ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 5:1-14

  • ኢየሱስ ከሰብዓዊ ሊቀ ካህናት ሁሉ የላቀ ነው (1-10)

    • “ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ” (6, 10)

    • “ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ” (8)

    • “ዘላለማዊ መዳን እንዲያገኙ ምክንያት ሆነላቸው” (9)

  • ‘ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ነው’ (11-14)

5  ከሰዎች መካከል የተመረጠ እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት ለኃጢአት መባና መሥዋዕት ያቀርብ ዘንድ+ እነሱን በመወከል የአምላክን አገልግሎት ለማከናወን ይሾማል።+  እሱ ራሱ ድክመት ስላለበት* አላዋቂ የሆኑትንና የሚሳሳቱትን* በርኅራኄ* ሊይዛቸው ይችላል፤  በዚህም የተነሳ ለሕዝቡ የኃጢአት መባ እንደሚያቀርብ ሁሉ ለራሱም ለማቅረብ ይገደዳል።+  አንድ ሰው ይህን የክብር ቦታ የሚያገኘው እንደ አሮን፣ አምላክ ሲጠራው ብቻ ነው እንጂ በራሱ ፈቃድ አይደለም።+  ክርስቶስም ሊቀ ካህናት በመሆን ራሱን ከፍ ከፍ አላደረገም፤+ ከዚህ ይልቅ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድኩህ”+ ብሎ ስለ እሱ የተናገረው፣ ከፍ ከፍ አደረገው።  ደግሞም በሌላ ቦታ ላይ “እንደ መልከጼዴቅ፣ አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ብሏል።+  ክርስቶስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን* ከሞት ሊያድነው ለሚችለው በከፍተኛ ጩኸትና እንባ ብዙ ምልጃና ልመና አቀረበ፤+ አምላካዊ ፍርሃት ስለነበረውም ጸሎቱ ተሰማለት።  ልጅ ቢሆንም እንኳ ከደረሰበት መከራ መታዘዝን ተማረ።+  በዚህም ፍጹም ከሆነ በኋላ+ የሚታዘዙት ሁሉ ዘላለማዊ መዳን እንዲያገኙ ምክንያት ሆነላቸው፤+ 10  ምክንያቱም ከመልከጼዴቅ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ አምላክ ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾሞታል።+ 11  እሱን በተመለከተ ብዙ የምንናገረው ነገር አለን፤ ይሁንና ጆሯችሁ ስለደነዘዘ ለማስረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። 12  በአሁኑ ጊዜ* አስተማሪዎች ልትሆኑ ይገባችሁ የነበረ ቢሆንም የአምላክን ቅዱስ መልእክት መሠረታዊ ነገሮች እንደገና ከመጀመሪያ ጀምሮ የሚያስተምራችሁ ሰው ትፈልጋላችሁ፤+ ደግሞም ጠንካራ ምግብ ከመመገብ ይልቅ እንደገና ወተት መፈለግ ጀምራችኋል። 13  ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ ከጽድቅ ቃል ጋር ትውውቅ የለውም።+ 14  ጠንካራ ምግብ ግን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት ላሠለጠኑ* ጎልማሳ ሰዎች ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለድክመት የተጋለጠ ስለሆነ።”
ወይም “በሥርዓት የማይሄዱትን።”
ወይም “በደግነት፤ በአግባቡ።”
ቃል በቃል “በሥጋው ቀናት።”
ቃል በቃል “ከጊዜው አንጻር።”
የግሪክኛው ቃል የጅምናስቲክ ስፖርተኛ የሚወስደውን ዓይነት ሥልጠና ያመለክታል።