ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 1:1-31

  • ሰላምታ (1-3)

  • ጳውሎስ በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተነሳ አምላክን አመሰገነ (4-9)

  • አንድነታቸውን እንዲጠብቁ የተሰጠ ማሳሰቢያ (10-17)

  • ክርስቶስ፣ የአምላክ ኃይልና ጥበብ (18-25)

  • “የሚኩራራ በይሖዋ ይኩራራ” (26-31)

1  በአምላክ ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ+ እንዲሆን ከተጠራው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከሶስቴንስ፣  በቆሮንቶስ ለሚገኘው የአምላክ ጉባኤ+ ይኸውም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባላችሁ አንድነት ለተቀደሳችሁ፣+ እንዲሁም የእነሱም ሆነ የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም+ በየስፍራው ሆነው ከሚጠሩ ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠራችሁ፦  ከአባታችን ከአምላክና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ በሰጠው ጸጋ የተነሳ አምላኬን ሁልጊዜ ስለ እናንተ አመሰግናለሁ፤  ምክንያቱም በሁሉም ነገር ይኸውም በመናገር ችሎታ ሁሉና በእውቀት ሁሉ በክርስቶስ በልጽጋችኋል፤+  ደግሞም ስለ ክርስቶስ የተሰጠው ምሥክርነት+ በእናንተ መካከል በሚገባ ሥር ሰዷል፤  ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጉጉት ስትጠባበቁ ማንኛውም ስጦታ ፈጽሞ አይጎድልባችሁም።+  በተጨማሪም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን+ ከማንኛውም ክስ ነፃ መሆን እንድትችሉ እስከ መጨረሻው ያጸናችኋል።  ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ* የጠራችሁ አምላክ ታማኝ ነው።+ 10  እንግዲህ ወንድሞች፣ ሁላችሁም ንግግራችሁ አንድ እንዲሆንና በመካከላችሁ መከፋፈል እንዳይኖር፣+ ከዚህ ይልቅ በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት እንዲኖራችሁ+ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጥብቄ አሳስባችኋለሁ። 11  ወንድሞቼ ሆይ፣ የቀሎኤ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አንዳንዶች በመካከላችሁ አለመግባባት እንዳለ ነግረውኛል። 12  ይኸውም እያንዳንዳችሁ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፣” “እኔ ግን የአጵሎስ+ ነኝ፣” “እኔ ደግሞ የኬፋ* ነኝ፣” “እኔ የክርስቶስ ነኝ” ትላላችሁ። 13  ታዲያ የክርስቶስ ጉባኤ ተከፋፍሏል ማለት ነው? ጳውሎስ ለእናንተ ሲል በእንጨት ላይ ተሰቅሏል እንዴ? ወይስ የተጠመቃችሁት በጳውሎስ ስም ነው? 14  ከቀርስጶስና+ ከጋይዮስ+ በስተቀር ከእናንተ አንዳችሁንም ባለማጥመቄ አምላክን አመሰግናለሁ፤ 15  በመሆኑም ከእናንተ መካከል በእኔ ስም እንደተጠመቀ ሊናገር የሚችል ማንም የለም። 16  እርግጥ የእስጢፋናስን+ ቤተሰብም አጥምቄአለሁ። ከእነዚህ ሌላ ግን ያጠመቅኩት ሰው መኖሩን አላስታውስም። 17  ክርስቶስ የላከኝ እንዳጠምቅ ሳይሆን ምሥራቹን እንዳውጅ ነው፤+ ደግሞም የክርስቶስ የመከራ እንጨት* ከንቱ እንዳይሆን ምሥራቹን የማውጀው በንግግር ጥበብ* አይደለም። 18  ስለ መከራው እንጨት* የሚነገረው መልእክት ወደ ጥፋት እያመሩ ላሉት ሞኝነት፣+ ወደ መዳን በሚወስደው ጎዳና ላይ ላለነው ለእኛ ግን የአምላክ ኃይል መገለጫ ነው።+ 19  “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የሊቃውንትንም ማስተዋል ወዲያ እጥላለሁ” ተብሎ ተጽፏልና።+ 20  የዚህ ሥርዓት* ጥበበኞች የት አሉ? ጸሐፍትስ* የት አሉ? ተሟጋቾችስ የት አሉ? አምላክ የዓለምን ጥበብ ሞኝነት አላደረገም? 21  ዓለም በራሱ ጥበብ+ አምላክን ሊያውቀው ስላልቻለ+ አምላክ በጥበቡ፣ እንደ ሞኝነት በሚቆጠረውና+ እየተሰበከ ባለው መልእክት አማካኝነት የሚያምኑትን ሰዎች ለማዳን መርጧል። 22  አይሁዳውያን ተአምራዊ ምልክቶች ማየት ይፈልጋሉ፤+ ግሪካውያን ደግሞ ጥበብን ይሻሉ፤ 23  እኛ ግን በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁዳውያን መሰናክል ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው።+ 24  ይሁን እንጂ ክርስቶስ ለተጠሩት፣ ለአይሁዳውያንም ሆነ ለግሪካውያን የአምላክ ኃይልና የአምላክ ጥበብ ነው።+ 25  ምክንያቱም የአምላክ ሞኝነት እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ነገር ከሰዎች ጥበብ ይበልጣል፤ የአምላክ ድክመት እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰበው ነገር ደግሞ ከሰዎች ብርታት ይበልጣል።+ 26  ወንድሞች፣ ከራሳችሁ ሁኔታ መረዳት እንደምትችሉት በሰብዓዊ አመለካከት* ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣+ ኃያላን የሆኑ ብዙዎች እንዲሁም ከትልቅ ቤተሰብ የተወለዱ ብዙዎች አልተጠሩም፤+ 27  ከዚህ ይልቅ አምላክ ጥበበኞችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱውንም ነገር ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤+ 28  አምላክ በሰዎች ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠውን ነገር ከንቱ ያደርግ ዘንድ በዚህ ዓለም ዝቅ ተደርጎ የሚታየውንና የተናቀውን ነገር ይኸውም ከንቱ መስሎ የሚታየውን ነገር መረጠ፤+ 29  ይህን ያደረገው ማንም ሰው* በአምላክ ፊት እንዳይኩራራ ነው። 30  ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድነት ሊኖራችሁ የቻለው በእሱ ምክንያት ነው፤ ክርስቶስ ደግሞ ለእኛ ከአምላክ የመጣ ጥበብ፣ ጽድቅና+ ቅድስና+ ሆኖልናል፤ እንዲሁም በቤዛው ነፃ አውጥቶናል፤+ 31  ይህም “የሚኩራራ በይሖዋ* ይኩራራ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ተካፋይ እንድትሆኑ።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “በአፈ ጮሌነት።”
ወይም “የዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ሕጉን ጠንቅቀው የተማሩ ሰዎችን ያመለክታል።
ቃል በቃል “በሥጋዊ መንገድ።”
ቃል በቃል “ሥጋ ሁሉ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።