በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ኤሌክትሮኒክ ጌሞችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ኤሌክትሮኒክ ጌሞችን በተመለከተ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

 ኤሌክትሮኒክ ጌም—ጥያቄዎች

 የኤሌክትሮኒክ ጌም ኢንዱስትሪው ብዙ ቢሊዮን ዶላር ገቢ በሚያገኝበት በዩናይትድ ስቴትስ . . .

  1.   ኤሌክትሮኒክ ጌም የሚጫወቱ ሰዎች ዕድሜ በአማካይ ስንት ነው?

    1.  ሀ. 18

    2.  ለ. 30

  2.   ኤሌክትሮኒክ ጌም ከሚጫወቱት መካከል ምን ያህሉ ወንዶች፣ ምን ያህሉ ደግሞ ሴቶች ናቸው?

    1.  ሀ. 55 በመቶ ወንዶች እና 45 በመቶ ሴቶች

    2.  ለ. 15 በመቶ ወንዶች እና 85 በመቶ ሴቶች

  3.   ዕድሜያቸው ከታች ከተገለጹት ሁለት ቡድኖች መካከል ኤሌክትሮኒክ ጌም በመጫወት አብላጫውን ቁጥር የያዙት የትኞቹ ናቸው?

    1.  ሀ. ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሴቶች

    2.  ለ. ዕድሜያቸው 17 እና ከዚያ በታች የሆኑ ወንዶች

 መልስ (በ2013 በተካሄደው ጥናት መሠረት)፦

  1.   ለ. 30

  2.   ሀ. ግማሽ አካባቢ ይኸውም 45 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው

  3.   ሀ. ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሴቶች 31 በመቶ ይሆናሉ፤ ዕድሜያቸው 17 እና ከዚያ በታች የሆኑ ወንዶች ግን 19 በመቶ ናቸው፥

 ይህ ጥናት የኤሌክትሮኒክ ጌም የሚጫወቱት እነማን እንደሆኑ አጠቃላይ መረጃ ይሰጣል። ይሁንና ጥናቱ፣ የኤሌክትሮኒክ ጌሞች በአንድ ሰው ላይ የሚያስከትሉትን ጠቃሚና ጎጂ ተጽዕኖ ሊያሳይህ አይችልም።

 ጥቅሙ

 ከዚህ ቀጥሎ ስለ ኤሌክትሮኒክ ጌሞች ከቀረቡት አስተያየቶች መካከል በየትኛው ትስማማለህ?

  •  “ከቤተሰብና ከጓደኞች ጋር ለመቀራረብ የሚረዱ መዝናኛዎች ናቸው።”—አይሪን

  •  “ከገሃዱ ዓለም ለመሸሽ ጥሩ መፍትሔ ናቸው።”—አኔት

  •  “ፈጣን እርምጃ የመውሰድ ችሎታን ያሻሽላሉ።”—ክሪስቶፈር

  •  “መፍትሔ የመፈለግ ችሎታን ያሳድጋሉ።”—ኤሚ

  •  “አእምሮን ያሠራሉ፤ እንድታስብ፣ እንድታቅድና መላ እንድትፈልግ ያደርጉሃል።”—አንቶኒ

  •  “አንዳንድ ጌሞች ከጓደኞችህ ጋር በቡድን የመሥራት ልማድን ያበረታታሉ።”—ቶማስ

  •  “አንዳንድ ጌሞች አካላዊ እንቅስቃሴ እንድታደርግ ስለሚጠይቁ ውፍረት ለመቆጣጠር ያስችላሉ።”—ጃኤል

 ከእነዚህ አስተያየቶች በአንዳንዶቹ ምናልባትም በሁሉም ትስማማለህ? ቪዲዮ ጌሞች ለአእምሮና ለሰውነት ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ አንዳንዶቹ ጌሞች እንዲሁ ጊዜ ማሳለፊያ ናቸው፤ ያም ቢሆን አኔት እንዳለችው አንዳንድ ጊዜ “ከገሃዱ ዓለም ለመሸሽ” መፈለግ ሁልጊዜ ስህተት አይደለም።

 ● መጽሐፍ ቅዱስ “ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው” ይላል፤ ይህም መዝናኛንም ይጨምራል።—መክብብ 3:1-4

 ጉዳቱ

 የኤሌክትሮኒክ ጌሞች ጊዜህን እየወሰዱብህ ነው?

 “አንዴ መጫወት ከጀመርኩ ማቆም ይከብደኛል። ‘ቆይ ይህቺን ደረጃ ልለፍና አቆማለሁ’ እያልኩ መጫወቴን እቀጥላለሁ። ከዚያም ሳይታወቀኝ እዚያው ቁጭ ብዬ ሰዓታት ያልፋሉ!”—አኔት

 “ቪዲዮ ጌሞች ጊዜን ሙጥጥ አድርገው ይወስዳሉ። ለሰዓታት ቁጭ ብለህ በመጫወት አምስት ጊዜ ስታሸንፍ የሆነ ጀብዱ እንደፈጸምክ ይሰማሃል፤ ወደ እውኑ ዓለም ስትመለስ ግን ምንም ያከናወንከው ነገር የለም።”—ሰሪና

 ዋናው ነጥብ፦ ገንዘብ ብታጣ መልሰህ ልታገኝ ትችል ይሆናል። ጊዜ ግን አንዴ ከጠፋ ተመልሶ ሊገኝ አይችልም። በሌላ አባባል ጊዜ ከገንዘብ ይበልጥ ውድ የሆነ ነገር ነው። ስለዚህ ጊዜህ እንዳይወሰድብህ ተጠንቀቅ!

 ● መጽሐፍ ቅዱስ “ጊዜ ለራሳችሁ በመግዛት . . . በጥበብ መመላለሳችሁን ቀጥሉ” ይላል።—ቆላስይስ 4:5

 የኤሌክትሮኒክ ጌሞች በአስተሳሰብህ ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው?

 “አንድ ሰው የቪዲዮ ጌም ሲጫወት በእውኑ ዓለም ቢሆን ኖሮ በእስራት ወይም በሞት ሊያስቀጡ የሚችሉ ወንጀሎችን ያለምንም ማመንታት ይፈጽማል።”—ሴት

 “በብዙ ጌሞች ላይ የምትፈልገው ግብ ላይ ለመድረስ ጠላቶችህን ድል ማድረግ አለብህ። ይህም አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ የጭካኔ መንገዶች ጠላቶችህን መግደልን ይጠይቃል።”—አኔት

 “አንዳንድ ጊዜ ጌም ስትጫወት በጣም የሚያስደነግጡ ነገሮችን ለጓደኞችህ ልትናገር ትችላለህ፤ ለምሳሌ ‘ድብን በል!’ ወይም ‘እጨርስሃለሁ!’ ትል ይሆናል።”—ናታን

 ዋናው ነጥብ፦ አምላክ የሚጠላቸውን ነገሮች ለምሳሌ ዓመፅን፣ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ የፆታ ግንኙነትን እና መናፍስታዊ ድርጊቶችን እንድትፈጽም የሚያበረታቱ ጌሞችን አትጫወት።—ገላትያ 5:19-21፤ ኤፌሶን 5:10፤ 1 ዮሐንስ 2:15, 16

 ● ይሖዋ ዓመፅን የሚያደርጉትን ብቻ ሳይሆን ዓመፅን “የሚወዱትን” ጭምር ‘እንደሚጠላ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መዝሙር 11:5) የምትጫወታቸው ኤሌክትሮኒክ ጌሞች ወደፊት ምን ዓይነት ሰው እንደምትሆን አይገልጹ ይሆናል፤ አሁን ምን ዓይነት ሰው እንደሆንክ ግን በተወሰነ መጠን ሊጠቁሙ ይችላሉ።

 ሊታሰብበት የሚገባው ነገር፦ ጌቲንግ ቱ ካልም የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “ዓመፅ የሚታይባቸው ቪዲዮ ጌሞች ከቴሌቪዥን የበለጠ በባሕርይ ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል ያላቸው ይመስላል፤ ምክንያቱም ልጆች በጌሙ ላይ ጨካኝና ደም አፍሳሽ የሆነውን ጀግና መመልከት ብቻ ሳይሆን እሱን ሆነው ይጫወታሉ። ጌሞች ልክ እንደ አንድ አስተማሪ ትምህርት ያስተላልፋሉ፤ ከዚህ አንጻር የዓመጽ ትምህርት እየሰጡ ነው ሊባል ይችላል።”—ከኢሳይያስ 2:4 ጋር አወዳድር።

 በእውን ባለው ሕይወት ላይ ማተኮር

 ብዙ ወጣቶች በኤሌክትሮኒክ ጌም አጠቃቀማቸው ረገድ ሚዛናዊ መሆንን ተምረዋል። እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን ተመልከት።

 “የቪዲዮ ጌሞችን እየተጫወትኩ በጣም አመሽ ነበር፤ ‘ለአምስት ሰዓት ያህል ከተኛሁ እኮ በቂ ነው! አንድ ደረጃ ብቻ እስካልፍ ልጫወትና እተኛለሁ’ እያልኩ ለራሴ ሰበብ አቀርባለሁ። አሁን ግን ከቪዲዮ ጌሞች ጋር በተያያዘ ከመጠን ማለፍ እንደሌለብኝ ተምሬያለሁ። ጌሞች አልፎ አልፎ ጥሩ የጊዜ ማሳለፊያ ሊሆኑ ይችላሉ። ያም ቢሆን ሁሉም ነገር በልኩ መደረግ አለበት።”—ጆሴፍ

 “ጌም የምጫወትበትን ጊዜ ስለቀነስኩ ሌሎች ብዙ ሥራዎችን ማከናወን ችያለሁ! አገልግሎቴን ማሻሻል፣ በጉባኤዬ ውስጥ ያሉትን ሰዎች መርዳት አልፎ ተርፎም አንድ የሙዚቃ መሣሪያ መማር ችያለሁ። ከጌም ውጭ ሌላ ሕይወት አለ!”—ዴቪድ

 ● ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በሳል ከሆኑ “በልማዶቻቸው ልከኞች” እንደሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 11) እንዲህ ያሉ ሰዎች በመዝናናት ጥሩ ጊዜ ያሳልፋሉ፤ ሆኖም መቼ ማቆም እንዳለባቸው ያውቃሉ፤ ደግሞም እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል ራስን የመግዛት ባሕርይ አላቸው።—ኤፌሶን 5:10

 ዋናው ነጥብ፦ ኤሌክትሮኒክ ጌሞችን መጫወት መጠኑን እስካላለፈ ድረስ ጥሩ መዝናኛ ሊሆን ይችላል። ይሁንና እነዚህ ጌሞች ጊዜህን እንዲወስዱብህ ወይም በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዳታተኩር እንዲያደርጉህ አትፍቀድ። በጌም ውስጥ የተቀመጠው ግብ ላይ ለመድረስ የምታደርገውን ጥረት በእውኑ ዓለም ባሉ ግቦችህ ላይ ለመድረስ ብትጠቀምበት የተሻለ አይሆንም?