በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ፍላጎትን ማርካትን ይከለክላል?

መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ፍላጎትን ማርካትን ይከለክላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ የፆታ ፍላጎትን ማርካትን አይከለክልም፤ ከዚህ ይልቅ የፆታ ግንኙነት አምላክ ለባለትዳሮች የሰጠው ስጦታ እንደሆነ ይገልጻል። አምላክ ሰዎችን የፈጠራቸው “ወንድና ሴት አድርጎ” ሲሆን ይህም “እጅግ መልካም” እንደሆነ ገልጿል። (ዘፍጥረት 1:27, 31) የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት በጋብቻ ሲያጣምር ሁለቱም “አንድ ሥጋ” እንደሚሆኑ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 2:24) ይህ ጥምረት የፆታ ፍላጎትን ማርካትንና እርስ በርስ የጠበቀ ግንኙነት መመሥረትን ያካትታል።

 መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች ከትዳር ስለሚያገኙት እርካታ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ። . . . ጡቶቿ ዘወትር ያርኩህ፤ ፍቅሯም ሁልጊዜ ይማርክህ።” (ምሳሌ 5:18, 19) አምላክ ሚስቶችም ከፆታ ግንኙነት እርካታ እንዲያገኙ ይፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ባልና ሚስት አንዳቸው የሌላውን የፆታ ፍላጎት ማርካት አለባቸው።”​—1 ቆሮንቶስ 7:3 ጎድስ ዎርድ ባይብል

የፆታ ፍላጎትን ከማርካት ጋር በተያያዘ ገደብ ማበጀት

 አምላክ የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ የፈቀደው የተጋቡ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ በዕብራውያን 13:4 ላይ ገልጿል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር፣ መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን፤ ምክንያቱም አምላክ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋል።” ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ መሆን የሚጠበቅባቸው ሲሆን የገቡትን ቃል ማክበርም ይኖርባቸዋል። ደስታ የሚያገኙት የራስ ወዳድነት ምኞትን በማራመድ ሳይሆን “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በሥራ ላይ በማዋል ነው።​—የሐዋርያት ሥራ 20:35