በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ስህተት ስሠራ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

ስህተት ስሠራ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

 አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?

 እስቲ ካሪና ምን እንዳጋጠማት እንመልከት፤ ሁኔታው በአንተ እንደደረሰ አድርገህ ለማሰብ ሞክር። በእሷ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርጋለህ?

 ካሪና፦ “ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ በፍጥነት እየነዳሁ ነበር፤ አንድ ፖሊስ አስቆመኝና ቀጣኝ። በጣም ተበሳጨሁ! ለእናቴ ስነግራት፣ ለአባቴ እንድነግረው ነገረችኝ፤ እኔ ደግሞ ይህን ማድረግ አልፈለግኩም።”

አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?

  1.  አማራጭ ሀ፦ አባትህ ጉዳዩን እንዳይሰማ ተስፋ በማድረግ ዝም ማለት።

  2.  አማራጭ ለ፦ የተፈጠረውን ነገር ለአባትህ በግልጽ መንገር።

 አማራጭ ሀ ላይ ያለውን ነገር ለማድረግ ትፈተን ይሆናል። ደግሞም እናትህ፣ ጉዳዩን ለአባትህ እንደነገርከው ማሰቧ አይቀርም። ይሁን እንጂ የሠራኸው ስህተት የትራፊክ ሕግ ከመጣስ ጋር የተያያዘ ሆነም አልሆነ፣ ስህተትህን በግልጽ መናገርህ ጠቃሚ የሚሆንባቸው ምክንያቶች አሉ።

 ስህተትህን አምነህ እንድትቀበል የሚያነሳሱ ሦስት ምክንያቶች

  1.  1. ስህተትን አምኖ መቀበል ትክክለኛ እርምጃ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ሊመሩበት የሚገባውን ደንብ ሲገልጽ “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር [እንመኛለን]” ይላል።—ዕብራውያን 13:18

     “ሐቀኛ ለመሆንና ለማደርጋቸው ነገሮች ኃላፊነቱን ለመውሰድ ከልቤ ጥረት አደርጋለሁ፤ ማለቴ ስህተት በምሠራበት ጊዜ ወዲያውኑ ጥፋቴን አምኜ ለመቀበል እጥራለሁ።”አሌክሲስ

  2.  2. ብዙውን ጊዜ ሰዎች፣ ስህተቱን አምኖ ለሚቀበል ሰው ይቅርታ ማድረግ አይከብዳቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል።”—ምሳሌ 28:13

     “ጥፋትን አምኖ መቀበል ድፍረት ይጠይቃል፤ የሰዎችን አመኔታ ለማትረፍ ግን ይህን ማድረግ አስፈላጊ ነው። እንደዚህ ስታደርግ ሰዎች ሐቀኛ እንደሆንክ ይመለከታሉ። ስህተትህን በማመን መጥፎ የሆነ ነገር ጥሩ ውጤት እንዲኖረው ማድረግ ትችላለህ።”ሪቻርድ

  3.  3. ከሁሉ በላይ ደግሞ ስህተትን አምኖ መቀበል ይሖዋ አምላክን ያስደስተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው” ይላል።—ምሳሌ 3:32 የ1954 ትርጉም

     “በአንድ ወቅት ከባድ ስህተት ሠርቼ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ጉዳዩን ለሌሎች መናገርና ስህተቴን አምኜ መቀበል እንዳለብኝ ተረዳሁ። ጉዳዩን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ባልይዘው ኖሮ የእሱን በረከት ማግኘት አልችልም ነበር።”ሬቸል

 ታዲያ ካሪና ምን አደረገች? በፍጥነት በማሽከርከሯ ምክንያት የተቀጣችበትን ወረቀት ከአባቷ ለመደበቅ ሞከረች። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ሚስጥር ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ አልቻለችም። ካሪና እንዲህ ብላለች፦ “ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ አባቴ፣ የኢንሹራንስ ሰነዶቻችንን ሲመለከት በእኔ ስም የተመዘገበ የትራፊክ የቅጣት ወረቀት ተመለከተ። ይህም ከባድ ችግር ውስጥ ከተተኝ፤ እናቴ እንኳ እሷ የነገረችኝን ነገር ባለማድረጌ በጣም ተቆጣች!”

 ምን ትምህርት አገኘች? ካሪና እንዲህ ብላለች፦ “ስህተትን መደበቅ ሁኔታውን ከማባባስ ውጪ ምንም ጥቅም የለውም። የኋላ ኋላ የእጃችሁን ማግኘታችሁ አይቀርም!”

 ከስህተትህ መማር የምትችለው እንዴት ነው?

 የማይሳሳት ሰው የለም። (ሮም 3:23፤ 1 ዮሐንስ 1:8) ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ወዲያውኑ ስህተትን አምኖ መቀበልና ጉዳዩ በተገቢው መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ የትሕትናና የብስለት ምልክት ነው።

 ቀጣዩ እርምጃ ከስህተትህ መማር ነው። የሚያሳዝነው አንዳንድ ወጣቶች ከስህተታቸው መማር ሳይችሉ ቀርተዋል! እነዚህ ወጣቶች ፕርስላ እንደተባለች ወጣት ይሰማቸው ይሆናል። እንዲህ ብላለች፦ “ስህተት መሥራቴ ተስፋ ያስቆርጠኝ ነበር። ለራሴ ያለኝ አመለካከት ዝቅ ያለ ስለነበር ስህተቶቼ ልሸከማቸው ከምችለው በላይ ከባድ እንደሆኑ ይሰማኝ ነበር። ሁኔታው ከአቅሜ በላይ ስለሚሆንብኝ የማልረባ እንደሆንኩ ማሰብ እጀምራለሁ።”

 አንተስ እንደዚህ የሚሰማህ ጊዜ አለ? ከሆነ የሚከተለውን ለማሰብ ሞክር፦ የሠራሃቸውን ስህተቶች እያሰቡ መብሰልሰል ዓይንን ከኋላ መመልከቻ መስታወት ሳይነቅሉ መኪና ከማሽከርከር ተለይቶ አይታይም። ባለፉ ነገሮች ላይ ማተኮር የዋጋ ቢስነት ስሜት እንዲሰማህ ከማድረጉም ሌላ ከፊትህ የሚያጋጥሙህን ችግሮች እንዳትወጣ አቅም ያሳጣሃል።

 ከዚህ ይልቅ ለምን ሚዛናዊ ለመሆን አትሞክርም?

 “ከዚህ በፊት የሠራሃቸውን ስህተቶች መለስ ብለህ አስብ፤ ከዚያም ደግመህ እንዳትሳሳት ካጋጠመህ ነገር ትምህርት ለማግኘት ሞክር። ያም ቢሆን ሕይወትህን እንዳያበላሹት ከልክ በላይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አትብሰልሰል።”ኤሊየት

 “ስህተቶቼን ለመማር እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርጌ ለመመልከት ጥረት አደርጋለሁ፤ ከእያንዳንዱ ስህተቴ ትምህርት በመውሰድ የተሻልኩ ሰው ለመሆንና ሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ሲያጋጥመኝ በተሻለ መንገድ ለመያዝ እሞክራለሁ። እንዲህ ማደረግ በጣም ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም እየበሰላችሁ እንድትሄዱ ይረዳችኋል።”ቪራ