በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ሕሊናዬን ማሠልጠን የምችለው እንዴት ነው?

ሕሊናዬን ማሠልጠን የምችለው እንዴት ነው?

 ሕሊናህ ከምን ጋር ሊመሳሰል ይችላል?

  •   ከኮምፓስ?

  •   ከመስተዋት?

  •   ከጓደኛ?

  •   ከዳኛ?

 አራቱም መልሶች ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ ይህ ርዕስ ያብራራል።

 ሕሊና ምንድን ነው?

 ሕሊና ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የሚረዳ ችሎታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሕሊና ‘በልብ ላይ እንደተጻፈ ሕግ’ እንደሆነ ይናገራል። (ሮም 2:15) ጥሩ ሕሊና ልታደርገው ያሰብከውን ወይም ያደረግከውን ውሳኔ እንድትገመግም ይረዳሃል።

  •   ሕሊና እንደ ኮምፓስ ነው። ችግር ውስጥ እንዳትገባ ወደ ትክክለኛው መንገድ ይመራሃል።

  •   ሕሊና እንደ መስተዋት ነው። ያለህን የሥነ ምግባር አቋምና ምን ዓይነት ሰው እንደሆንክ ያሳይሃል።

  •   ሕሊና እንደ ጥሩ ጓደኛ ነው። ከሰማኸው ስኬታማ እንድትሆን የሚረዳ ጥሩ ምክር ይሰጥሃል።

  •   ሕሊና እንደ ዳኛ ነው። መጥፎ ነገር ስታደርግ ይፈርድብሃል።

ጥሩ ሕሊና ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ይረዳሃል

 ዋናው ነጥብ፦ ሕሊና (1) ጥሩ ውሳኔ እንድታደርግ እንዲሁም (2) ስህተትህን ማረም እንድትችል የሚረዳህ በጣም አስፈላጊ የሆነ መሣሪያ ነው።

 ሕሊናህን ማሠልጠን ያለብህ ለምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ “ጥሩ ሕሊና ይኑራችሁ” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥሮስ 3:16) ሆኖም ሕሊናህ ካልሠለጠነ ጥሩ ሕሊና መያዝ ከባድ ይሆንብሃል።

 “ወላጆቼ የት እንዳለሁ ሲጠይቁኝ እዋሻቸው ነበር። መጀመሪያ አካባቢ ሕሊናዬ ይረብሸኝ ነበር፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ይህ ስሜት ጠፋ።”—ጄኒፈር

 በኋላ ላይ የጄኒፈር ሕሊና ለወላጆቿ እውነቱን እንድትነግራቸውና እነሱን ማታለሏን እንድታቆም አነሳስቷታል።

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የጄኒፈር ሕሊና መቼ ቢያስጠነቅቃት ይሻል ነበር?

 “ሁለት ዓይነት ሕይወት መምራት ከባድና ውጥረት የሚፈጥር ነገር ነው። ሕሊናችሁ አንድ ጊዜ መጥፎ ውሳኔ እንድታደርጉ ከፈቀደላችሁ ሌላ ጊዜ መጥፎ ውሳኔ ማድረግ እየቀለላችሁ ይመጣል።”—ማቲው

 አንዳንድ ሰዎች ሕሊናቸውን ከናካቴው መስማት ያቆማሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው እነዚህ ሰዎች ‘የሥነ ምግባር ስሜታቸው ደንዝዟል።’ (ኤፌሶን 4:19) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ሐረግ “የኀፍረት ስሜታቸው በሙሉ ጠፍቷል” በማለት ተርጉሞታል።

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ መጥፎ ነገር ቢሠሩም የጥፋተኝነት ስሜት የማይሰማቸው ሰዎች ሕይወታቸው የተሻለ የሚሆን ይመስልሃል? እነዚህ ሰዎች ወደፊት ምን ዓይነት ችግር ያጋጥማቸዋል?

 ዋናው ነጥብ፦ ጥሩ ሕሊና እንዲኖርህ ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የማስተዋል ችሎታህን በማሠራት ማሠልጠን’ ያስፈልግሃል።—ዕብራውያን 5:14

 ሕሊናህን ማሠልጠን የምትችለው እንዴት ነው?

 ሕሊናህን ለማሠልጠን የራስህን ድርጊት ከአንድ መሥፈርት ጋር ልታወዳድር ይገባል። አንዳንዶች፣ ሌሎች ሰዎች ባወጧቸው መሥፈርቶች ይመራሉ፤ ለምሳሌ

  •   ቤተሰባቸው ወይም ማኅበረሰቡ

  •   እኩዮቻቸው

  •   ታዋቂ ሰዎች

 ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት እነዚህ ሰዎች ከሚያወጡት መሥፈርት በእጅጉ የላቀ ነው። ደግሞም ይህ መሆኑ አያስገርምም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው “በአምላክ መንፈስ መሪነት” ነው፤ አምላክ ደግሞ ፈጣሪያችን ከመሆኑም ሌላ ለእኛ የሚበጀን ምን እንደሆነ ያውቃል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

 እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

 መሥፈርት፦ “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18

  •   ፈተና ላይ ለመኮረጅ፣ ወላጆችህን ለመዋሸት ወይም ለመስረቅ ስትፈተን ይህ መሥፈርት ሕሊናህን ለማሠልጠን የሚረዳህ እንዴት ነው?

  •   ሕሊናህ በሁሉም ነገር ሐቀኛ እንድትሆን የሚገፋፋህ ከሆነ አሁንም ሆነ ወደፊት ምን ጥቅም የምታገኝ ይመስልሃል?

 መሥፈርት፦ “ከፆታ ብልግና ሽሹ።”—1 ቆሮንቶስ 6:18

  •    ፖርኖግራፊ ለማየት ወይም ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ስትፈተን ይህ መሥፈርት ሕሊናህን ለማሠልጠን የሚረዳህ እንዴት ነው?

  •   ሕሊናህ ከፆታ ብልግና እንድትሸሽ የሚገፋፋህ ከሆነ አሁንም ሆነ ወደፊት ምን ጥቅም ታገኛለህ?

 መሥፈርት፦ “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ . . . እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።”—ኤፌሶን 4:32

  •    ከወንድምህ፣ ከእህትህ ወይም ከጓደኛህ ጋር በምትጣላበት ጊዜ ይህ መሥፈርት ሕሊናህን ለማሠልጠን የሚረዳህ እንዴት ነው?

  •   ሕሊናህ መሐሪና ሩኅሩኅ እንድትሆን የሚገፋፋህ ከሆነ አሁንም ሆነ ወደፊት ምን ጥቅም ታገኛለህ?

 መሥፈርት፦ “ይሖዋ . . . ዓመፅን የሚወድን ማንኛውንም ሰው ይጠላል።”—መዝሙር 11:5

  •    ፊልም፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ወይም ቪዲዮ ጌም በምትመርጥበት ጊዜ ይህ መሥፈርት የሚረዳህ እንዴት ነው?

  •   ሕሊናህ ዓመፅ ከሚንጸባረቅበት መዝናኛ እንድትርቅ የሚገፋፋህ ከሆነ አሁንም ሆነ ወደፊት ምን ጥቅም ታገኛለህ?

 እውነተኛ ታሪክ፦ “ጓደኞቼ ዓመፅ የሚንጸባረቅበት የቪዲዮ ጌም ይጫወቱ ነበር፤ እኔም እጫወት ነበር። በኋላ ግን አባቴ እነዚህን ጌሞች እንዳልጫወት ከለከለኝ። ስለዚህ ጓደኞቼ ቤት ስሄድ ብቻ መጫወት ጀመርኩ። ወደ ቤት ስመለስ ምን ሳደርግ እንደቆየሁ አልናገርም ነበር። አባቴ ‘ምን ሆነሃል?’ ብሎ ሲጠይቀኝ ‘ምንም አልሆንኩም’ እለው ነበር። አንድ ቀን ግን መዝሙር 11:5⁠ን ሳነብ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰማኝ። እነዚያን ጌሞች መጫወት እንደሌለብኝ ገባኝ። ከዚያም መጫወቴን አቆምኩ። አንዱ ጓደኛዬም የእኔን ምሳሌ በመከተል ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸው ጌሞችን መጫወት አቆመ።”—ጄረሚ

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የጄረሚ ሕሊና መሥራት የጀመረው መቼ ነው? ጄረሚ ሕሊናውን መስማት የጀመረውስ መቼ ነው? ከጄረሚ ታሪክ ምን ትማራለህ?

 ዋናው ነጥብ፦ ሕሊናችን ምን ዓይነት ሰው እንደሆንንና ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ለምን ነገር እንደሆነ ያሳያል። ሕሊናህ ስለ አንተ ምን ይናገር ይሆን?