በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ሰዎች ስለ እኔ የሚያወሩት ለምንድን ነው?

ሰዎች ስለ እኔ የሚያወሩት ለምንድን ነው?

 ጎጂ የሆነው ለምንድን ነው?

 አንዳንድ ጊዜ ሐሜት ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፤ ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች ሆን ብለው ውሸት በመናገር ስምህን ለማጥፋት ይሞክሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ የተወራብህ ነገር ያን ያህል መጥፎ ባይሆንም እንኳ ስሜትህን ሊጎዳው ይችላል፤ በተለይም ግለሰቡ የቅርብህ ሰው ከሆነ ልትጎዳ ትችላለህ።​—መዝሙር 55:12-14

 “አንድ ጓደኛዬ ‘ለሰዎች ግድ የላትም’ ብላ እንዳስወራችብኝ አወቅሁ። በወቅቱ በጣም ተሰምቶኝ ነበር! እንዲህ ያለ ወሬ ያስወራችብኝ ለምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም።”​—አሽሊ

 እውነታው፦ ሐሜቱን ያሰራጨው ሰው የቅርብ ጓደኛህ ሆነም አልሆነ ስለ አንተ መጥፎ ወሬ መወራቱን ስትሰማ እንደማትደሰት የታወቀ ነው።

 የሚያሳዝነው ነገር​—ሰዎች ስለ አንተ እንዳያወሩ ማድረግ አትችልም

 ሰዎች፣ ስለ ሌሎች እንዲያወሩ የሚያደርጓቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

 በቅንነት ተነሳስተው። የሰው ልጆች በተፈጥሯቸው እርስ በርሳቸው መጨዋወት ይወዳሉ። በመሆኑም ስለ ራሳችንም ሆነ ስለ ሌሎች ማውራታችን የተለመደ ነገር ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ለሌሎች ሰዎች ጉዳይ” በተወሰነ መጠን ትኩረት እንድንሰጥ ያበረታታናል።​—ፊልጵስዩስ 2:4

 “ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ስለ ሌሎች ሰዎች ማውራት ያስደስታቸዋል!”​—ቢያንካ

 “ስለ ሌሎች ሰዎች ማወቅ እና ስለ እነሱ ማውራት እንደሚያስደስተኝ አልክድም። ለምን እንደሆነ ባላውቅም ደስ ይለኛል።”​—ኬቲ

 ሥራ መፍታት። በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች “ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት ብቻ” እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 17:21) ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

 “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች፣ በዙሪያቸው አዲስ ነገር ካልተፈጠረ ወሬ ፈጥረው ስለ ሌሎች ያወራሉ።”​—ጆአና

 በራስ አለመተማመን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ራሳችንን ከሌሎች ጋር እንዳናወዳድር ማስጠንቀቁ ተገቢ ነው። (ገላትያ 6:4) የሚያሳዝነው፣ አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው ስለማይተማመኑና ለራሳቸው ያላቸው ግምት ከፍ እንደሚል ስለሚሰማቸው ሌሎችን ያማሉ።

 “አንድ ሰው ሐሜተኛ መሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ስለ እሱ የሚያሳየው ነገር አለ። ብዙውን ጊዜ ይህ ሰው፣ የሚያማውን ግለሰብ እንደሚቀናበት ይጠቁማል። ሐሜተኛ ሰዎች አሉባልታ የሚያሰራጩት ስለ ራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ነው፤ በሌላ አባባል እንዲህ በማድረግ ከዚያ ግለሰብ የተሻሉ እንደሆኑ ራሳቸውን ያሳምናሉ።”​—ፊል

 እውነታው፦ ወደድክም ጠላህ ሰዎች ስለ ሰዎች ማውራታቸው አይቀርም፤ ይህ ደግሞ አንተንም ይጨምራል።

 ደስ የሚለው ነገር​—ሁኔታው አንተን እንዳይቆጣጠርህ ማድረግ ትችላለህ

 ሰዎች ጨርሶ ስለ አንተ እንዳያወሩ ማድረግ አትችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ለዚህ የምትሰጠው ምላሽ በአንተ ላይ የተመካ ነው። ስለ አንተ እየተወራ እንደሆነ ካወቅህ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ትችላለህ።

 አማራጭ 1፦ ችላ ብሎ ማለፍ። አብዛኛውን ጊዜ የተሻለው አማራጭ ችላ ብሎ ማለፍ ነው፤ በተለይም የተወራው ነገር ያን ያህል ከባድ ካልሆነ እንዲህ ማድረጉ የተሻለ ነው። የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርግ፦ “በመንፈስህ ለቍጣ አትቸኵል።”​—መክብብ 7:9

 “አንድ ልጅ ፍቅረኛዬ እንደሆነ ይወራብኝ ጀመር፤ ልጁን አግኝቼው እንኳ አላውቅም! ነገሩ ጨርሶ የማይመስል ስለነበር ችላ ብዬ አለፍኩት።”​—ኤሊዝ

 “ሐሜትን ለመዋጋት ከሁሉ የተሻለው መሣሪያ ጥሩ ስም ማትረፍ ነው። ጥሩ ስም ካለህ፣ መጥፎ ነገር ቢወራብህ እንኳ ወሬውን ብዙ ሰው አያምነውም። እውነት ማሸነፉ አይቀርም።”​—አሊሰን

 ጠቃሚ ምክር፦ (1) ስለ አንተ የተወራውን ነገር እና (2) ወሬው ምን ስሜት እንደፈጠረብህ ጻፍ። ሁኔታውን ‘በልብህ ካሰብህበት’ በኋላ ችላ ብሎ ማለፍ ቀላል ሊሆንልህ ይችላል።​መዝሙር 4:4 የ1954 ትርጉም

 አማራጭ 2፦ ወሬውን ያስወራብህን ሰው ቀርበህ አነጋግረው። አንዳንድ ጊዜ፣ ወሬው በጣም ጎጂ ከመሆኑ የተነሳ ያስወራብህን ሰው ማነጋገር ሊያስፈልግህ ይችላል።

 “መጥፎ ነገር ያስወሩብህን ሰዎች ቀርበህ ካነጋገርካቸው፣ ሐሜት ዞሮ ዞሮ የባለቤቱ ጆሮ መድረሱ እንደማይቀር እያስተማርካቸው ነው። በተጨማሪም በመካከላችሁ የተፈጠረውን ችግር መፍታትና ሐሜቱን ካሰራጨው ግለሰብ ጋር ያለህን ግንኙነት ማደስ ትችል ይሆናል።”​—ኤሊስ

 መጥፎ ነገር ያስወራብህን ሰው ቀርበህ ከማነጋገርህ በፊት የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች አስብባቸው፤ እንዲሁም ከጥቅሶቹ ሥር ያሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ።

  •   “ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስ፣ ቂልነት . . . ይሆንበታል።” (ምሳሌ 18:13) ‘ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ አለኝ? መጥፎ ነገር እንደተወራብኝ የነገረኝ ሰው፣ የሰማውን ነገር በተሳሳተ መንገድ ተረድቶት ይሆን?’

  •   “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።” (ያዕቆብ 1:19) ‘መጥፎ ነገር ያስወራብኝን ሰው ለማነጋገር ጊዜው አመቺ ነው? ስለ ጉዳዩ ስሜታዊ ሳልሆን መናገር እችላለሁ? ወይስ ስሜቴ እስኪረጋጋ ድረስ ጥቂት ጊዜ መጠበቅ ይኖርብኛል?’

  •   “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል።” (ማቴዎስ 7:12) ‘ሐሜቱን ያሰራጨሁት እኔ ብሆን ኖሮ ባለቤቱ እንዴት ቢያነጋግረኝ ደስ ይለኛል? ስለ ጉዳዩ የት ቢያናግረኝ እመርጣለሁ? የተሻለ ውጤት የሚያስገኘው የትኞቹን ቃላት ወይም ምን ዓይነት አቀራረብ መጠቀም ነው?’

 ጠቃሚ ምክር፦ ሐሜት ያሰራጨብህን ሰው ቀርበህ ከማነጋገርህ በፊት ምን እንደምትለው ጻፍ። ከዚያም ከአንድ ወይም ከሁለት ሳምንት በኋላ የጻፍከውን ነገር መልሰህ አንብበው፤ በጻፍከው ነገር ላይ ለውጥ ማድረግ የሚያስፈልግ ነገር ይኖር እንደሆነ ተመልከት። በተጨማሪም ለማድረግ ያሰብከውን ከወላጆችህ ወይም ብስለት ካለው አንድ ጓደኛህ ጋር ተወያይበት፤ እንዲሁም ምክር እንዲሰጥህ ጠይቀው።

 እውነታው፦ በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ ሁልጊዜ ልትቆጣጠራቸው ከማትችላቸው ነገሮች አንዱ ሐሜት ነው። ይሁን እንጂ አንተን እንዳይቆጣጠርህ ማድረግ ትችላለህ!