የዮሐንስ ወንጌል 1:1-51

  • ‘ቃል ሥጋ ሆነ’ (1-18)

  • መጥምቁ ዮሐንስ የሰጠው ምሥክርነት (19-28)

  • የአምላክ በግ የሆነው ኢየሱስ (29-34)

  • የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት (35-42)

  • ፊልጶስና ናትናኤል (43-51)

1  በመጀመሪያ ቃል+ ነበረ፤ ቃልም ከአምላክ ጋር ነበር፤+ ቃልም አምላክ*+ ነበር።  እሱም በመጀመሪያ ከአምላክ ጋር ነበር።  ሁሉም ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡት በእሱ በኩል ነው፤+ ያለእሱ ወደ ሕልውና የመጣ አንድም ነገር የለም።  በእሱ አማካኝነት ሕይወት ወደ ሕልውና መጥቷል፤ ይህ ሕይወት ደግሞ የሰው ብርሃን ነበር።+  ብርሃኑም በጨለማ እየበራ ነው፤+ ጨለማውም አላሸነፈውም።  ከአምላክ የተላከ አንድ ሰው ነበር፤ እሱም ዮሐንስ+ ይባላል።  ይህ ሰው ስለ ብርሃኑ ይመሠክር ዘንድ ምሥክር ሆኖ መጣ፤+ ይህን ያደረገው ሁሉም ዓይነት ሰዎች በእሱ በኩል እንዲያምኑ ነው።  ያ ብርሃን እሱ አልነበረም፤+ ከዚህ ይልቅ እሱ የመጣው ስለ ብርሃኑ ሊመሠክር ነው።  ለሁሉም ዓይነት ሰው ብርሃን የሚሰጠው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ደርሶ ነበር።+ 10  እሱም በዓለም ነበረ፤+ ዓለምም ወደ ሕልውና የመጣው በእሱ በኩል ነው፤+ ሆኖም ዓለም አላወቀውም። 11  ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም። 12  ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ስላመኑ+ የአምላክ ልጆች+ የመሆን መብት ሰጣቸው። 13  እነሱም የተወለዱት ከአምላክ እንጂ+ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አይደለም። 14  ቃልም ሥጋ ሆነ፤+ በመካከላችንም ኖረ፤ አንድያ ልጅ+ ከአባቱ እንደሚያገኘው ክብር ያለ ክብሩን አየን፤ እሱም መለኮታዊ ሞገስንና* እውነትን ተሞልቶ ነበር። 15  (ዮሐንስ ስለ እሱ መሥክሯል፤ እንዲያውም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “‘ከእኔ ኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ ይበልጣል’ ብዬ የተናገርኩት ስለ እሱ ነው።”)+ 16  ከእሱ የጸጋ ሙላት የተነሳ ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀብለናል። 17  ምክንያቱም ሕጉ የተሰጠው በሙሴ በኩል ነበር፤+ ጸጋና+ እውነት ግን የመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው።+ 18  በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም፤+ ስለ እሱ የገለጸልን+ ከአብ ጎን* ያለውና+ አምላክ+ የሆነው አንድያ ልጁ ነው። 19  አይሁዳውያን “አንተ ማን ነህ?”+ ብለው እንዲጠይቁት ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩ ጊዜ ዮሐንስ የሰጠው ምሥክርነት ይህ ነው፤ 20  “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” ብሎ በግልጽ ተናገረ እንጂ ጥያቄውን ከመመለስ ወደኋላ አላለም። 21  እነሱም “ታዲያ ማን ነህ? ኤልያስ ነህ?”+ ሲሉ ጠየቁት። እሱም መልሶ “አይደለሁም” አለ። “ነቢዩ ነህ?”+ አሉት። እሱም “አይደለሁም!” ሲል መለሰ። 22  በዚህ ጊዜ “ለላኩን ሰዎች መልስ መስጠት እንድንችል ታዲያ አንተ ማን ነህ? ስለ ራስህስ ምን ትላለህ?” አሉት። 23  እሱም “ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው ‘የይሖዋን* መንገድ አቅኑ’ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኸው ሰው እኔ ነኝ” አለ።+ 24  ሰዎቹን የላኳቸውም ፈሪሳውያን ነበሩ። 25  በመሆኑም “ታዲያ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካልሆንክ ለምን ታጠምቃለህ?” ሲሉ ጠየቁት። 26  ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔ በውኃ አጠምቃለሁ። እናንተ የማታውቁት ግን በመካከላችሁ ቆሟል፤ 27  እሱም ከኋላዬ ይመጣል፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት አልበቃም።”+ 28  ይህ የሆነው ዮሐንስ ሲያጠምቅ+ ከነበረበት ከዮርዳኖስ ማዶ በሚገኘው በቢታንያ ነበር። 29  በማግስቱ ኢየሱስ ወደ እሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው+ የአምላክ በግ+ ይኸውላችሁ!+ 30  ‘ከኋላዬ አንድ ሰው ይመጣል፤ ከእኔ በፊት ስለነበረ ከእኔ ይበልጣል’ ያልኳችሁ እሱ ነው።+ 31  እኔም እንኳ አላውቀውም ነበር፤ እኔ በውኃ እያጠመቅኩ የመጣሁበት ምክንያት ግን እሱ ለእስራኤል እንዲገለጥ ነው።”+ 32  በተጨማሪም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምሥክርነት ሰጥቷል፦ “መንፈስ ከሰማይ ወጥቶ እንደ ርግብ ሲወርድ አይቻለሁ፤ በእሱም ላይ አረፈ።+ 33  እኔም እንኳ አላውቀውም ነበር፤ ሆኖም በውኃ እንዳጠምቅ የላከኝ ራሱ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣+ መንፈስ ሲወርድበትና ሲያርፍበት+ የምታየው ያ ሰው ነው’ አለኝ። 34  እኔም አይቻለሁ፤ እሱም የአምላክ ልጅ መሆኑን መሥክሬአለሁ።”+ 35  በማግስቱም ዮሐንስ ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደገና በዚያ ቆሞ ነበር፤ 36  ኢየሱስ ሲያልፍ አይቶም “የአምላክ በግ+ ይኸውላችሁ!” አለ። 37  ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ይህን ሲናገር በሰሙ ጊዜ ኢየሱስን ተከተሉት። 38  ከዚያም ኢየሱስ ዞር ብሎ ሲከተሉት አየና “ምን ፈልጋችሁ ነው?” አላቸው። እነሱም “ረቢ፣ የት ነው የምትኖረው?” አሉት (ረቢ ማለት “መምህር” ማለት ነው)፤ 39  እሱም “ኑና እዩ” አላቸው። ስለዚህ ሄደው የት እንደሚኖር አዩ፤ ጊዜውም አሥር ሰዓት ገደማ ነበር፤ በዚያም ዕለት አብረውት ዋሉ። 40  ዮሐንስ የተናገረውን ከሰሙትና ኢየሱስን ከተከተሉት ሁለት ሰዎች አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ+ ነበር። 41  እንድርያስ በመጀመሪያ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና “መሲሑን አገኘነው”+ አለው (መሲሕ ማለት “ክርስቶስ” ማለት ነው)፤ 42  ወደ ኢየሱስም ወሰደው። ኢየሱስም ባየው ጊዜ “አንተ የዮሐንስ ልጅ ስምዖን+ ነህ፤ ኬፋ ተብለህ ትጠራለህ” አለው (ኬፋ ማለት “ጴጥሮስ” ማለት ነው)።+ 43  በማግስቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ። ከዚያም ፊልጶስን+ አግኝቶ “ተከታዬ ሁን” አለው። 44  ፊልጶስም እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ የቤተሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ። 45  ፊልጶስ ናትናኤልን+ አግኝቶ “ሙሴ በሕጉ፣ ነቢያት ደግሞ በመጻሕፍት የጻፉለትን የዮሴፍን+ ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው” አለው። 46  ናትናኤል ግን “ደግሞ ከናዝሬት ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?” አለው። ፊልጶስም “መጥተህ እይ” አለው። 47  ኢየሱስም ናትናኤል ወደ እሱ ሲመጣ አይቶ ስለ እሱ “ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይኸውላችሁ!” አለ።+ 48  ናትናኤልም “እንዴት ልታውቀኝ ቻልክ?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ ከበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አይቼሃለሁ” አለው። 49  ናትናኤልም “ረቢ፣ አንተ የአምላክ ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” ሲል መለሰለት።+ 50  ኢየሱስም መልሶ “ያመንከው ከበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ ስላልኩህ ነው? ከዚህ የሚበልጥ ነገር ገና ታያለህ” አለው። 51  ከዚያም “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሰማይ ተከፍቶ የአምላክ መላእክት ወደዚያ ሲወጡና የሰው ልጅ ወዳለበት ሲወርዱ ታያላችሁ” አለው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “መለኮት።”
ወይም “ጸጋንና።”
ወይም “በአብ እቅፍ።” ይህ አባባል ልዩ ሞገስ ማግኘትን ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።