በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ይቅርታ መጠየቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?

ይቅርታ መጠየቅ ያለብኝ ለምንድን ነው?

 የሚከተሉት ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህ ምን ታደርጋለህ?

  1.   ክፍል ውስጥ በመረበሽህ ምክንያት አስተማሪህ ተቆጣህ።

     አስተማሪህ ትንሽ እንዳካበደ ቢሰማህም ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብሃል?

  2.   አንዲት ጓደኛሽ ስለ እሷ ጥሩ ያልሆነ ነገር እንደተናገርሽ ሰማች።

     ስለ ጓደኛሽ የተናገርሽው ነገር እውነት እንደሆነ ብታውቂም ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብሻል?

  3.   አባትህ ስላበሳጨህ አክብሮት በጎደለው መንገድ አናገርከው።

     መጀመሪያ ያበሳጨህ አባትህ ራሱ እንደሆነ ቢሰማህም ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብሃል?

 የሦስቱም ጥያቄዎች መልስ “አዎ” የሚል ነው። ይሁንና ጥፋቱ የአንተ ብቻ እንደሆነ ባይሰማህም እንኳ ይቅርታ መጠየቅ ያለብህ ለምንድን ነው?

 ይቅርታ መጠየቅ ያለብህ ለምንድን ነው?

  •   ይቅርታ መጠየቅህ በሳል ሰው እንደሆንክ ያሳያል። ለተናገርከው ወይም ላደረግከው ነገር ኃላፊነት መውሰድህ አዋቂ ስትሆን የሚጠቅሙህን አንዳንድ አስፈላጊ ባሕርያት እያዳበርክ እንደሆነ ያሳያል።

     “ትሑትና ታጋሽ ከሆንን ይቅርታ መጠየቅና ያስቀየምነው ሰው የሚናገረውን ነገር ማዳመጥ ቀላል ይሆንልናል።”—ሬቸል

  •   ይቅርታ መጠየቅህ ሰላም ለመፍጠር ይረዳሃል። ይቅርታ የሚጠይቁ ሰዎች ይበልጥ የሚያሳስባቸው ነገር ጥፋተኞቹ እነሱ እንዳልሆኑ ማረጋገጥ ሳይሆን ሰላም መፍጠር እንደሆነ ያሳያሉ።

     “ጥፋተኛ እንዳልሆንክ ቢሰማህም ቅድሚያ የምትሰጠው ሰላም ለመፍጠር ሊሆን ይገባል። ይቅርታ መጠየቅ ቀላል ነገር ሊመስል ቢችልም ከጓደኛህ ጋር ያለህን ግንኙነት ለማደስ ይረዳሃል።”—ሚሪያም

  •   ይቅርታ መጠየቅህ ከጥፋተኝነት ስሜት ነፃ እንድትሆን ይረዳሃል። በተናገርከው ወይም ባደረግከው ነገር ምክንያት ሌላ ሰው ማስቀየምህ ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። ይቅርታ ከጠየቅክ በኋላ ግን የጥፋተኝነት ስሜቱ ቀለል ይልሃል። a

     “እናቴን ወይም አባቴን አክብሮት በጎደለው መንገድ ያነጋገርኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። የጥፋተኝነት ስሜት ቢሰማኝም ይቅርታ መጠየቅ ይከብደኝ ነበር። ይቅርታ ከጠየቅኩ በኋላ ግን በቤተሰባችን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን በማድረጌ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል።”—ኒያ

    የጥፋተኝነት ስሜት ከባድ ሸክም ነው፤ ይቅርታ ከጠየቅክ በኋላ ግን ሸክሙ ይወርድልሃል

 “ይቅርታ” ማለት ጥረት ይጠይቃል? አዎ! ዲና የተባለች አንዲት ወጣት እናቷን አክብሮት በጎደለው መንገድ በማነጋገሯ ምክንያት በተደጋጋሚ ይቅርታ መጠየቅ አስፈልጓታል፤ እንዲህ ብላለች፦ “ይቅርታ መጠየቅ ቀላል አይደለም። ‘ይቅርታ’ የሚለውን ቃል ማውጣት ይተናነቀኛል!”

 ይቅርታ መጠየቅ የምትችለው እንዴት ነው?

  •   ከቻልክ በአካል ሄደህ ይቅርታ ጠይቅ። በአካል ሄደህ ይቅርታ ስትጠይቅ ግለሰቡ ከልብህ እንደተጸጸትክ የሚያይበት አጋጣሚ ያገኛል። በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት ይቅርታ ከጠየቅክ ግን ግለሰቡ መጸጸትህን ላያምን ይችላል። የሐዘን ፊት የሚያሳይ ኢሞጂ መላክህም ቢሆን ይቅርታው ከልብህ መሆኑን አያሳይም።

     ጠቃሚ ምክር፦ በአካል ሄደህ ይቅርታ መጠየቅ ካልቻልክ ስልክ መደወል ወይም ፖስት ካርድ መጻፍ ትችል ይሆናል። ይቅርታ የምትጠይቅበት ዘዴ የትኛውም ቢሆን በሚገባ የታሰበባቸውን ቃላት ተጠቀም።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የጻድቅ ልብ፣ መልስ ከመስጠቱ በፊት ያሰላስላል።”—ምሳሌ 15:28

  •   ሳትዘገይ ይቅርታ ጠይቅ። አለመግባባቱ ሳይፈታ በቆየ መጠን ችግሩ እየከረረ ሊሄድ እንዲሁም ካስቀየምከው ግለሰብ ጋር ያለህ ግንኙነት ይበልጥ እየሻከረ ሊመጣ ይችላል።

     ጠቃሚ ምክር፦ ግብ አውጣ፤ ለምሳሌ ‘ዛሬ ይቅርታ እጠይቃለሁ’ የሚል ግብ ልታወጣ ትችላለህ። መቼ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብህ ወስን፤ ከዚያም ባወጣኸው የጊዜ ገደብ መሠረት ይቅርታ ጠይቅ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፈጥነህ ታረቅ።”—ማቴዎስ 5:25

  •   ከልብህ ይቅርታ ጠይቅ። “እንደዚያ ስለተሰማህ አዝናለሁ” ብትል ይቅርታ እንደጠየቅክ አይቆጠርም! ጃኔል የተባለች ወጣት “በአብዛኛው፣ የበደልከው ሰው ለጥፋትህ ኃላፊነት እንደወሰድክ ሲመለከት ያከብርሃል” ብላለች።

     ጠቃሚ ምክር፦ ይቅርታ ስትጠይቅ ቅድመ ሁኔታ አታስቀምጥ። “አንተ ላጠፋኸው ጥፋት ይቅርታ ከጠየቅክ እኔም ለጥፋቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ” የሚል መንፈስ አታንጸባርቅ።

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰላም የሚገኝበትን . . . ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።”—ሮም 14:19

a የሰው ንብረት ከጠፋብህ ወይም ከተበላሸብህ ይቅርታ ከመጠየቅ ባለፈ ንብረቱን ለመተካት ወይም ለማስተካከል እርምጃ ብትወስድ የተሻለ ይሆናል።