ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 5:1-26

  • ክርስቲያናዊ ነፃነት (1-15)

  • በመንፈስ መመላለስ (16-26)

    • የሥጋ ሥራዎች (19-21)

    • የመንፈስ ፍሬ (22, 23)

5  ክርስቶስ ነፃ ያወጣን እንዲህ ዓይነት ነፃነት እንድናገኝ ነው። ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤+ ዳግመኛ ራሳችሁን በባርነት ቀንበር አታስጠምዱ።+  እኔ ጳውሎስ፣ የምትገረዙ ከሆነ ክርስቶስ ለእናንተ ምንም እንደማይጠቅማችሁ አሳውቃችኋለሁ።+  የሚገረዝ እያንዳንዱ ሰው መላውን ሕግ የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ዳግመኛ አሳስበዋለሁ።+  እናንተ በሕግ አማካኝነት ለመጽደቅ ስለምትጥሩ ከክርስቶስ ተለይታችኋል፤+ ከጸጋውም ርቃችኋል።  እኛ ግን ተስፋ የምናደርገውን በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ በመንፈስ አማካኝነት በጉጉት እንጠባበቃለን።  ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ላላቸው በፍቅር የሚመራ እምነት እንጂ መገረዝ ወይም አለመገረዝ ፋይዳ የለውም።+  በአግባቡ ትሮጡ ነበር፤+ ታዲያ ለእውነት መታዘዛችሁን እንዳትቀጥሉ እንቅፋት የሆነባችሁ ማን ነው?  እንዲህ ያለው ማግባቢያ እየጠራችሁ ካለው የመጣ አይደለም።  ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።+ 10  ከጌታ ጋር አንድነት ያላችሁ ሁሉ+ የተለየ ሐሳብ እንደማይኖራችሁ እተማመናለሁ፤ ሆኖም እያወካችሁ+ ያለው ማንም ይሁን ማን የሚገባውን ፍርድ ይቀበላል። 11  ወንድሞች፣ እኔ አሁንም ስለ መገረዝ እየሰበክሁ ከሆነ እስካሁን ለምን ስደት ይደርስብኛል? እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ የመከራው እንጨት* እንቅፋት+ መሆኑ በቀረ ነበር። 12  ሊያውኳችሁ እየሞከሩ ያሉት ሰዎች ከናካቴው ቢሰለቡ* ደስታዬ ነው። 13  ወንድሞች፣ የተጠራችሁት ነፃ እንድትወጡ ነው፤ ብቻ ይህን ነፃነት የሥጋን ፍላጎት ለማርካት አትጠቀሙበት፤+ ይልቁንም አንዳችሁ ሌላውን በፍቅር አገልግሉ።+ 14  መላው ሕግ “ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ” በሚለው አንድ ትእዛዝ ተፈጽሟልና።*+ 15  ይሁንና እርስ በርሳችሁ መነካከሳችሁንና መባላታችሁን ካልተዋችሁ+ እርስ በርስ ልትጠፋፉ ስለምትችሉ ተጠንቀቁ።+ 16  እኔ ግን በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ እላለሁ፤+ እንዲህ ካደረጋችሁ የሥጋን ምኞት ከቶ አትፈጽሙም።+ 17  የሥጋ ፍላጎት ከመንፈስ ፍላጎት ጋር፣ የመንፈስ ፍላጎት ደግሞ ከሥጋ ፍላጎት ጋር አይጣጣምም፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ይቃረናሉ። ስለሆነም ማድረግ የምትፈልጉትን አታደርጉም።+ 18  በተጨማሪም በመንፈስ የምትመሩ ከሆነ በሕግ ሥር አይደላችሁም። 19  የሥጋ ሥራዎች በግልጽ የታወቁ ናቸው፤ እነሱም፦ የፆታ ብልግና፣*+ ርኩሰት፣ ማንአለብኝነት፣*+ 20  ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣*+ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ ጭቅጭቅ፣ መከፋፈል፣ መናፍቅነት፣ 21  ምቀኝነት፣ ሰካራምነት፣+ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያና እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው።+ እነዚህን በተመለከተ አስቀድሜ እንዳስጠነቀቅኳችሁ ሁሉ አሁንም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ* የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።+ 22  በሌላ በኩል ግን የመንፈስ ፍሬ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣+ እምነት፣ 23  ገርነት፣* ራስን መግዛት ነው።+ እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚከለክል ሕግ የለም። 24  ከዚህም በተጨማሪ የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከመጥፎ ምኞቱና ፍላጎቱ ጋር በእንጨት ላይ ቸንክረውታል።*+ 25  በመንፈስ የምንኖር ከሆነ መንፈስ የሚሰጠንን አመራር በመከተል ምንጊዜም በሥርዓት እንመላለስ።+ 26  በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና+ አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ጃንደረባ ቢሆኑ።” እንዲህ መሆናቸው የሚደግፉትን ሕግ ለመፈጸም ብቃት እንዳይኖራቸው ያደርጋቸዋል።
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
“ተጠቃሏልና” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ጥንቆላ፤ መድኃኒተኝነት።”
እንዲህ ያሉ ነገሮችን የመሥራት ልማድ ያላቸውን ያመለክታል።
“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሸካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ገድለውታል።”