መዝሙር 94:1-23

  • አምላክ የበቀል እርምጃ እንዲወስድ የቀረበ ጸሎት

    • “ክፉዎች እስከ መቼ ድረስ ይፈነጥዛሉ?” (3)

    • ያህ የሚሰጠው እርማት ደስታ ያስገኛል (12)

    • ‘አምላክ ሕዝቡን አይጥልም’ (14)

    • ‘በሕግ ስም ችግር መፍጠር’ (20)

94  የበቀል አምላክ፣ ይሖዋ ሆይ፣+የበቀል አምላክ ሆይ፣ ብርሃንህን አብራ!   የምድር ፈራጅ ሆይ፣ ተነስ።+ ለትዕቢተኞች የሚገባቸውን ብድራት ክፈላቸው።+   ክፉዎች እስከ መቼ፣ ይሖዋ ሆይ፣ክፉዎች እስከ መቼ ድረስ ይፈነጥዛሉ?+   ይለፈልፋሉ፤ በእብሪት ይናገራሉ፤ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ስለ ራሳቸው ጉራ ይነዛሉ።   ይሖዋ ሆይ፣ ሕዝብህን ያደቃሉ፤+ርስትህንም ይጨቁናሉ።   መበለቲቱንና ባዕዱን ሰው ይገድላሉ፤አባት የሌላቸውንም ልጆች ሕይወት ያጠፋሉ።   “ያህ አያይም፤+የያዕቆብ አምላክ አያስተውለውም” ይላሉ።+   እናንተ ማመዛዘን የጎደላችሁ ሰዎች፣ ይህን ልብ በሉ፤እናንተ ሞኞች፣ አስተዋዮች የምትሆኑት መቼ ነው?+   ጆሮን ያበጀው* እሱ መስማት አይችልም? ወይስ ዓይንን የሠራው እሱ ማየት አይችልም?+ 10  ብሔራትን የሚያርመው እሱ መውቀስ አይችልም?+ ለሰዎች እውቀት የሚሰጠው እሱ ነው!+ 11  ይሖዋ የሰዎችን ሐሳብ ያውቃል፤ከንቱ እንደሆነም ይረዳል።+ 12  ያህ ሆይ፣ አንተ የምታርመው፣+ከሕግህ ላይ የምታስተምረው ሰው ደስተኛ ነው፤+ 13  ይህም ለክፉዎች ጉድጓድ እስኪቆፈር ድረስ፣+በመከራ ወቅት ለእሱ ሰላም ትሰጠው ዘንድ ነው። 14  ይሖዋ ሕዝቡን አይጥልምና፤+ርስቱንም አይተውም።+ 15  ፍርድ፣ ዳግመኛ ጽድቅ የሚንጸባረቅበት ይሆናልና፤ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችም ሁሉ ይከተሉታል። 16  ከክፉዎች ጋር የሚሟገትልኝ ማን ነው? ክፉ አድራጊዎችን በመቃወም ከጎኔ የሚቆም ማን ነው? 17  ይሖዋ ረዳቴ ባይሆን ኖሮ፣በአጭር ጊዜ ውስጥ በጠፋሁ ነበር።*+ 18  “እግሬ አዳለጠኝ” ባልኩ ጊዜ፣ ይሖዋ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርህ ደገፈኝ።+ 19  በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣*አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።*+ 20  ምግባረ ብልሹ ገዢዎች* በሕግ ስም* ችግር ለመፍጠር እያሴሩ፣+የአንተ ተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ? 21  በጻድቁ ላይ* ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ይሰነዝራሉ፤+በንጹሕ ሰው ላይ ሞት ይፈርዳሉ።*+ 22  ለእኔ ግን ይሖዋ አስተማማኝ መጠጊያ ይሆንልኛል፤አምላኬ መጠጊያ ዓለቴ ነው።+ 23  ክፉ ሥራቸውን በላያቸው ይመልሳል፤+ በገዛ ክፋታቸው ያጠፋቸዋል።* ይሖዋ አምላካችን ያጠፋቸዋል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የተከለው።”
ቃል በቃል “ነፍሴ በዝምታ በኖረች ነበር።”
ወይም “እረፍት የሚነሱ ሐሳቦች በውስጤ በበዙ ጊዜ።”
ወይም “ማጽናኛዎችህ ነፍሴን አረጋጓት።”
ወይም “በአዋጅ።”
ወይም “ፈራጆች።” ቃል በቃል “ዙፋን።”
ወይም “በጻድቁ ነፍስ ላይ።”
ቃል በቃል “የንጹሑንም ሰው ደም በደለኛ (ክፉ) ያደርጉታል።”
ቃል በቃል “ጸጥ ያሰኛቸዋል።”