በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ስለ ፆታ ግንኙነት ማሰቤን ማቆም የምችለው እንዴት ነው?

ስለ ፆታ ግንኙነት ማሰቤን ማቆም የምችለው እንዴት ነው?

 “ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ሐሳብ በድንገት ይመጣብኝና ስለ ሌላ ነገር ማሰብ ያቅተኛል። ሌላ ሰው አእምሮዬን የሚቆጣጠረው ያህል ሆኖ ነው የሚሰማኝ።”—ቬራ

 “ስለ ፆታ ግንኙነት ማውጠንጠኔን ማቆም የምችል አይመስለኝም። ክንፍ አውጥቶ መብረር ራሱ ከዚህ የሚቀል ይመስለኛል።”—ጆን

 እንደ ቬራ ወይም እንደ ጆን ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ይህ ርዕስ ሊረዳህ ይችላል።

 አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው?

 “አጎቴ ‘የፆታ ግንኙነት መፈጸም ተገቢ ባይሆን ኖሮ አምላክ ይህ ፍላጎት እንዲኖርህ አድርጎ አይፈጥርህም ነበር’ ይል ነበር” በማለት አሌክስ የተባለ ወጣት ተናግሯል።

 የአሌክስ አጎት የተናገረው ነገር በከፊል እውነት ነው፤ የፆታ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ የፈጠረን አምላክ ነው፤ ይህን ያደረገበትም በቂ ምክንያት አለው። መዋለድ ባይኖር ኖሮ ዛሬ የሰው ዘር በምድር ላይ አይኖርም ነበር። ታዲያ ስለ ፆታ ግንኙነት ማሰብህን የማቆሙ ጉዳይ ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው? ሁለት ምክንያቶችን እንመልከት።

  •   መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አምላክ የፆታ ግንኙነት እንዲፈጸም የሚፈቅደው በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል ብቻ ነው።—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:24

     አምላክ ያወጣውን መሥፈርት የሚያከብር ያላገባ ወጣት ከሆንክ ስለ ፆታ ግንኙነት ማውጠንጠንህ ምንም የሚፈይድልህ ነገር የለም፤ እንዲያውም ምኞትህን ማሳካት ባለመቻልህ ለሐዘን ትዳረጋለህ። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ በተጽዕኖ ተሸንፈህ የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽም ሊያደርግህ ይችላል፤ ብዙዎች እንዲህ በማድረጋቸው የኋላ ኋላ ተቆጭተዋል።

  •   ስለ ፆታ ግንኙነት ማውጠንጠንህን ለማቆም መማርህ ራስን መግዛትን እንድታዳብር ይረዳሃል፤ ይህ ባሕርይ ደግሞ በሌሎች የሕይወትህ ዘርፎችም ይጠቅምሃል።—1 ቆሮንቶስ 9:25

 ራስን መግዛት በአሁኑ ጊዜም ሆነ ወደፊት ስኬታማ ሕይወት ለመምራት የሚረዳህ አስፈላጊ ባሕርይ ነው። እንዲያውም አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ራሳቸውን የሚገዙ ልጆች፣ ትልቅ ሲሆኑ በሕመም የመያዛቸው፣ በገንዘብ ችግር ውስጥ የመግባታቸው እንዲሁም ሕግ የመጣሳቸው አጋጣሚ ጠባብ ነው። a

 ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?

 የምንኖርበት ዓለም ሁልጊዜ ስለ ፆታ ግንኙነት በሚያወሩና በሚያስቡ ሰዎች የተሞላ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሆርሞኖችህም ስለ ፆታ ግንኙነት ማሰብህን ማቆም ከባድ እንዲሆንብህ ሊያደርጉ ይችላሉ።

 “ሁሉም የቴሌቪዥን ድራማዎች ማለት ይቻላል ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ጥሩ እንደሆነና ምንም ጉዳት እንደሌለው አድርገው ያቀርባሉ። ተገቢ ያልሆነ የፆታ ግንኙነት ምንም መዘዝ የሌለው ስለሚመስል እንዲህ ያለውን ነገር ለማውጠንጠን ልንገፋፋ እንችላለን።”—ሩት

 “በሥራ ቦታዬ ያሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ የብልግና ወሬ ያወራሉ፤ ስለዚህ የማወቅ ጉጉት ያድርብኛል። አብዛኞቹ ሰዎች ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸም ምንም ችግር እንደሌለው የሚሰማቸው መሆኑ እኔም ጉዳዩን አቅልዬ እንድመለከተው አድርጎኛል።”—ኒኮል

 “ማኅበራዊ ሚድያ ስንጠቀም ሳናስበው መጥፎ ምስል ልናይ እንችላለን። ያየነው አንድ የብልግና ምስል አእምሯችን ላይ ታትሞ ሊቀርና ጨርሶ አልጠፋ ሊለን ይችላል!”—ማሪያ

 በእነዚህ ነገሮች የተነሳ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሊሰማህ ይችላል። ጳውሎስ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው” በማለት ጽፎ ነበር።—ሮም 7:21

መጥፎ ሐሳቦች ጭንቅላትህ ላይ ጎጆ እንዲሠሩብህ አትፍቀድ

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

 አእምሮህ በሌላ ነገር ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ስለ ፆታ ግንኙነት ሳይሆን ስለ ሌላ ነገር ለማሰብ ሞክር። የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ፣ ስፖርት ወይም ሌሎች እንቅስቃሴዎች አእምሮህ በሌላ ነገር ላይ እንዲያተኩር ሊረዱህ ይችላሉ። ቫለሪ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም ይረዳል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው ሐሳብ ስለ አምላክ የሚገልጽ ነው፤ አእምሯችን እንዲህ ባለው ሐሳብ ከተሞላ ደግሞ ስለ መጥፎ ነገር ለማሰብ አንፈተንም።”

 እርግጥ ነው፣ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ሐሳብ ወደ አእምሮህ ሊመጣብህ ይችላል። ሆኖም ከዚያ በኋላ የምታደርገው ነገር በአንተ ምርጫ ላይ የተመካ ነው። ከፈለግክ እንዲህ ያለውን ሐሳብ ከአእምሮህ ማስወጣት ትችላለህ።

 “ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ሐሳብ ሲመጣብኝ አእምሮዬ ሌላ ነገር ላይ እንዲያተኩር አደርጋለሁ። በተጨማሪም ስለ ፆታ ግንኙነት እንዳስብ ያደረገኝ ምን እንደሆነ ለማወቅ እሞክራለሁ፤ ማጥፋት ያለብኝ ዘፈን ወይም ፎቶ ሊኖር ይችላል።”—ሄለና

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ [እና] ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ . . . ማሰባችሁን አታቋርጡ።”—ፊልጵስዩስ 4:8

 ጥሩ ጓደኞች ምረጥ። ጓደኞችህ ሁልጊዜ ስለ ፆታ ጉዳዮች የሚያወሩ ከሆነ አስተሳሰብህን ንጹሕ ማድረግ ከባድ ይሆንብሃል።

 “በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለሁ አስተሳሰቤን መቆጣጠር በጣም ያስቸግረኝ ነበር፤ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ጓደኞቼ ነበሩ። መጥፎ ምኞቶች ምንም ችግር እንደሌላቸው ከሚያስቡ ሰዎች ጋር ስትሆኑ አስተሳሰባችሁን መቆጣጠር ታቆማላችሁ፤ ያ ደግሞ በእሳት ላይ ነዳጅ እንደመጨመር ነው።”—ሳራ

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል፤ ከሞኞች ጋር የሚገጥም ግን ጉዳት ይደርስበታል።”—ምሳሌ 13:20

 ተገቢ ካልሆነ መዝናኛ ራቅ። የመዝናኛው ኢንዱስትሪ የሚያቀርባቸው አብዛኞቹ ነገሮች በፆታዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ እንደሆኑ አስተውለህ መሆን አለበት። ኒኮል እንዲህ ብላለች፦ “ለእኔ ትልቁ ፈተናዬ ሙዚቃ ነው። ጨርሶ ከቁጥጥሬ ውጭ የሆነ እስኪመስለኝ ድረስ ምኞቴን ይቀሰቅሰዋል።”

 “ፆታዊ ነገሮችን የሚያሳዩ ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን አይ ነበር። ሳይታወቀኝ ስለ ፆታ ግንኙነት ብዙ ማሰብ ጀመርኩ። እንደዚያ ዓይነት አስተሳሰብ ያሳደረብኝ ምን እንደሆነ ለማወቅ አልተቸገርኩም። እነዚያን ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ማየት ሳቆም ሐሳቤን መቆጣጠር ቻልኩ። በመዝናኛ ምርጫ ረገድ ጠንቃቃ መሆን መጥፎ ሐሳቦችን ማስወገድ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል።”—ጆአን

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የፆታ ብልግናና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ።”—ኤፌሶን 5:3

 ዋናው ነጥብ፦ አንዳንድ ሰዎች የፆታ ስሜት ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ እንዲሁም ይህን ስሜት መቆጣጠር እንደማያስፈልግ ብሎም እንደማይቻል ይሰማቸዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ አስተሳሰባችንን መቆጣጠር እንደምንችል ይናገራል፤ ይህም ክብር ያለን ፍጥረታት እንደሆንን ያሳያል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ።”—ኤፌሶን 4:23

a ያገቡ ሰዎችም ራሳቸውን መግዛት ያስፈልጋቸዋል፤ ስለዚህ ሳታገባ በፊት ይህን ባሕርይ ማዳበርህ ይጠቅምሃል።