ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 16:1-24

  • በኢየሩሳሌም ላሉ ክርስቲያኖች መዋጮ ማሰባሰብ (1-4)

  • የጳውሎስ የጉዞ ዕቅድ (5-9)

  • ጢሞቴዎስና አጵሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሊመጡ እንደሚችሉ ተነገረ (10-12)

  • ማሳሰቢያዎችና ሰላምታዎች (13-24)

16  ለቅዱሳን መዋጮ ማሰባሰብን በተመለከተ+ ደግሞ በገላትያ ለሚገኙ ጉባኤዎች የሰጠሁትን መመሪያ መከተል ትችላላችሁ።  መዋጮ የሚሰባሰበው እኔ በምመጣበት ጊዜ እንዳይሆን ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን አቅሙ በሚፈቅድለት መጠን የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጥ።  ስመጣም የመረጣችኋቸውንና የድጋፍ ደብዳቤ የጻፋችሁላቸውን ሰዎች+ የልግስና ስጦታችሁን ኢየሩሳሌም እንዲያደርሱ እልካቸዋለሁ።  ይሁን እንጂ የእኔም መሄድ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አብረውኝ ይሄዳሉ።  ይሁንና በመቄዶንያ በኩል ማለፌ ስለማይቀር በዚያ ሳልፍ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤+  ወደምሄድበትም ቦታ የተወሰነ መንገድ እንድትሸኙኝ ምናልባት እናንተ ጋ ልቆይ እችላለሁ፤ እንዲያውም ክረምቱን ከእናንተ ጋር አሳልፍ ይሆናል።  ይሖዋ* ቢፈቅድ ከእናንተ ጋር የተወሰነ ጊዜ አሳልፋለሁ ብዬ ተስፋ ስለማደርግ አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ላያችሁ አልፈልግም።+  ይሁንና እስከ ጴንጤቆስጤ በዓል ድረስ በኤፌሶን+ እቆያለሁ፤  ምክንያቱም ትልቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤+ ሆኖም ብዙ ተቃዋሚዎች አሉ። 10  ጢሞቴዎስ+ ከመጣ በመካከላችሁ በሚቆይበት ጊዜ ፍርሃት እንዳይሰማው ተባበሩት፤ እሱም እንደ እኔ የይሖዋን* ሥራ የሚሠራ ነውና።+ 11  ስለዚህ ማንም አይናቀው። ከወንድሞች ጋር እየጠበቅኩት ስለሆነ ወደ እኔ እንዲመጣ በሰላም ሸኙት። 12  ወንድማችንን አጵሎስን+ በተመለከተ ደግሞ ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ አጥብቄ ለምኜው ነበር። እሱ አሁን የመምጣት ሐሳብ የለውም፤ ሆኖም ሁኔታው ሲመቻችለት ይመጣል። 13  ነቅታችሁ ኑሩ፤+ በእምነት ጸንታችሁ ቁሙ፤+ ወንድ ሁኑ፤*+ ብርቱዎች ሁኑ።+ 14  የምታደርጉትን ነገር ሁሉ በፍቅር አድርጉ።+ 15  እንግዲህ ወንድሞች ይህን አሳስባችኋለሁ፦ የእስጢፋናስ ቤተሰብ በአካይያ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት* እንደሆኑና ቅዱሳንን ለማገልገል ራሳቸውን እንደሰጡ ታውቃላችሁ። 16  እናንተም እንደ እነሱ ላሉት እንዲሁም ከእኛ ጋር ለሚተባበሩትና በትጋት ለሚሠሩት ሁሉ ተገዙ።+ 17  እስጢፋናስ+ እና ፈርጡናጦስ እንዲሁም አካይቆስ እዚህ በመገኘታቸው እጅግ ተደስቻለሁ፤ ምክንያቱም የእናንተ እዚህ አለመኖር በእነሱ ተካክሷል። 18  እነሱ የእኔንም ሆነ የእናንተን መንፈስ አድሰዋልና። ስለዚህ እንዲህ ላሉት ሰዎች እውቅና ስጡ። 19  በእስያ ያሉ ጉባኤዎች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ እንዲሁም በቤታቸው ያለው ጉባኤ+ ሞቅ ያለ ክርስቲያናዊ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 20  ወንድሞች ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። እርስ በርሳችሁ በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ። 21  እኔ ጳውሎስ በገዛ እጄ የጻፍኩላችሁ ሰላምታ ይድረሳችሁ። 22  ጌታን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፣ ና! 23  የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። 24  የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሆናችሁ ሁሉ፣ ፍቅሬ ይድረሳችሁ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ደፋሮች ሁኑ።”
ቃል በቃል “የአካይያ በኩራት።”