በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

በሚዲያ ላይ የሚታዩ እኩዮቼን መምሰል የሌለብኝ ለምንድን ነው?—ክፍል 1 (ለሴቶች)

በሚዲያ ላይ የሚታዩ እኩዮቼን መምሰል የሌለብኝ ለምንድን ነው?—ክፍል 1 (ለሴቶች)

 በሚዲያ ላይ የሚቀርቡት እኩዮችሽ ምን ዓይነት ባሕርይ አላቸው?

 ከታች ያሉትን ባሕርያት ተመልከቺ፤ ከዚያም ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ስጪ።

ረድፍ 1

ረድፍ 2

ብስለት የሌላት

ኃላፊነት የሚሰማት

የማትታዘዝ

ታዛዥ

ሥርዓተ ቢስ

ጥሩ ሥነ ምግባር ያላት

ሞኝ

ብልህ

ሐሜተኛ

ቁጥብ

አታላይ

ሐቀኛ

  1.   በፊልም፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ወይም በመጽሔት ላይ የሚታዩት ወጣት ሴቶች ከላይ ከተጠቀሱት መካከል ይበልጥ የሚታወቁት በየትኞቹ ባሕርያት ነው?

  2.   አንቺስ ከላይ ከተጠቀሱት ባሕርያት መካከል የትኞቹ እንዲኖሩሽ ትፈልጊያለሽ?

 ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ የሰጠሽው ከረድፍ 1 በመምረጥ ሊሆን ይችላል፤ ለሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ በረድፍ 2 ሥር ካሉት መካከል እንደምትመርጪ የታወቀ ነው። ይህም በሚዲያ ላይ ከሚቀርቡት ወጣቶች የተሻለ ሰው መሆን እንደምትፈልጊ ያሳያል፤ ደግሞም እንዲህ መሆን የምትፈልጊው አንቺ ብቻ አይደለሽም! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

 “ብዙውን ጊዜ ፊልሞች፣ ወጣት ሴቶች መታዘዝ የማይወዱና የሆነ የባሕርይ ችግር ያለባቸው እንደሆኑ አድርገው ያቀርባሉ። እነዚህ ፊልሞች፣ ወጣት ሴቶች የተባልን በሙሉ እምነት የማይጣልብን፣ ሌሎች ሰዎች ስለ እኛ ያላቸው አመለካከት ከልክ በላይ የሚያሳስበንና ከመጠን በላይ ስሜታዊ የሆንን ያስመስሉናል።”—ኤሪን

 “በፊልሞችና በቲቪ ላይ የሚቀርቡት ወጣት ሴቶች የሰዎችን ትኩረት መሳብ በጣም ይፈልጋሉ፤ ሁልጊዜ የሚያስቡት ስለ መልካቸው፣ ስለ ልብሳቸው፣ ተወዳጅ ስለ መሆናቸው ወይም ደግሞ ስለ ወንዶች ነው።”—ናታሊ

 “አንዲት ‘አሪፍ’ የምትባል ልጅ አብዛኛውን ጊዜ የምትታየው ስትጠጣ፣ ከወንዶች ጋር ስትወጣ ወይም ወላጆቿን አልታዘዝም ስትል ነው። አንዲት ልጅ እነዚህን ነገሮች ካላደረገች እንደ አክራሪ ሃይማኖተኛ ወይም ስለ ወሲብ ሲነሳ በጣም እንደምታፍር አድርገው ይመለከቷታል።”—ማሪያ

 ራስሽን እንዲህ ብለሽ ጠይቂ፦ ‘አለባበሴ፣ ሁኔታዬ ወይም የምናገርበት መንገድ የሚያንጸባርቀው የራሴን ማንነት ነው ወይስ በሚዲያ ላይ የሚቀርቡትን ወጣቶች?’

 ልታውቂው የሚገባ ነገር

  •   የራሳቸው ማንነት እንዳላቸው የሚሰማቸው በርካታ ወጣቶች በሚዲያ ላይ የሚታዩ ሰዎችን እየመሰሉ እንዳለ አያውቁም። “ይህንን ሁኔታ በትንሿ እህቴ ላይ ተመልክቻለሁ” በማለት ካረን የተባለች ወጣት ተናግራለች። “የምታስበው ስለ ልብስ እና ስለ ወንዶች ብቻ እንደሆነ ለማስመሰል ትሞክራለች። በጣም ጎበዝ ልጅ ነች፤ ደግሞም የምታስበው ስለ እነዚህ ጉዳዮች ብቻ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ ግን እንደ ሌሎቹ ሴቶች መሆን ከፈለገች ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላት ይሰማታል። በዚያ ላይ ደግሞ ገና የ12 ዓመት ልጅ ናት!”

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የዚህን ሥርዓት የአኗኗር ዘይቤ መኮረጅ አቁሙ።”—ሮም 12:2

  •   በሚዲያ ላይ እንደሚቀርቡት ሴቶች መሆን የሚፈልጉት ሁሉም ወጣት ሴቶች አይደሉም። የ15 ዓመቷ አሌክሲስ እንዲህ ብላለች፦ “በሚዲያ ላይ ወጣት ሴቶች ስለ ራሳቸው ከልክ በላይ ሲጨነቁ እና የሞኝነት ድርጊት ሲፈጽሙ ይታያሉ፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ብዙዎቻችን ከዚህ በተሻለ አስተዋዮች እንደሆንን ይሰማኛል። ስለ አንድ የሚያምር ልጅ ቀኑን ሙሉ እያሰብን ከመዋል በተሻለ የምናከናውናቸው ብዙ ቁም ነገሮች አሉ።”

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‘ጎልማሳ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ያሠለጥናሉ።’—ዕብራውያን 5:14

  •   ሚዲያው ሴቶችን በዚህ መንገድ የሚያቀርብበት ምክንያት ወጣት ሴቶችን ሳይሆን ነጋዴዎችን ለመጥቀም ነው። በሕትመት፣ በፋሽን፣ በቴክኖሎጂና በመዝናኛው ዓለም ያሉ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ወደፊት የሚያስገኝላቸውን ትርፍ በማሰብ ገና 13 ዓመት ባልሞላቸው ወጣቶች ላይ ያተኮሩ ማስታወቂያዎች ይሠራሉ። “የማስታወቂያ ባለሙያዎች 13 ዓመት ላልሞላቸው ወጣቶች ‘የፋሽን ልብሶች፣ ጌጣጌጦች፣ መኳኳያዎች ወይም የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ከሌሏችሁ በጓደኞቻችሁ ዘንድ ተወዳጅ አትሆኑም’ የሚል መልእክት የሚያስተላልፉ ማስታወቂያዎችን ይሠራሉ። እነዚህ ለጋ ወጣቶች እነሱን ለመማረክ ተብለው የተዘጋጁትን ማስታወቂያዎች ዘወትር ይመለከታሉ ወይም ይሰማሉ፤ ታዳጊዎቹ ለእነዚህ ማስታወቂያዎች የሚጋለጡት ገና ከፆታ ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሳይደርሱ ነው” በማለት 12 ጎይንግ ኦን 29 የተባለው መጽሐፍ ተናግሯል።

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በዓለም ያለው ነገር ሁሉ ይኸውም የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጭ አይደለም።”—1 ዮሐንስ 2:16

 እስቲ አስቢው፦ ታዋቂ የፋሽን ብራንድ ያላቸው ምርቶችን መጠቀም የሚያሳስብሽ ከሆነ ከሁሉ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ይመስልሻል? በጓደኞችሽ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስትዪ ብቻ አዲስ የወጣ ሞባይል መያዝ እንዳለብሽ የሚሰማሽ ከሆነ ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ነው? የንግድ ድርጅቶች ይበልጥ የሚያሳስባቸው ምን ይመስልሻል? የአንቺ ጉዳይ ወይስ የራሳቸው ትርፍ?

 ምን ማድረግ ትችያለሽ?

  •   በሚዲያ ላይ የሚታዩ ሰዎች የሚያደርጉትን ነገር ዝም ብለሽ አትቀበዪ። እያደግሽ ስትሄጂ አንድ ነገር ከላይ እንደሚታየው ጥሩ መሆን አለመሆኑን የመለየት ችሎታ እያዳበርሽ ትሄጃለሽ። በሚዲያ ላይ የሚታዩ ሰዎች በአንቺ ላይ ስለሚያሳድሩት ተጽዕኖ ቆም ብለሽ ማሰብ ይኖርብሻል። የ14 ዓመቷ አላና እንዲህ ብላለች፦ “በሚዲያ ላይ ወጣት ሴቶች የሚቀርቡት በጣም ተኳኩለው ነው፤ ብዙ ወጣቶች ግን ከልክ በላይ መኳኳል ቆንጆ እንደማያደርጋቸው፣ ከዚህ ይልቅ የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ በጣም እንደሚፈልጉ የሚጠቁም መሆኑ አይገባቸውም።”

  •   መሆን የምትፈልጊውን ዓይነት ሰው ለመሆን የሚረዱሽን ግቦች አውጪ። ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተዘረዘሩትን አንቺ የምትፈልጊያቸውን ባሕርያት ለማሰብ ሞክሪ። እነዚህ ባሕርያት እንዲኖሩሽ ለማድረግ ወይም ባሕርያቱን ይበልጥ ለማሳየት ለምን ጥረት አታደርጊም? መጽሐፍ ቅዱስ በማስታወቂያዎች ላይ የሚታዩትን ሰዎች ዓይነት ስብዕና ሳይሆን “ከፈጣሪው አምሳል ጋር በሚስማማ ሁኔታ በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ስብዕና” እንድንለብስ ያበረታታል።—ቆላስይስ 3:10

  •   ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑሽ የሚችሉ ሰዎችን ፈልጊ። የቤተሰብሽን አባላት ለምሳሌ የእናትሽን ወይም የአክስትሽን ምሳሌ መከተል ትችያለሽ። ብስለት ያላቸው የሴት ጓደኞችሽ ወይም ሌሎች የምታከብሪያቸው ሴቶችም ምሳሌ ሊሆኑሽ ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወጣት ሴቶች፣ ምሳሌ ሊሆኗቸው የሚችሉ በርካታ ሴቶችን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ማግኘት ይችላሉ።—ቲቶ 2:3-5

 እንዲህ ለማድረግ ሞክሪ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ታሪካቸው ስለተጠቀሱ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑሽ የሚችሉ ሴቶች ለማወቅ በእምነታቸው ምሰሏቸው የተባለውን መጽሐፍ አንብቢ፤ በመጽሐፉ ላይ የሩት፣ የሐና፣ የአቢግያ፣ የአስቴር፣ የማርያምና የማርታ ታሪክ ተጠቅሷል። በእምነታቸው ምሰሏቸው የተባለው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው መጽሐፍ www.pr418.com/am ላይ ይገኛል።