የዮሐንስ ወንጌል 8:12-59

  • አብ ስለ ኢየሱስ ይመሠክራል (12-30)

    • ኢየሱስ፣ “የዓለም ብርሃን” (12)

  • የአብርሃም ልጆች (31-41)

    • ‘እውነት ነፃ ያወጣችኋል’ (32)

  • የዲያብሎስ ልጆች (42-47)

  • ኢየሱስና አብርሃም (48-59)

8  12  ደግሞም ኢየሱስ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።+ እኔን የሚከተል ሁሉ በምንም ዓይነት በጨለማ አይሄድም፤ ከዚህ ይልቅ የሕይወት ብርሃን ያገኛል።”+ 13  ፈሪሳውያንም “አንተ ስለ ራስህ ትመሠክራለህ፤ ምሥክርነትህም እውነት አይደለም” አሉት። 14  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “ስለ ራሴ ብመሠክር እንኳ ከየት እንደመጣሁና ወዴት እንደምሄድ ስለማውቅ+ ምሥክርነቴ እውነት ነው። እናንተ ግን ከየት እንደመጣሁና ወዴት እንደምሄድ አታውቁም። 15  እናንተ በሥጋዊ አስተሳሰብ* ትፈርዳላችሁ፤+ እኔ በማንም ላይ አልፈርድም። 16  እኔ ብፈርድ እንኳ ፍርዴ እውነተኛ ነው፤ ምክንያቱም የምፈርደው ብቻዬን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው።+ 17  በሕጋችሁም ላይ ‘የሁለት ሰዎች ምሥክርነት እውነት ነው’+ ተብሎ ተጽፏል። 18  ስለ ራሴ የምመሠክር አንዱ እኔ ነኝ፤ ደግሞም የላከኝ አብ ስለ እኔ ይመሠክራል።”+ 19  በዚህ ጊዜ “አባትህ የት ነው?” አሉት። ኢየሱስም “እናንተ እኔንም ሆነ አባቴን አታውቁም።+ እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር”+ ሲል መለሰላቸው። 20  ኢየሱስ ይህን የተናገረው በቤተ መቅደስ፣ ግምጃ ቤቱ+ አካባቢ ሆኖ ሲያስተምር ነበር። ሆኖም ሰዓቱ ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም።+ 21  ኢየሱስም እንደገና “እኔ እሄዳለሁ፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ይሁንና ኃጢአተኛ እንደሆናችሁ ትሞታላችሁ።+ እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም”+ አላቸው። 22  አይሁዳውያኑም “‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ የሚለው ራሱን ሊገድል አስቦ ይሆን እንዴ?” አሉ። 23  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ከምድር ናችሁ፤ እኔ ከላይ ነኝ።+ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፤ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። 24  በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ ያልኳችሁ ለዚህ ነው። እኔ እሱ እንደሆንኩ ካላመናችሁ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ።” 25  እነሱም “ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ድሮውንም እኔ ከእናንተ ጋር የምነጋገረው እንዲያው በከንቱ ነው። 26  ስለ እናንተ ብዙ የምናገረው ነገር አለኝ፤ ፍርድ የምሰጥበትም ብዙ ነገር አለኝ። በመሠረቱ የላከኝ እውነተኛ ነው፤ እኔም ከእሱ የሰማሁትን ያንኑ ነገር ለዓለም እየተናገርኩ ነው።”+ 27  እነሱ ግን ስለ አብ እየነገራቸው እንደሆነ አልተረዱም ነበር። 28  ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሰውን ልጅ ከሰቀላችሁት+ በኋላ እኔ እሱ+ እንደሆንኩና በራሴ ተነሳስቼ አንዳች ነገር እንደማላደርግ+ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ መሆኑን ታውቃላችሁ። 29  እኔን የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለማደርግ+ ብቻዬን አልተወኝም።” 30  ይህን በተናገረ ጊዜ ብዙዎች በእሱ አመኑ። 31  ከዚያም ኢየሱስ በእሱ ላመኑት አይሁዳውያን እንዲህ አለ፦ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ በእርግጥ ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ 32  እውነትንም ታውቃላችሁ፤+ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል።”+ 33  እነሱም መልሰው “እኛ የአብርሃም ዘር ነን፤ ለማንም ባሪያዎች ሆነን አናውቅም። ታዲያ አንተ ‘ነፃ ትወጣላችሁ’ እንዴት ትለናለህ?” አሉት። 34  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው።+ 35  ደግሞም ባሪያ በጌታው ቤት ለዘለቄታው አይኖርም፤ ልጅ ከሆነ ግን ሁልጊዜ ይኖራል። 36  ስለዚህ ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ። 37  የአብርሃም ዘር እንደሆናችሁ አውቃለሁ። ሆኖም ቃሌ በእናንተ ውስጥ ሥር ስለማይሰድ ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። 38  እኔ ከአባቴ ጋር ሳለሁ ያየሁትን ነገር እናገራለሁ፤+ እናንተ ግን ከአባታችሁ የሰማችሁትን ነገር ታደርጋላችሁ።” 39  እነሱም መልሰው “አባታችን አብርሃም ነው” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የአብርሃም ልጆች+ ብትሆኑ ኖሮ አብርሃም የሠራውን ትሠሩ ነበር። 40  እናንተ ግን ከአምላክ የሰማሁትን እውነት የነገርኳችሁን+ እኔን ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ። አብርሃም እንዲህ አላደረገም። 41  እናንተ እየሠራችሁ ያላችሁት የአባታችሁን ሥራ ነው።” እነሱም “እኛስ በዝሙት* የተወለድን አይደለንም፤ እኛ አንድ አባት አለን፤ እሱም አምላክ ነው” አሉት። 42  ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አምላክ አባታችሁ ቢሆን ኖሮ እኔ ወደዚህ የመጣሁት ከእሱ ዘንድ ስለሆነ በወደዳችሁኝ ነበር።+ እሱ ላከኝ እንጂ እኔ በራሴ ተነሳስቼ አልመጣሁም።+ 43  እየተናገርኩት ያለው ነገር የማይገባችሁ ለምንድን ነው? ቃሌን መስማት ስለማትችሉ ነው። 44  እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የአባታችሁንም ፍላጎት መፈጸም ትሻላችሁ።+ እሱ በራሱ መንገድ መሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ* ነፍሰ ገዳይ ነበር፤+ በእሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም። ውሸታምና የውሸት አባት ስለሆነ ውሸት ሲናገር ከራሱ አመንጭቶ ይናገራል።+ 45  በሌላ በኩል ግን እኔ እውነትን ስለምናገር አታምኑኝም። 46  ከመካከላችሁ እኔን ኃጢአት ሠርተሃል ብሎ በማስረጃ ሊወነጅለኝ የሚችል ማን ነው? የምናገረው እውነት ከሆነ ደግሞ የማታምኑኝ ለምንድን ነው? 47  ከአምላክ የሆነ የአምላክን ቃል ይሰማል።+ እናንተ ግን ከአምላክ ስላልሆናችሁ አትሰሙም።”+ 48  አይሁዳውያኑም መልሰው “‘አንተ ሳምራዊ+ ነህ፤ ደግሞም ጋኔን አድሮብሃል’+ ማለታችን ትክክል አይደለም?” አሉት። 49  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ አባቴን አከብራለሁ እንጂ ጋኔን የለብኝም፤ እናንተ ግን ታቃልሉኛላችሁ። 50  እኔ ለራሴ ክብር እየፈለግኩ አይደለም፤+ ይሁንና ይህን የሚፈልግና የሚፈርድ አለ። 51  እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ቃሌን የሚጠብቅ ከሆነ ፈጽሞ ሞትን አያይም።”+ 52  አይሁዳውያኑም እንዲህ አሉት፦ “አሁን በእርግጥ ጋኔን እንዳለብህ ተረዳን። አብርሃም ሞቷል፤ ነቢያትም ሞተዋል፤ አንተ ግን ‘ማንም ሰው ቃሌን የሚጠብቅ ከሆነ ፈጽሞ ሞትን አይቀምስም’ ትላለህ። 53   አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሃም ትበልጣለህ እንዴ? ነቢያትም ሞተዋል። ለመሆኑ አንተ ማን ነኝ ልትል ነው?” 54  ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እኔ ራሴን የማከብር ከሆነ ክብሬ ከንቱ ነው። እኔን የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን ነው የምትሉት አባቴ ነው።+ 55  ሆኖም እናንተ አላወቃችሁትም፤+ እኔ ግን አውቀዋለሁ።+ አላውቀውም ብል እንደ እናንተ ውሸታም መሆኔ ነው። ይሁንና እኔ አውቀዋለሁ፤ ቃሉንም እጠብቃለሁ። 56  አባታችሁ አብርሃም ቀኔን እንደሚያይ ተስፋ በማድረግ እጅግ ተደሰተ፤ አይቶትም ደስ ተሰኘ።”+ 57   አይሁዳውያኑም “አንተ ገና 50 ዓመት እንኳ ያልሞላህ፣ አብርሃምን አይቼዋለሁ ትላለህ?” አሉት። 58  ኢየሱስም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብርሃም ከመወለዱ በፊት እኔ ነበርኩ” አላቸው።+ 59  በዚህ ጊዜ ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ፤ ኢየሱስ ግን ተሰወረና ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ሄደ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በሰው መሥፈርት።”
ወይም “በፆታ ብልግና።” ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “እሱ ከመጀመሪያው አንስቶ።”