽ?

 የሚከተለው ሁኔታ ቢያጋጥምሽ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ የምታደርጊው እንዴት ነው? እስቲ ጃኔት የተናገረችውን ነገር አንብቢ፤ የተሻለ የሚሆነው የትኛው አማራጭ ነው?

 “አንድ ቀን ከአንድ ልጅ ጋር ተዋወቅንና ስልክ ተለዋወጥን። ከሳምንት በኋላ በዋና ልብስ የተነሳሁትን ፎቶ እንድልክለት ጠየቀኝ።”​—ጃኔት

 ጃኔት ምን ማድረግ ይኖርባታል? አንቺ ብትሆኚ ምን ታደርጊያለሽ?

  •  አማራጭ ሀ እንዲህ ብለሽ ልታስቢ ትችያለሽ፦ ‘ምን ችግር አለው? መዋኛ ቦታ ብንሄድ የዋና ልብስ ለብሼ ማየቱ አይቀርም።’

  •  አማራጭ ለ እንዲህ ብለሽ ልታስቢ ትችያለሽ፦ ‘ይሄ ልጅ ምን እንደፈለገ እርግጠኛ አይደለሁም፤ ሰውነቴን ያን ያህል የማያጋልጥ ፎቶ ልላክለትና ከዚያ የሚሆነውን አያለሁ።’

  •  አማራጭ ሐ እንዲህ ብለሽ ልታስቢ ትችያለሽ፦ ‘ይሄ ልጅ ከእኔ የሚፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው። እንዲያውም መልእክቱን ላጠፋው ይገባል።’

 ከሁሉም የተሻለው አማራጭ ሐ ነው፤ አይደለም እንዴ? መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን እንዲህ ይላል፦ “ብልኅ ሰው መከራ ሲመጣ አይቶ ይሸሻል፤ ማስተዋል የጐደለው ሰው ግን ሰተት ብሎ ወደ መከራ ከገባ በኋላ እንደገና ይጸጸታል።”​—ምሳሌ 22:3 የ1980 ትርጉም

 ከላይ ያለው ሁኔታ ሴክስቲንግን ጨምሮ ሥነ ምግባርን የሚያበላሹ ሌሎች ድርጊቶች መንስኤ አብዛኛውን ጊዜ ምን እንደሆነ ይጠቁማል፤ ይህም በጓደኛ ምርጫ ረገድ ጠንቃቃ አለመሆን ነው። (ምሳሌ 13:20) ሣራ የተባለች ወጣት “መጥፎ ምግባርን ችላ ብለው ከማያልፉ ሰዎች ጋር ጓደኝነት መሥርቱ” ብላለች። ዲሊያ የተባለች ወጣትም በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጓደኛ ተብዬዎች የሥነ ምግባር አቋማችሁን ከመገንባት ይልቅ ያፈርሱታል። ምግባራቸው ከአምላክ ሕጎች ጋር የሚጻረር ከሆነ እናንተም የሥነ ምግባር አቋማችሁን እንድታፈርሱ ያደርጓችኋል። ታዲያ ይህ እንዲደርስባችሁ ትፈልጋላችሁ?”