የዮሐንስ ወንጌል 20:1-31

  • መቃብሩ ባዶ ሆነ (1-10)

  • ኢየሱስ ለመግደላዊቷ ማርያም ተገለጠ (11-18)

  • ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠ (19-23)

  • ቶማስ ተጠራጠረ፤ በኋላ ግን አመነ (24-29)

  • የዚህ ጥቅልል ዓላማ (30, 31)

20  በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን መግደላዊቷ ማርያም በማለዳ፣ ገና ጨለማ ሳለ ወደ መቃብሩ መጣች፤+ መቃብሩ የተዘጋበትም ድንጋይ ተንከባሎ አየች።+  ስለዚህ ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር+ እየሮጠች መጥታ “ጌታን ከመቃብሩ ውስጥ ወስደውታል፤+ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው።  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወደ መቃብሩ አመሩ።  ሁለቱም አብረው ይሮጡ ጀመር፤ ሆኖም ሌላው ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን ቀድሞ በመሮጥ መቃብሩ ጋ ደረሰ።  ጎንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት የበፍታ ጨርቆቹ እዚያ ተቀምጠው አየ፤+ ወደ ውስጥ ግን አልገባም።  ከዚያም ስምዖን ጴጥሮስ ተከትሎት መጥቶ መቃብሩ ውስጥ ገባ። የበፍታ ጨርቆቹም በዚያ ተቀምጠው አየ።  በራሱ ላይ የነበረው ጨርቅ፣ ከመግነዝ ጨርቆቹ ጋር ሳይሆን ለብቻው ተጠቅልሎ አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ አየ።  ከዚያም ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደርሶ የነበረው ሌላው ደቀ መዝሙርም ወደ ውስጥ ገባ፤ እሱም አይቶ አመነ።  ከሞት መነሳት እንዳለበት የሚናገረውን የቅዱስ መጽሐፉን ቃል ገና አልተረዱም ነበር።+ 10  ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደየቤታቸው ተመልሰው ሄዱ። 11  ይሁን እንጂ ማርያም እዚያው መቃብሩ አጠገብ ቆማ ታለቅስ ነበር። እያለቀሰችም ወደ መቃብሩ ውስጥ ለማየት ጎንበስ አለች፤ 12  ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክትም+ የኢየሱስ አስከሬን አርፎበት በነበረው ቦታ አንዱ በራስጌው ሌላው በግርጌው ተቀምጠው አየች። 13  እነሱም “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ?” አሏት። እሷም “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” አለቻቸው። 14  ይህን ካለች በኋላ ዞር ስትል ኢየሱስን በዚያ ቆሞ አየችው፤ ነገር ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቀችም።+ 15  ኢየሱስም “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ? የምትፈልጊው ማንን ነው?” አላት። እሷም አትክልተኛው ስለመሰላት “ጌታዬ፣ አንተ ከዚህ ወስደኸው ከሆነ የት እንዳደረግከው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ” አለችው። 16  ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እሷም ዞር ብላ በዕብራይስጥ “ራቦኒ!” አለችው (ትርጉሙም “መምህር!” ማለት ነው)። 17  ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “ጥብቅ አድርገሽ አትያዥኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግኩምና። ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ+ ‘ወደ አባቴና+ ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና+ ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው’ ብለሽ ንገሪያቸው።” 18  መግደላዊቷ ማርያም መጥታ “ጌታን አየሁት!” ብላ ለደቀ መዛሙርቱ አበሰረቻቸው፤ እሱ ያላትንም ነገረቻቸው።+ 19  የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በነበረው በዚያው ቀን ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱ አይሁዳውያኑን* በመፍራታቸው በሮቹን ቆልፈው ተቀምጠው ሳለ ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው።+ 20  ይህን ካለ በኋላ እጆቹንና ጎኑን አሳያቸው።+ ደቀ መዛሙርቱም ጌታን በማየታቸው እጅግ ተደሰቱ።+ 21  ኢየሱስም ዳግመኛ “ሰላም ለእናንተ ይሁን።+ አብ እኔን እንደላከኝ፣+ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ”+ አላቸው። 22  ይህን ካለ በኋላ እፍ አለባቸውና እንዲህ አላቸው፦ “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ።+ 23  የማንንም ሰው ኃጢአት ይቅር ብትሉ ኃጢአቱ ይቅር ይባላል፤ ይቅር የማትሉት ሰው ሁሉ ደግሞ ኃጢአቱ እንዳለ ይጸናል።” 24  ይሁን እንጂ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ዲዲሞስ* የሚባለው ቶማስ+ ኢየሱስ በመጣበት ጊዜ አብሯቸው አልነበረም። 25  ስለዚህ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት “ጌታን አየነው!” አሉት። እሱ ግን “በእጆቹ ላይ ምስማሮቹ የተቸነከሩበትን ምልክት ካላየሁ እንዲሁም ጣቴን ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ካላስገባሁና እጄን በጎኑ ካላስገባሁ+ ፈጽሞ አላምንም” አላቸው። 26  እንደገናም ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም ከእነሱ ጋር ነበር። በሮቹ ተቆልፈው የነበሩ ቢሆንም ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አለ።+ 27  ከዚያም ቶማስን “ጣትህን እዚህ ክተት፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አስገባ። መጠራጠርህን* ተውና እመን” አለው። 28  ቶማስም መልሶ “ጌታዬ፣ አምላኬ!” አለው። 29  ኢየሱስ “ስላየኸኝ አመንክ? ሳያዩ የሚያምኑ ደስተኞች ናቸው” አለው። 30  እርግጥ ኢየሱስ በዚህ ጥቅልል ውስጥ ያልተጻፉ ሌሎች ብዙ ተአምራዊ ምልክቶችም በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል።+ 31  ሆኖም እነዚህ የተጻፉት ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ እንዲሁም የአምላክ ልጅ እንደሆነ እንድታምኑና በማመናችሁም በስሙ አማካኝነት ሕይወት እንዲኖራችሁ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

የአይሁዳውያን ሃይማኖታዊ መሪዎችን ያመለክታል።
ወይም “መንትያ።”
ቃል በቃል “አለማመንህን።”