የዮሐንስ ወንጌል 4:1-54

  • ኢየሱስና ሳምራዊቷ ሴት (1-38)

    • አምላክን “በመንፈስና በእውነት” አምልኩ (23, 24)

  • ብዙ ሳምራውያን በኢየሱስ አመኑ (39-42)

  • ኢየሱስ የአንድን ባለሥልጣን ልጅ ፈወሰ (43-54)

4  ጌታ፣ ከዮሐንስ ይበልጥ ብዙ ደቀ መዛሙርት እያፈራና እያጠመቀ+ መሆኑን ፈሪሳውያን እንደሰሙ ባወቀ ጊዜ፣  (እርግጥ ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም)  ይሁዳን ለቆ እንደገና ወደ ገሊላ ሄደ።  ሆኖም በሰማርያ በኩል ማለፍ ነበረበት።  ስለሆነም ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው መሬት አጠገብ+ ወዳለችው ሲካር ወደተባለች የሰማርያ ከተማ መጣ።  ደግሞም በዚያ የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ ነበረ።+ ኢየሱስም ከጉዞው የተነሳ ደክሞት ስለነበር በውኃ ጉድጓዱ* አጠገብ ተቀመጠ። ጊዜው ስድስት ሰዓት ገደማ ነበር።  አንዲት የሰማርያ ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “እባክሽ፣ የምጠጣው ውኃ ስጪኝ” አላት።  (ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማዋ ሄደው ነበር።)  ሳምራዊቷም “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት የምጠጣው ውኃ ስጪኝ ትለኛለህ?” አለችው። (ይህን ያለችው አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት ስላልነበራቸው ነው።)+ 10  ኢየሱስም መልሶ “የአምላክን ነፃ ስጦታ+ ብታውቂና ‘የምጠጣው ውኃ ስጪኝ’ የሚልሽ ማን መሆኑን ብትረጂ ኖሮ አንቺ ራስሽ ትጠይቂው ነበር፤ እሱም ሕያው ውኃ ይሰጥሽ ነበር”+ አላት። 11  እሷም እንዲህ አለችው፦ “ጌታዬ፣ አንተ ውኃ መቅጃ እንኳ የለህም፤ ጉድጓዱ ደግሞ ጥልቅ ነው። ታዲያ ይህን ሕያው ውኃ ከየት ታገኛለህ? 12  አንተ ይህን የውኃ ጉድጓድ ከሰጠን እንዲሁም ከልጆቹና ከከብቶቹ ጋር ከዚህ ጉድጓድ ከጠጣው ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህ?” 13  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላት፦ “ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል። 14  እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ፈጽሞ አይጠማም፤+ ከዚህ ይልቅ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ የሚፈልቅ የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ የውኃ ምንጭ ይሆናል።”+ 15  ሴትየዋም “ጌታዬ፣ እንዳልጠማም ሆነ ውኃ ለመቅዳት ወደዚህ ቦታ እንዳልመላለስ ይህን ውኃ ስጠኝ” አለችው። 16  እሱም “ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ተመልሰሽ ነይ” አላት። 17  ሴትየዋም “ባል የለኝም” ብላ መለሰችለት። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “‘ባል የለኝም’ ማለትሽ ትክክል ነው። 18  ምክንያቱም አምስት ባሎች ነበሩሽ፤ አሁን አብሮሽ ያለው ሰው ደግሞ ባልሽ አይደለም። ስለዚህ የተናገርሽው እውነት ነው።” 19  ሴትየዋም እንዲህ አለችው፦ “ጌታዬ፣ አንተ ነቢይ እንደሆንክ አሁን ተረዳሁ።+ 20  አባቶቻችን በዚህ ተራራ ላይ አምልኳቸውን ያካሂዱ ነበር፤ እናንተ አይሁዳውያን ግን ሰዎች ማምለክ ያለባቸው በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ።”+ 21  ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ “አንቺ ሴት፣ እመኚኝ፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም አብን የማታመልኩበት ሰዓት ይመጣል። 22  እናንተ የማታውቁትን ታመልካላችሁ፤+ እኛ ግን መዳን የሚጀምረው ከአይሁዳውያን ስለሆነ የምናውቀውን እናመልካለን።+ 23  ይሁንና እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩበት ሰዓት ይመጣል፤ ያም ሰዓት አሁን ነው፤ ምክንያቱም አብ እንዲያመልኩት የሚፈልገው እንዲህ ያሉ ሰዎችን ነው።+ 24  አምላክ መንፈስ ነው፤+ የሚያመልኩትም በመንፈስና በእውነት ሊያመልኩት ይገባል።”+ 25  ሴትየዋም “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ አውቃለሁ። እሱ ሲመጣ ሁሉንም ነገር ግልጥልጥ አድርጎ ይነግረናል” አለችው። 26  ኢየሱስም “እያነጋገርኩሽ ያለሁት እኔ፣ እሱ ነኝ” አላት።+ 27  በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡ፤ ከሴት ጋር ሲነጋገር አይተውም ተደነቁ። ይሁን እንጂ “ምን ፈልገህ ነው?” ወይም “ከእሷ ጋር የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ያለው ማንም አልነበረም። 28  ሴትየዋም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማዋ በመሄድ ሰዎቹን እንዲህ አለቻቸው፦ 29  “ያደረግኩትን ሁሉ የነገረኝን ሰው መጥታችሁ እዩ። ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆን እንዴ?” 30  እነሱም ከከተማዋ ወጥተው ወደ እሱ መጡ። 31  በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ “ረቢ፣+ ብላ እንጂ” እያሉ ጎተጎቱት። 32  እሱ ግን “እናንተ የማታውቁት የምበላው ምግብ አለኝ” አላቸው። 33  ደቀ መዛሙርቱም እርስ በርሳቸው “ምግብ ያመጣለት ይኖር ይሆን እንዴ?” ተባባሉ። 34  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና+ እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው።+ 35  እናንተ መከር ሊገባ ገና አራት ወር ይቀረዋል ትሉ የለም? እነሆ እላችኋለሁ፣ ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ።+ 36  አሁንም እንኳ አጫጁ ደሞዙን እየተቀበለና ለዘላለም ሕይወት ፍሬ እየሰበሰበ ነው፤ ስለዚህ ዘሪውም ሆነ አጫጁ በአንድነት ደስ ይላቸዋል።+ 37  ከዚህም የተነሳ ‘አንዱ ይዘራል፤ ሌላኛውም ያጭዳል’ የሚለው አባባል እውነት ነው። 38  እኔም ያልደከማችሁበትን እንድታጭዱ ላክኋችሁ። ሌሎች በደከሙበት እናንተ የድካማቸው ፍሬ ተካፋዮች ሆናችሁ።” 39  ሴትየዋ “ያደረግኩትን ሁሉ ነገረኝ”+ ብላ ስለመሠከረች ከዚያች ከተማ ብዙ ሳምራውያን በእሱ አመኑ። 40  ሳምራውያኑም ወደ እሱ በመጡ ጊዜ አብሯቸው እንዲቆይ ለመኑት፤ እሱም በዚያ ሁለት ቀን ቆየ። 41  በመሆኑም ሌሎች ብዙ ሰዎች ከተናገረው ቃል የተነሳ አመኑ፤ 42  ሴትየዋንም “ከእንግዲህ የምናምነው አንቺ ስለነገርሽን ብቻ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ ራሳችን ሰምተናል፤ እንዲሁም ይህ ሰው በእርግጥ የዓለም አዳኝ+ እንደሆነ አውቀናል” አሏት። 43  ከሁለት ቀናት በኋላ ከዚያ ተነስቶ ወደ ገሊላ ሄደ። 44  ይሁንና ኢየሱስ ራሱ፣ ነቢይ በገዛ አገሩ እንደማይከበር+ ተናግሮ ነበር። 45  ገሊላ በደረሰ ጊዜም የገሊላ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ ተቀበሉት፤ ምክንያቱም በኢየሩሳሌም በበዓሉ ላይ ተገኝተው+ በዚያ ያከናወናቸውን ነገሮች ሁሉ አይተው ነበር።+ 46  ከዚያም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ወደለወጠባት በገሊላ ወደምትገኘው ወደ ቃና በድጋሚ መጣ።+ በዚህ ጊዜ በቅፍርናሆም፣ ልጁ የታመመበት የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን የሆነ አንድ ሰው ነበር። 47  ይህ ሰው ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መምጣቱን ሲሰማ ወደ እሱ ሄደና ወደ ቅፍርናሆም ወርዶ በሞት አፋፍ ላይ ያለውን ልጁን እንዲፈውስለት ለመነው። 48  ኢየሱስ ግን “መቼም እናንተ ተአምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ካላያችሁ ፈጽሞ አታምኑም” አለው።+ 49  የቤተ መንግሥት ባለሥልጣኑም “ጌታዬ፣ ልጄ ከመሞቱ በፊት እባክህ በቶሎ ድረስ” አለው። 50  ኢየሱስም “ሂድ፤ ልጅህ ድኗል” አለው።+ ሰውየውም ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አምኖ ሄደ። 51  ሆኖም ሰውየው ወደዚያ እየወረደ ሳለ ባሪያዎቹ አገኙትና ልጁ በሕይወት እንዳለ* ነገሩት። 52  እሱም ልጁ ስንት ሰዓት ላይ እንደተሻለው ጠየቃቸው። እነሱም “ትናንት ሰባት ሰዓት ላይ ትኩሳቱ ለቀቀው” ብለው መለሱለት። 53   በዚህ ጊዜ አባትየው ልጁ የዳነው ልክ ኢየሱስ “ልጅህ ድኗል” ባለው ሰዓት ላይ መሆኑን አወቀ።+ እሱና መላው ቤተሰቡም አማኞች ሆኑ። 54  ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ ሲመጣ ያከናወነው ሁለተኛው ተአምራዊ ምልክት ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ምንጩ።”
ወይም “መዳኑን።”