ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 6:1-18

  • አንዳችሁ የሌላውን ሸክም ተሸከሙ (1-10)

    • ሰው የዘራውን ያጭዳል (7, 8)

  • መገረዝ አስፈላጊ አይደለም (11-16)

    • አዲስ ፍጥረት (15)

  • መደምደሚያ (17, 18)

6  ወንድሞች፣ አንድ ሰው ሳያውቅ የተሳሳተ ጎዳና ቢከተል መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ እናንተ እንዲህ ዓይነቱን ሰው በገርነት* መንፈስ ለማስተካከል ጥረት አድርጉ።+ ይሁንና እናንተም ፈተና ላይ እንዳትወድቁ+ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።+  አንዳችሁ የሌላውን ከባድ ሸክም ተሸከሙ፤+ በዚህ መንገድ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ።+  አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ+ ራሱን እያታለለ ነው።  ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤+ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር+ ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።  እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማልና።+  ከዚህም በተጨማሪ ቃሉን በመማር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው፣ ይህን ትምህርት* ከሚያስተምረው ሰው ጋር መልካም ነገሮችን ሁሉ ይካፈል።+  አትታለሉ፤ አምላክ አይዘበትበትም። አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል፤+  ምክንያቱም ለሥጋው ብሎ የሚዘራ ከሥጋው መበስበስን ያጭዳል፤ ለመንፈስ ብሎ የሚዘራ ግን ከመንፈስ የዘላለም ሕይወት ያጭዳል።+  ካልታከትን* ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።+ 10  እንግዲያው ይህን ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ* እስካገኘን ድረስ ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም እናድርግ። 11  በራሴ እጅ እንዴት ባሉ ትላልቅ ፊደላት እንደጻፍኩላችሁ ተመልከቱ። 12  በሥጋ ተቀባይነት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ* እንድትገረዙ ሊያስገድዷችሁ ይሞክራሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን በክርስቶስ የመከራ እንጨት* ሳቢያ ስደት እንዳይደርስባቸው ነው። 13  እነሱ እንድትገረዙ የሚፈልጉት በእናንተ ሥጋ ለመኩራራት ብለው ነው እንጂ የተገረዙት ራሳቸውም እንኳ ሕጉን አይጠብቁም።+ 14  ይሁንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመከራ እንጨት* ካልሆነ በስተቀር በሌላ ነገር ፈጽሞ መኩራራት አልፈልግም፤+ በእሱ የተነሳ፣ በእኔ አመለካከት ዓለም ሞቷል፤* በዓለም አመለካከት ደግሞ እኔ ሞቻለሁ።* 15  መገረዝም ሆነ አለመገረዝ ምንም አይጠቅምም፤+ ከዚህ ይልቅ የሚጠቅመው አዲስ ፍጥረት መሆን ነው።+ 16  ይህን የሥነ ምግባር ደንብ በመከተል በሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ይኸውም በአምላክ እስራኤል+ ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን። 17  የኢየሱስ ባሪያ መሆኔን የሚያሳይ መለያ ምልክት በሰውነቴ ላይ ስላለ+ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም አያስቸግረኝ። 18  ወንድሞች፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከምታሳዩት መንፈስ ጋር ይሁን። አሜን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሸካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ይህን የቃል ትምህርት።”
ወይም “ተስፋ ካልቆረጥን።”
ቃል በቃል “የተቀጠረ ጊዜ።”
ወይም “ከውጭ ሲያዩአቸው ጥሩ መስለው መታየት የሚፈልጉ ሁሉ።”
ወይም “በእንጨት ላይ ተሰቅሏል።”
ወይም “በእንጨት ላይ ተሰቅያለሁ።”