በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ሐቀኛ መሆን ለምን አስፈለገ?

ሐቀኛ መሆን ለምን አስፈለገ?

 አንዳንዶች ሐቀኛ የማይሆኑበት ምክንያት

 በዘመናችን ብዙ ሰዎች ሐቀኛ መሆን ምንም ጥቅም እንደሌለው ይሰማቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ ሊሉ ይችላሉ፦

  •   ‘ወላጆቼን ካልዋሸኋቸው ሊቀጡኝ ይችላሉ።’

  •   ‘በዚህ ፈተና ላይ ካልኮረጅኩ ልወድቅ እችላለሁ።’

  •   ‘ይህን ዕቃ ካልሰረቅኩ ዕቃውን ለመግዛት ገንዘብ ማጠራቀም ይኖርብኛል።’

 ከዚህም በተጨማሪ አንዳንዶች ‘ምን ችግር አለው? ሁሉም ሰው ሐቀኝነት የጎደለው ተግባር ይፈጽም የለ?’ በማለት ሊጠይቁ ይችላሉ።

 ያም ቢሆን ሐቀኝነት በጎደለው ተግባር የሚካፈለው ሁሉም ሰው አይደለም። በርካታ ወጣቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ሐቀኛ መሆን ጥቅም እንደሚያስገኝ ይሰማቸዋል፤ ደግሞም እንዲህ ማሰባቸው ተገቢ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል” ይላል። (ገላትያ 6:7) ይህ ማለት የምናደርጋቸው ነገሮች ምንጊዜም ቢሆን ጥሩ ወይም መጥፎ ውጤት ይኖራቸዋል ማለት ነው።

 ለምሳሌ፣ አንዳንዶች መዋሸታቸው ያስከተለባቸውን መጥፎ መዘዝ እንመልከት፦

“እናቴ፣ ከአንድ ልጅ ጋር አውርቼ እንደነበር ስትጠይቀኝ ዋሸሁ። ጉዳዩን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መረጃ ስለነበራት እንደዋሸኋት ተረድታ ነበር። ስለ ልጁ ለሦስተኛ ጊዜ ስዋሻት በጣም ተናደደች። ለሁለት ሳምንት ያህል ከቤት ወጥቼ እንዳልዝናና የተቀጣሁ ሲሆን ለአንድ ወር ያህል ሞባይል ስልኬን እንዳልጠቀም እንዲሁም ቴሌቪዥን እንዳላይ ተከለከልኩ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ወላጆቼን ዋሽቼ አላውቅም!”—አኒታ

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ አኒታ፣ የእናቷን አመኔታ በድጋሚ ለማትረፍ ጊዜ ሊወስድባት የሚችለው ለምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አሁን አታላይነትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።”—ኤፌሶን 4:25

“ወላጆቼን ዋሽቼ ማምለጥ የምችል መስሎኝ ነበር፤ ሆኖም ያወራሁትን ነገር በድጋሚ እንድነግራቸው ሲጠይቁኝ ያልጠበቅኩት ነገር ተከሰተ። የነገርኳቸው ነገር በጣም ከእውነት የራቀ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ ዝርዝር ነገሮችን ማስታወስ አቃተኝ። መጀመሪያውኑ እውነቱን ከተናገራችሁ እንደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ አትገቡም!”—አንቶኒ

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ አንቶኒ እንዲህ ያለ አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባ ምን ማድረግ ይችል ነበር?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ይሖዋ ውሸታም ከንፈሮችን ይጸየፋል፤ በታማኝነት የሚመላለሱ ግን ደስ ያሰኙታል።”—ምሳሌ 12:22

“ወሬ አዳምቃ ማውራት የምትወድ ጓደኛ አለችኝ። ነገሮች አጋንና ማውራት የምትወድ ከመሆኑም ሌላ ሰዎች ባላሰቡት መንገድ ነገሮችን ተርጉማ ልታወራ ትችላለች። ስለምወዳት በምታወራው ነገር ላይ ትኩረት ላለማድረግ እሞክራለሁ። ይሁንና እሷን ማመንም ሆነ በእሷ ላይ እምነት መጣል በጣም ይከብዳል።”—ኢቮን

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የኢቮን ጓደኛ ነገሮችን አጋንና ማውራቷ ወይም “ጥቃቅን” ውሸቶችን መናገሯ ምን ዓይነት ስም አሰጥቷታል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18

በአንድ ሕንፃ መሠረት ላይ የሚፈጠር ስንጥቅ ጠቅላላ ሕንፃውን ሊያናጋ እንደሚችል ሁሉ ሐቀኝነት የጎደለው ተግባርም ጥሩ ስምህን ሊያጎድፍ ይችላል

 ሐቀኛ መሆን ምን ጥቅም ያስገኛል?

 አሁን ደግሞ ሐቀኛ መሆን የሚያስገኛቸውን አንዳንድ ጥቅሞች እንመልከት፦

“ከፊት ለፊቴ ትሄድ የነበረች አንዲት ሴት ገንዘብ ብትጥልም አላየችውም። በመሆኑም ጠርቼ ገንዘቡን ሰጠኋት። እሷም በጣም አመሰገነችኝ። ከዚያም ‘በጣም ጥሩ ሰው ነሽ። በሐቀኝነት እንዲህ የሚያደርግ ብዙ ሰው የለም’ አለችኝ። ትክክል የሆነውን ነገር አድርጎ መመስገን ጥሩ ስሜት ይፈጥራል!”ቪቪየን

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ይህቺ ሴት እንደዚህ ዓይነት የሐቀኝነት ድርጊት ማየቷ ያስገረማት ለምን ሊሆን ይችላል? ቪቪየን ሐቀኛ መሆኗ የጠቀማት እንዴት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ምንጊዜም ትክክል የሆነውን የሚያደርጉ ደስተኞች ናቸው።”—መዝሙር 106:3

“ቤተሰባችን በጽዳት ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ቢሮዎችን ስናጸዳ ሳንቲም መሬት ላይ ወድቆ እናገኛለን። በዚህ ጊዜ ሳንቲሙን አንስተን አቅራቢያው ባለ ጠረጴዛ ላይ እናስቀምጣለን። ከሠራተኞቹ አንዷ በምናሳየው የሐቀኝነት ድርጊት ትበሳጭ ነበር። እንዲያውም አንድ ቀን ‘አሥር ሳንቲም እኮ ነው!’ አለችን። ያም ቢሆን ምንጊዜም ትተማመንብን ነበር።”—ጁሊያ

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ጁሊያ፣ ሐቀኝነት በማሳየት ረገድ ያተረፈችው ስም ወደፊት ሌላ ሥራ ለመቀጠር የድጋፍ ደብዳቤ በሚያስፈልጋት ጊዜ ሊጠቅማት የሚችለው እንዴት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚገባውና ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ አድርገህ ራስህን በአምላክ ፊት ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።”—2 ጢሞቴዎስ 2:15

“የሠራሁት 64 ሰዓት ቢሆንም የ80 ሰዓት የክፍያ ደረሰኝ ተሰጠኝ። ገንዘቡን ብወስደው ሊጠቅመኝ የሚችል ቢሆንም እንኳ እንደዛ አላደረግኩም። ሁኔታውን ለሒሳብ ክፍል ኃላፊዋ ሳሳውቃት በጣም አመሰገነችኝ። ምንም እንኳ ድርጅቱ አትራፊ ቢሆንም የተሰረቀ አድርጌ የምመለከተውን ገንዘብ ለማስቀረት አልፈለግኩም።”—ቤተኒ

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ከአንድ ድርጅት ላይ መስረቅ ከአንድ ሰው ላይ ከመስረቅ ጋ ሲወዳደር ቀለል ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋልና፤ ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው።”—ምሳሌ 3:32