በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ጓደኛዬ ቢበድለኝ ምን ላድርግ?

ጓደኛዬ ቢበድለኝ ምን ላድርግ?

 ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

  •   ሁሉም ጓደኛሞች ችግር ያጋጥማቸዋል። ጥሩ የሆነ ጓደኛህ ሌላው ቀርቶ በጣም የምትቀርበው ጓደኛህ እንኳ ፍጹም ስላልሆነ አንተን የሚጎዳ ነገር ሊናገር አሊያም ሊያደርግ ይችላል። አንተም ብትሆን ፍጹም እንዳልሆንክ የታወቀ ነው። በዚህ ምክንያት የሆነ ሰውን የጎዳህበትን ጊዜ አታስታውስም?—ያዕቆብ 3:2

  •   ኢንተርኔት በቀላሉ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ዴቪድ የተናገረውን እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ እንዲህ ብሏል፦ “ኢንተርኔት ስትጠቀም፣ ጓደኛህ በአንድ ግብዣ ላይ ከሌሎች ጋር አብሮ ጊዜ ሲያሳልፍ የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ ትመለከታለህ፤ በዚህ ጊዜ ‘እንዴት እኔ አልተጠራሁም?’ ብለህ ታስባለህ። ከዚያም ጓደኛህ እንደማይወድህ በማሰብ ታዝናለህ።”

  •   ችግሩን በተሻለ መንገድ መፍታት ትችላለህ።

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

 ራስህን መርምር። መጽሐፍ ቅዱስ “ቁጣ የሞኝ ሰው መለያ ስለሆነ ለቁጣ አትቸኩል” ይላል።—መክብብ 7:9 የግርጌ ማስታወሻ

 “አንዳንድ ጊዜ፣ አናዶህ የነበረው ነገር ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልነበረ ከጊዜ በኋላ ትገነዘባለህ።”—አሊሳ

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ በቀላሉ ትከፋለህ? ሌሎች የሚሠሩትን ስህተት ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በማየት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆን?—መክብብ 7:21, 22

 ይቅር ባይ መሆን ያለውን ጥቅም አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በደልን መተው ውበት ያጎናጽፋል’ ይላል።—ምሳሌ 19:11

 “ቅር ለመሰኘት የሚያበቃ ምክንያት እንዳለህ ቢሰማህ እንኳ በነፃ ይቅር ማለትህ ጠቃሚ ነው፤ ይህም ጓደኛህ ያደረሰብህን በደል ዳግም አለማንሳትን እንዲሁም ስለ ጉዳዩ በተነሳ ቁጥር ይቅርታ እንዲጠይቅህ አለመጠበቅን ይጨምራል። አንዴ ይቅርታ ካደረግክ በኋላ ስለ ጉዳዩ ዳግመኛ አታንሳ።—ማለሪ

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ጉዳዩ ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው? ሰላም ለመፍጠር ስትል ጉዳዩን በይቅርታ ማለፍ ትችል ይሆን?

በጓደኛሞች መካከል የሚፈጠረውን እያንዳንዱ ችግር አንስቶ መወያየት አንድን በር ደጋግሞ እየከፈቱ ሙቀት ወዳለበት ክፍል ቀዝቃዛ አየር እንደማስገባት ነው።

 ስለ ጓደኛህ አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ” በማለት ይናገራል።—ፊልጵስዩስ 2:4

 በአንተና በጓደኛህ መካከል ፍቅርና አክብሮት ካለ በመካከላችሁ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የሚያስችል በቂ ምክንያት አለህ፤ ምክንያቱም ጓደኝነታችሁ እንዲጠናከር አንተም የበኩልህን አስተዋጽኦ አድርገሃል። ጓደኝነታችሁ እንዲጠናከር ያደረከው ጥረት መና እንዲቀር እንደማትፈልግ ግልጽ ነው።—ኒኮል

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ጓደኛህ ይህን ያደረገበት አጥጋቢ ምክንያት ይኖረው ይሆን?—ፊልጵስዩስ 2:3

 ዋናው ነጥብ፦ ሌሎች ሲበድሉህ የሚያድርብህን ስሜት መቋቋም አዋቂ ስትሆንም የሚጠቅምህ ችሎታ ነው። ታዲያ ይህንን ችሎታ ከአሁኑ ለምን አትማርም?