በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጓደኝነት ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጓደኝነት ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ጓደኝነት በሕይወታችን ደስተኛና ስኬታማ እንድንሆን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። ጥሩ ጓደኞች በጎ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል፤ እንዲሁም የተሻልን ሰዎች እንድንሆን ይረዱናል።—ምሳሌ 27:17

 እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ጓደኞቻችንን በጥንቃቄ መምረጣችን አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ይገልጻል። መጥፎ ጓደኞች መያዝ ለችግር ሊዳርግ እንደሚችል ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) እንዲህ ያሉት ጓደኞች የሞኝነት አካሄድ እንድንከተል ሊያደርጉን ወይም መልካም ባሕርያታችንን ሊያበላሹብን ይችላሉ።

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ጥሩ ጓደኛ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው?

 ሁለት ሰዎች፣ የሚወዷቸው ወይም የሚያስደስቷቸው ነገሮች ተመሳሳይ መሆናቸው ብቻውን ለጥሩ ጓደኝነት መሠረት እንደማይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 119:63 “አንተን a ለሚፈሩ ሁሉ፣ መመሪያዎችህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ” ይላል። የዚህ ጥቅስ ጸሐፊ ጓደኛ አድርጎ የመረጠው አምላክን ላለማሳዘን የሚፈሩና በአምላክ መሥፈርቶች የመመራት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች እንደሆነ ልብ እንበል።

 መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ጓደኛ ሊኖሩት የሚገቡትን ባሕርያትም ይጠቅሳል። ለምሳሌ፦

  •   “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17

  •   “እርስ በርስ ከመጠፋፋት ወደኋላ የማይሉ ጓደኛሞች አሉ፤ ነገር ግን ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ።”—ምሳሌ 18:24

 እነዚህ ጥቅሶች እንደሚገልጹት ጥሩ ጓደኛ ታማኝ፣ አፍቃሪ፣ ደግ እና ለጋስ ነው። እውነተኛ ጓደኛ በሕይወታችን ውስጥ ውጣ ውረዶች ሲያጋጥሙን እንደሚረዳን የምንተማመንበት ሰው ነው። በተጨማሪም እውነተኛ ጓደኛ በተሳሳተ ጎዳና እየሄድን እንደሆነ ወይም መጥፎ ውሳኔ ልናደርግ እንደሆነ ካስተዋለ በድፍረት ከመናገር ወደኋላ አይልም።—ምሳሌ 27:6, 9

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ጥሩ ጓደኛሞች እነማን ናቸው?

 መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ዕድሜ፣ አስተዳደግ፣ ባሕል እና ሥልጣን ቢኖራቸውም ጥሩ ጓደኝነት መመሥረት ስለቻሉ ሰዎች ይናገራል። ሦስት ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

  •   ሩት እና ናኦሚ። ሩት የናኦሚ ምራት ነበረች፤ በመካከላቸው ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ሳይኖር አይቀርም። በተጨማሪም ሩትና ናኦሚ ባሕላቸው በጣም የተለያየ ነበር። እነዚህ ልዩነቶች ቢኖሩም በጣም የሚዋደዱና የሚቀራረቡ ጓደኛሞች ሆነዋል።—ሩት 1:16

  •   ዳዊት እና ዮናታን። ዮናታን ዳዊትን በ30 ዓመት ገደማ ሳይበልጠው አይቀርም፤ ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ “ዮናታንና ዳዊት የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ” ይላል።—1 ሳሙኤል 18:1

  •   ኢየሱስ እና ሐዋርያቱ። ኢየሱስ መምህር እና ጌታ እንደመሆኑ መጠን ለሐዋርያቱ የበላያቸው ነበር። (ዮሐንስ 13:13) ሆኖም የእሱ ጓደኞች ለመሆን እንደማይበቁ አድርጎ አልተመለከታቸውም። ከዚህ ይልቅ ትምህርቶቹን ከሚከተሉ ሰዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው። “ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ” ብሏል።—ዮሐንስ 15:14, 15

 የአምላክ ወዳጅ መሆን ይቻላል?

 አዎ፣ ሰዎች የአምላክ ወዳጅ መሆን ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ከቅኖች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አለው’ ይላል። (ምሳሌ 3:32) ይህም ሲባል አምላክ፣ ሥርዓታማና ሐቀኛ ለመሆን እንዲሁም ትክክል ወይም ስህተት የሆኑ ነገሮችን በተመለከተ የእሱን መሥፈርቶች ለመከተል ከሚጥሩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ይመሠርታል ማለት ነው። ለምሳሌ ታማኝ ሰው የነበረው አብርሃም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘የአምላክ ወዳጅ’ ተብሎ ተጠርቷል።—2 ዜና መዋዕል 20:7፤ ኢሳይያስ 41:8፤ ያዕቆብ 2:23

a የዚህ መዝሙር አውድ እንደሚያሳየው በዚህ ጥቅስ ላይ “አንተ” የሚለው የሚያመለክተው አምላክን ነው።