የያዕቆብ ደብዳቤ 3:1-18

  • ምላስን መግራት (1-12)

    • “ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ” (1)

  • “ከሰማይ የሆነው ጥበብ” (13-18)

3  ወንድሞቼ ሆይ፣ ከእናንተ መካከል ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛ የባሰ ፍርድ እንደምንቀበል* ታውቃላችሁ።+  ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለንና።*+ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው መላ ሰውነቱንም መቆጣጠር* የሚችል ፍጹም ሰው ነው።  ፈረሶች እንዲታዘዙልን አፋቸው ውስጥ ልጓም ካስገባን መላ ሰውነታቸውንም መምራት እንችላለን።  መርከቦችንም ተመልከቱ፦ በጣም ትልቅና በኃይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ሁሉ ይመራቸዋል።  ልክ እንደዚሁም ምላስ ትንሽ የአካል ክፍል ሆና ሳለ ጉራዋን ትነዛለች። በጣም ሰፊ የሆነን ጫካ በእሳት ለማያያዝ ትንሽ እሳት ብቻ ይበቃል!  ምላስም እሳት ናት።+ ምላስ በአካል ክፍሎቻችን መካከል የክፋትን ዓለም ትወክላለች፤ መላ ሰውነትን ታረክሳለችና፤+ እንዲሁም መላውን የሕይወት ጎዳና* ታቃጥላለች፤ እሷም በገሃነም* ትቃጠላለች።  ማንኛውም ዓይነት የዱር እንስሳ፣ ወፍ፣ በምድር ላይ የሚሳብ ፍጥረትና በባሕር ውስጥ የሚኖር ፍጥረት በሰዎች ሊገራ ይችላል፤ ደግሞም ተገርቷል።  ምላስን ግን ሊገራ የሚችል አንድም ሰው የለም። ምላስ ገዳይ መርዝ የሞላባት፣ ለመቆጣጠር የምታስቸግር ጎጂ ነገር ናት።+  በምላሳችን አባት የሆነውን ይሖዋን* እናወድሳለን፤ ይሁንና በዚህችው ምላሳችን “በአምላክ አምሳል” የተፈጠሩትን ሰዎች+ እንረግማለን። 10  ከአንድ አፍ በረከትና እርግማን ይወጣሉ። ወንድሞቼ፣ ይህ መሆኑ ተገቢ አይደለም።+ 11  አንድ ምንጭ ከዚያው ጉድጓድ ጣፋጭና መራራ ውኃ ያፈልቃል? 12  ወንድሞቼ፣ የበለስ ዛፍ ወይራን ወይም ደግሞ የወይን ተክል በለስን ሊያፈራ ይችላል?+ ከጨዋማ ውኃም ጣፋጭ ውኃ ሊገኝ አይችልም። 13  ከእናንተ መካከል ጥበበኛና አስተዋይ ሰው ማን ነው? ሥራውን የሚያከናውነው ከጥበብ በመነጨ ገርነት* መሆኑን በመልካም ምግባሩ ያሳይ። 14  ሆኖም በልባችሁ ውስጥ መራራ ቅናትና+ ጠበኝነት*+ ካለ አትኩራሩ፤+ እንዲሁም በእውነት ላይ አትዋሹ። 15  ይህ ከሰማይ የሚመጣ ጥበብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምድራዊ፣+ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው። 16  ቅናትና ጠበኝነት* ባለበት ሁሉ ብጥብጥና መጥፎ ነገሮችም ይኖራሉ።+ 17  ከሰማይ የሆነው ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጹሕ+ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣+ ምክንያታዊ፣+ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት+ እንዲሁም አድልዎና+ ግብዝነት የሌለበት+ ነው። 18  ከዚህም በላይ የጽድቅ ፍሬ ሰላም ፈጣሪ ለሆኑ ሰዎች*+ ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች+ ይዘራል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ፍርዱ እኛ ላይ እንደሚጠብቅ።”
ወይም “እንሳሳታለንና።”
ወይም “ለመላ ሰውነቱ ልጓም ማስገባት።”
ወይም “ተፈጥሯዊውን የሕይወት እሽክርክሪት።” ቃል በቃል “የመወለድን እሽክርክሪት።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሸካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
“የራስ ወዳድነት ምኞት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“የራስ ወዳድነት ምኞት” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“ሰላም ፈጣሪ በሆኑ ሰዎች” ማለትም ሊሆን ይችላል።