ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 3:1-23

  • የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ገና ሥጋውያን ናቸው (1-4)

  • ‘የሚያሳድገው አምላክ ነው’ (5-9)

    • “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” (9)

  • እሳትን መቋቋም በሚችሉ ነገሮች መገንባት (10-15)

  • ‘የአምላክ ቤተ መቅደስ ናችሁ’ (16, 17)

  • የዓለም ጥበብ በአምላክ ዘንድ ሞኝነት ነው (18-23)

3  በመሆኑም ወንድሞች፣ ከክርስቶስ ጋር በተያያዘ ገና ሕፃናት+ እንደሆኑ እንደ ሥጋውያን ሰዎች እንጂ እንደ መንፈሳውያን ሰዎች+ ላነጋግራችሁ አልቻልኩም።  ጠንካራ ስላልነበራችሁ ወተት እንጂ ጠንካራ ምግብ አልመገብኳችሁም። አሁንም ቢሆን ገና አልጠነከራችሁም፤+  ደግሞም ገና ሥጋውያን ናችሁ።+ ቅናትና ጠብ በመካከላችሁ ስላለ ሥጋውያን መሆናችሁ፣+ ደግሞም በዓለም እንዳሉ ሰዎች መመላለሳችሁ አይደለም?  አንዱ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፣” ሌላው ደግሞ “እኔ የአጵሎስ+ ነኝ” ሲል እንደ ማንኛውም ሰው መሆናችሁ አይደለም?  ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ የሰጣቸውን ሥራ የሚያከናውኑ አገልጋዮች+ ናቸው፤ እናንተም አማኞች የሆናችሁት በእነሱ አማካኝነት ነው።  እኔ ተከልኩ፤+ አጵሎስ አጠጣ፤+ ያሳደገው ግን አምላክ ነው፤  ስለዚህ ምስጋና የሚገባው የሚያሳድገው አምላክ እንጂ የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው አይደለም።+  የሚተክለውም ሆነ የሚያጠጣው በኅብረት የሚሠሩ ናቸው፤* ሆኖም እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል።+  እኛ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። እናንተ በመልማት ላይ ያለ የአምላክ እርሻ ናችሁ፤ የአምላክ ሕንፃ ናችሁ።+ 10  በተሰጠኝ የአምላክ ጸጋ መሠረት በሙያው እንደተካነ ግንበኛ* እኔ መሠረት ጣልኩ፤+ ሌላው ደግሞ በዚያ ላይ ይገነባል። ሆኖም እያንዳንዱ በዚያ ላይ እንዴት እንደሚገነባ በጥንቃቄ ሊያስብ ይገባል። 11  ማንም ሰው ከተጣለው መሠረት ሌላ አዲስ መሠረት መጣል አይችልምና፤ ይህም መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።+ 12  ማንም በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮች፣ በእንጨት፣ በሣር ወይም በአገዳ ቢገነባ 13  የፈተናው ቀን ሲመጣ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ እሳቱ+ ሁሉንም ነገር ይገልጣልና፤ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው ምን ዓይነት ግንባታ እንዳከናወነ እሳቱ ራሱ ፈትኖ ያሳያል። 14  ማንም በመሠረቱ ላይ የገነባው ነገር ቢጸናለት ወሮታ ያገኛል፤ 15  ይሁንና ማንም ሰው የሠራው ሥራ ቢቃጠል ኪሳራ ይደርስበታል፤ እሱ ግን ይተርፋል፤ ሆኖም በእሳት ውስጥ አልፎ የመትረፍ ያህል ይሆናል። 16  እናንተ ራሳችሁ የአምላክ ቤተ መቅደስ+ እንደሆናችሁና የአምላክ መንፈስ በእናንተ ውስጥ እንደሚያድር አታውቁም?+ 17  ማንም የአምላክን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ አምላክ ያፈርሰዋል፤ የአምላክ ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ቤተ መቅደሱም እናንተ ናችሁ።+ 18  ማንም ራሱን አያታል፤ ከእናንተ መካከል ማንም በዚህ ሥርዓት* ጥበበኛ እንደሆነ ቢያስብ፣ ጥበበኛ መሆን ይችል ዘንድ ሞኝ ይሁን። 19  ምክንያቱም የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው፤ “ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኮል ይይዛቸዋል” ተብሎ ተጽፏልና።+ 20  ደግሞም “ይሖዋ* የጥበበኞች ሐሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል” ተብሏል።+ 21  በመሆኑም ማንም በሰዎች አይኩራራ፤ ሁሉም ነገር የእናንተ ነውና፤ 22  ጳውሎስም ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም*+ ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ የሚመጡትም ነገሮች ቢሆኑ ሁሉም ነገር የእናንተ ነው፤ 23  እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤+ ክርስቶስ ደግሞ የአምላክ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “አንድ ናቸው።” ወይም “አንድ ዓላማ አላቸው።”
ወይም “በሙያው እንደተካነ መሐንዲስ።”
ወይም “በዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።