ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 2:1-16

  • ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሰበከ (1-5)

  • የአምላክ ጥበብ ያለው ብልጫ (6-10)

  • የመንፈሳዊ ሰውና የዓለማዊ ሰው ልዩነት (11-16)

2  ስለዚህ ወንድሞች፣ የአምላክን ቅዱስ ሚስጥር+ ለእናንተ ለመግለጽ በመጣሁ ጊዜ በንግግር ችሎታ+ ወይም በጥበብ እናንተን ለማስደመም አልሞከርኩም።  ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ትኩረቴን በኢየሱስ ክርስቶስና በእሱ መሰቀል ላይ ብቻ ለማድረግ ወስኜ ነበርና።+  ወደ እናንተም የመጣሁት ደካማ ሆኜ እንዲሁም በፍርሃትና እጅግ በመንቀጥቀጥ ነበር፤  ንግግሬም ሆነ የሰበክሁላችሁ መልእክት የሚያባብል የጥበብ ቃል አልነበረም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንፈስና ኃይል የሚያሳይ ነበር፤+  ይኸውም እምነታችሁ በአምላክ ኃይል ላይ እንጂ በሰው ጥበብ ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን ነው።  በመሆኑም በጎለመሱት+ መካከል ስለ ጥበብ እንናገራለን፤ ሆኖም የምንናገረው የዚህን ሥርዓት* ጥበብ ወይም የሚጠፉትን የዚህን ሥርዓት ገዢዎች+ ጥበብ አይደለም።  ከዚህ ይልቅ የምንናገረው በቅዱስ ሚስጥር+ የተገለጠውን የአምላክ ጥበብ ይኸውም አምላክ ለእኛ ክብር ከዘመናት በፊት* አስቀድሞ የወሰነውን የተሰወረ ጥበብ ነው።  ይህን ጥበብ ከዚህ ሥርዓት* ገዢዎች መካከል አንዳቸውም አላወቁትም፤+ ቢያውቁትማ ኖሮ ታላቅ ክብር ያለውን ጌታ ባልሰቀሉት* ነበር።  ይሁንና “አምላክ ለሚወዱት ያዘጋጃቸውን ነገሮች ዓይን አላየም፣ ጆሮም አልሰማም፣ የሰውም ልብ አላሰበም” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+ 10  አምላክ እነዚህን ነገሮች በመንፈሱ+ አማካኝነት የገለጠው ለእኛ ነውና፤+ ምክንያቱም መንፈስ ሁሉንም ነገሮች አልፎ ተርፎም የአምላክን ጥልቅ ነገሮች ይመረምራል።+ 11  ከሰዎች መካከል በአንድ ሰው ውስጥ ያለውን ነገር በውስጡ ካለው የሰውየው መንፈስ በቀር ማን ሊያውቅ ይችላል? በተመሳሳይም በአምላክ ውስጥ ያለውን ነገር ከአምላክ መንፈስ በቀር ማንም አያውቅም። 12  እኛ አምላክ በደግነት የሰጠንን ነገሮች ማወቅ እንድንችል ከአምላክ የሆነውን መንፈስ+ ተቀበልን እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። 13  ደግሞም እነዚህን ነገሮች እንናገራለን፤ የምንናገረው ግን ከሰው ጥበብ+ በተማርነው ቃል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በመንፈሳዊ ቃል ስናብራራ* ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን።+ 14  ዓለማዊ ሰው ግን ከአምላክ መንፈስ የሆኑትን ነገሮች አይቀበልም፤ እንዲህ ያሉት ነገሮች ለእሱ ሞኝነት ናቸውና፤ በመንፈስ የሚመረመሩ ስለሆኑም ሊረዳቸው አይችልም። 15  ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ሰው ሁሉንም ነገር ይመረምራል፤+ እሱ ራሱ ግን በማንም ሰው አይመረመርም። 16  “ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን* አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?” ተብሏልና፤+ እኛ ግን የክርስቶስ አስተሳሰብ አለን።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የዚህን ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ከዓለም ሥርዓቶች በፊት።”
ወይም “በእንጨት ላይ ባልሰቀሉት።”
ወይም “ከዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ከመንፈሳዊ ቃላት ጋር በማዛመድ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።