በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

አለባበሴ እንዴት ነው?

አለባበሴ እንዴት ነው?

 አለባበስህ ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የምትለብሳቸው ልብሶች ስለ አንተ የሚናገሩት ነገር አለ። አለባበስህ ስለ አንተ ምን መልእክት ያስተላልፋል?

 ከአለባበስ ጋር የተያያዙ ሦስት ስህተቶችና እነዚህን ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ

ስህተት #1፦ ሚዲያው በአለባበስህ ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ መፍቀድ።

 ቴሪሳ የተባለች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ፣ አንድን ፋሽን የምወደው ማስታወቂያ ላይ በተደጋጋሚ ስላየሁት ነው። አንድን አለባበስ ብዙ ጊዜ በመመልከትህ ያንን ፋሽን ለመከተል ልትፈተን ትችላለህ።”

 ማስታወቂያ ተጽዕኖ የሚያደርግባቸው ሴቶች ልጆች ብቻ አይደሉም። ዚ ኤቭሪቲንግ ጋይድ ቱ ሬይዚንግ አዶለሰንት ቦይስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ወንዶች ልጆችም በፋሽን በቀላሉ ሊማረኩ ይችላሉ። የንግዱ ዓለም ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ በእነሱ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ይጥራል።”

 የተሻለው አካሄድ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) ከዚህ ምክር ጋር በሚስማማ መልኩ በማስታወቂያዎች ላይ የምታየውን ነገር ቆም ብለህ አስብበት። ለምሳሌ፣ ከአንድ ልብስ ጋር የተያያዙ ማስታወቂያዎችን ስትመለከት ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦

  •  ‘ይህን ፋሽን ብከተል የሚጠቀመው ማን ነው?’

  •  ‘ከምን ዓይነት ሰዎች ጋር ያስመድበኛል?’

  •  ‘ይህ አለባበስ የእኔን እውነተኛ ማንነትና አቋሜን የሚገልጽ ይሆናል?’

 ጠቃሚ ምክር፦ የልብስ ማስታወቂያዎችንና በፋሽን ላይ የሚያተኩሩ ሌሎች ሚዲያዎችን እስቲ ለአንድ ሳምንት ያህል ተከታተል። የሚያበረታቱህ ምን ዓይነት አካሄድ እንድትከተል ነው? አንድን ፋሽን መከተል እንዳለብህ እንዲሰማህ የሚያደርግ መልእክት በተዘዋዋሪ መንገድ እያስተላለፉ ነው? በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኘው ካረን እንዲህ ብላለች፦ “እንከን የለሽ ሆነን እንድንታይ፣ እንከን የለሽ አለባበስ እንዲኖረንና ‘እንከን የማይወጣለትን’ ሰውነታችንን እንድናሳይ ከፍተኛ ጫና ይደርስብናል። ይህን ለተገነዘቡ ማስታወቂያ አዘጋጆች ወጣቶችን መማረክ ቀላል ነው።”

ስህተት #2፦ ብዙኃኑን ለመምሰል ሲባል ፋሽን የሆነውን አለባበስ መከተል።

 ማኑዌል የተባለ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ልብስ ፋሽን ከሆነ ሁሉም ሰው ይለብሰዋል። ያንን ፋሽን ካልተከተልክ እንደ ኋላቀር ያዩሃል።” በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው አና ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ሰጥታለች። አና ወጣቶቹን “ይበልጥ የሚማርካቸው ፋሽኑን መከተላቸው ሳይሆን ከሌሎች ጋር መመሳሰላቸው” እንደሆነ ተናግራለች።

 የተሻለው አካሄድ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” ይላል። (ሮም 12:2) ከዚህ ምክር አንጻር ልብሶችህን ተመልከት፤ ከዚያም ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦

  •  ‘በልብስ ምርጫዬ ላይ በዋነኝነት ተጽዕኖ የሚያደርገው ምንድን ነው?’

  •  ‘ታዋቂ ዲዛይነሮች ወይም ድርጅቶች ለሚያዘጋጇቸው ልብሶች ምን ያህል ቦታ እሰጣለሁ?’

  •  ‘አለባበሴ ዓይን ውስጥ እንድገባ የሚያደርግ ነው?’

 ጠቃሚ ምክር፦ ስለ አለባበሳችሁ ስታስቡ ፋሽን የሆነ (ተቀባይነት ያለው) ወይም ፋሽኑ ያለፈበት (ተቀባይነት የሌለው) የሚሉትን ምርጫዎች ብቻ ከማሰብ ይልቅ ሦስተኛ አማራጭ ይኸውም በራስ መተማመን የሚንጸባረቅበት የሚለውንም አስቡ። በራስህ የምትተማመን ከሆነ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ያን ያህል አያሳስብህም።

ስህተት #3፦ ‘ወንዶችን/ሴቶችን የሚስበው ይሄ ነው’ ብሎ ማሰብ።

 ጄኒፈር የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እውነቱን ለመናገር ትንሽ ወጣ ያለ፣ ማለቴ በጣም አጭር ወይም ጥብቅ ያለ አሊያም ሰውነትን የሚያጋልጥ ልብስ ለመልበስ የምፈተንበት ጊዜ አለ።”

 የተሻለው አካሄድ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በማጌጥ . . . አይሁን፤ ከዚህ ይልቅ ውበታችሁ . . . የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን” ይላል። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4) ይህን ምክር ከግምት በማስገባት እንደሚከተለው ብለህ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ሌሎችን ይበልጥ የሚስበው ምንድን ነው? ዓይንን የሚማርክ አለባበስ ወይስ ልብን የሚማርክ ባሕርይ?’

 ጠቃሚ ምክር፦ በፋሽን ረገድ ከሁሉ የተሻለው አካሄድ፣ ልከኝነት የሚንጸባረቅበት አለባበስ መምረጥ ነው። እርግጥ ነው፣ ልከኝነት በዛሬው ጊዜ የሚወደድ ሐሳብ አይደለም። ይሁንና እስቲ በሚከተለው መንገድ ለማሰብ ሞክር፦

 ስለ ራሱ ብዙ የሚያወራ ሰው አጋጥሞህ ያውቃል? የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ ግለሰቡ እንድትርቀው እያደረገህ እንዳለ አይገነዘብም!

እንደ ወሬያችን ሁሉ አለባበሳችንም ወደ ራሳችን ትኩረት የሚስብ ከሆነ ሌሎች እንዲርቁን ሊያደርግ ይችላል

 የምትለብሰው ልብስ ጨዋነት የጎደለው ከሆነ እንደዚህ ግለሰብ ትሆናለህ። አለባበስህ ‘እዩኝ፣ እዩኝ’ እያልክ እንደሆነ ሊያስመስልብህ ይችላል፤ ይህ ደግሞ በራስህ እንደማትተማመን ወይም ስለ ራስህ ከመጠን በላይ እንደምታስብ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የሌሎችን ትኩረት (ተገቢ ያልሆነውንም ጭምር) ለማግኘት በጣም የምትጓጓ ሰው እንደሆንክ ተደርገህ ልትታይ ትችላለህ።

 ይህም የማትሸጠውን ነገር እንደማስተዋወቅ ነው፤ ከዚህ ይልቅ ልከኛ አለባበስ ይኑርህ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ሞኒካ እንዲህ ብላለች፦ “ልከኛ መሆን ሲባል እንደ አያትሽ ትለብሻለሽ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለራስሽም ሆነ ለሌሎች አክብሮት እንዳለሽ የሚያሳይ አለባበስ ይኖርሻል ማለት ነው።”