በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የምችለው እንዴት ነው?

የተመጣጠነ ምግብ መመገብ የምችለው እንዴት ነው?

 የተመጣጠነ ምግብ አለመመገብ ጤንነትህን እንደሚጎዳው ሳታውቅ አትቀርም። ጤናማ አመጋገብ የሌላቸው ወጣቶች አዋቂ ከሆኑ በኋላም አመጋገባቸው ጤናማ አይሆንም፤ በመሆኑም ከአሁኑ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ ማዳበርህ አስፈላጊ ነው።

 የተመጣጠነ ምግብ ምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ ‘በልማዶቻችን ልከኞች’ እንድንሆን ይመክረናል፤ ይህም አመጋገብን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:11) ይህን በአእምሯችን ይዘን የሚከተሉትን ነጥቦች ማስተዋላችን ጠቃሚ ነው፦

  •   የተመጣጠነ ምግብ ሁሉንም የምግብ ቡድኖች ያካትታል። አምስቱ የምግብ ቡድኖች የወተት ተዋጽኦዎችን፣ ፕሮቲንን፣ ፍራፍሬን፣ አትክልትንና የእህል ዘሮችን ይጨምራሉ። አንዳንድ ሰዎች ውፍረት ለመቀነስ በማሰብ ከእነዚህ ቡድኖች መካከል የተወሰኑትን ሙሉ በሙሉ ይተዋሉ። ሆኖም እንዲህ ካደረግክ ለሰውነትህ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ልታጣ ትችላለህ።

     እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በምግብ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ያላቸውን ጥቅም ለማወቅ ምርምር አድርግ ወይም ሐኪምህን አማክር። ለምሳሌ፦

     ካርቦሃይድሬት ጉልበት ይሰጥሃል። ፕሮቲን በሽታ የሚከላከል ከመሆኑም ሌላ ሰውነትህን ይጠግነዋል እንዲሁም ይገነባዋል። አንዳንድ ቅባቶችን በተገቢው መጠን መመገብህ በልብ በሽታ የመያዝ አጋጣሚህ እንዲቀንስ እንዲሁም ኃይል እንዲኖርህ ያደርጋል።

     “ከሁሉም የምግብ ቡድኖች ለመመገብ ጥረት አደርጋለሁ። አልፎ አልፎ ጣፋጭ ነገር ወይም ቅባት የበዛበት ምግብ መመገብ ችግር እንዳለው አይሰማኝም። ግን ሁልጊዜ እንዲህ ያሉ ምግቦችን መመገብም ተገቢ አይደለም። ብቻ ሁሉንም ነገር በልክ ማድረግ ጥሩ ነው።”—ብሬንዳ

    አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ያላሟላ ምግብ አንድ እግር እንደጎደለው ወንበር ነው

  •   ጽንፈኛ አትሁን። ጽንፈኛ መሆን ሲባል በቂ ምግብ አለመመገብን፣ ከልክ በላይ መብላትን ወይም አንድን ምግብ የምትወደው ቢሆንም ጨርሶ ከመብላት መቆጠብን ይጨምራል።

     እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ለአንድ ወር ያህል አመጋገብህን ገምግም። ከላይ በተጠቀሱት ጽንፈኛ የአመጋገብ ልማዶች ብዙ ጊዜ ትሸነፋለህ? ጤናማ አመጋገብ እንዲኖርህ ምን ማስተካከያዎችን ማድረግ ትችላለህ?

     “አንዳንድ ጊዜ በጣም ብዙ ካሎሪ ያለው ምግብ እመገባለሁ፤ አንዳንዴ ደግሞ በጣም ጥቂት ካሎሪ ያለው ምግብ ብቻ እመገባለሁ። በኋላ ላይ ግን ካሎሪ ከመቁጠር ይልቅ ከልክ በላይ ላለመብላት መጠንቀቅ እንዲሁም ልክ እንደጠገብኩ መብላቴን ማቆም ጀመርኩ። እንዲህ ለማድረግ ጊዜ ቢወስድብኝም አሁን አመጋገቤ ጤናማ ነው።”—ሄይሊ

 የተመጣጠነ ምግብ የመመገብ ልማድ ሊኖረኝ የሚችለው እንዴት ነው?

  •   አስቀድመህ አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) ጤናማ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር ዕቅድ ማውጣት ይጠይቃል።

     “የተመጣጠነ ምግብ ለመብላት ዕቅድ ማውጣት ይጠይቃል፤ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ምግብ ጤናማ የሚሆነው ቤት ውስጥ ሲሠራ ነው። እንዲህ ማድረግ ጥረት ቢጠይቅም በኋላ ላይ መልሶ ይክሳል፤ ገንዘብም ይቆጥባል።”—ቶማስ

  •   ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን በጤናማ ምግቦች ተካ። መጽሐፍ ቅዱስ “ማስተዋል የታከለበትን ጥበብ . . . ጠብቅ” ይላል። (ምሳሌ 3:21 የግርጌ ማስታወሻ) ማስተዋል የታከለበት ጥበብ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር የምትችልበትን መንገድ እንድታስተውል ይረዳሃል።

     “በቀን አንድን ጤናማ ያልሆነ ምግብ በጤናማ ምግብ ለመተካት እሞክራለሁ። ለምሳሌ በቸኮሌት ፋንታ ፖም እበላለሁ። ብዙም ሳይቆይ ጤናማ ያልሆኑ በርካታ ምግቦችን በጤናማ ምግቦች መተካት ቻልኩ!”—ኪያ

  •   ከራስህ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ሚዛናዊ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “ምግብህን በደስታ ብላ” ይላል። (መክብብ 9:7) የተመጣጠነ ምግብ ለመመገብ ስትል ከመብላት የሚገኘውን ደስታ ማጣት የለብህም፤ እንዲሁም ስለ እያንዳንዱ ጉርሻ መጨነቅ አይኖርብህም። ክብደት መቀነስ ቢኖርብህም እንኳ ዋነኛው ግብህ ጤናማ መሆን እንደሆነ አትዘንጋ። ከራስህ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ሚዛናዊ ሁን።

     “በቅርቡ 14 ኪሎ ገደማ ቀንሻለሁ፤ ይህን ለማድረግ ስል ግን አልተራብኩም፤ የተውኩት የምግብ ቡድን የለም እንዲሁም ጣፋጭ እያማረኝ ሳልበላ ቀርቼ አላውቅም። በአንዴ ውፍረት መቀነስ እንደማልችልና የአመጋገብ ልማዴን መቀየር እንዳለብኝ ተገንዝቤ ነበር።”—ሜላኒ