ለገላትያ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 2:1-21

  • ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት ጋር ተገናኘ (1-10)

  • ጳውሎስ ጴጥሮስን (ኬፋን) ገሠጸው (11-14)

  • ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ነው (15-21)

2  ከዚያም ከ14 ዓመት በኋላ ዳግመኛ ወደ ኢየሩሳሌም ስወጣ በርናባስ አብሮኝ ነበር፤+ ቲቶንም ይዤው ሄድኩ።+  ሆኖም የሄድኩት በተገለጠልኝ ራእይ መሠረት ነበር፤ ከዚያም በአሕዛብ መካከል እየሰበክሁ ያለሁትን ምሥራች ከፍ ተደርገው በሚታዩት ወንድሞች ፊት አቀረብኩ። ይሁን እንጂ እየሮጥኩ ያለሁት ወይም የሮጥኩት ምናልባት በከንቱ እንዳይሆን ስለሰጋሁ ይህን ያስታወቅኳቸው ለብቻቸው ነበር።  ይሁንና ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ+ እንኳ ግሪካዊ ቢሆንም እንዲገረዝ አልተገደደም።+  ሆኖም ይህ ጉዳይ የተነሳው ሙሉ በሙሉ ባሪያዎች ሊያደርጉን በማሰብ+ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባለን አንድነት ያገኘነውን ነፃነት+ ሊሰልሉ ሾልከው በስውር በገቡት ሐሰተኛ ወንድሞች ምክንያት ነው፤+  እኛ ግን የምሥራቹ እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር በማለት ለአንድ አፍታ* እንኳ እሺ ብለን አልተገዛንላቸውም።+  ወሳኝ ሰዎች ተደርገው የሚታዩትን+ በተመለከተ ግን እነዚህ ሰዎች ለእኔ የጨመሩልኝ አዲስ ነገር የለም። አዎ፣ አምላክ የሰውን ውጫዊ ማንነት አይቶ ስለማያዳላ እነዚህ ከፍ ተደርገው የሚታዩት ሰዎች ቀደም ሲል ምንም ይሁኑ ምን ለእኔ የሚያመጣው ለውጥ የለም።  በአንጻሩ ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት እንዲሰብክ ምሥራቹ በአደራ እንደተሰጠው ሁሉ እኔም ላልተገረዙት እንድሰብክ ምሥራቹ በአደራ እንደተሰጠኝ በተገነዘቡ ጊዜ+  (ጴጥሮስ ለተገረዙት ሐዋርያ ሆኖ እንዲያገለግል ኃይል የሰጠው አምላክ ለእኔም ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን እንዳገለግል ኃይል ሰጥቶኛልና፤)+  እንዲሁም እንደ ዓምድ የሚታዩት ያዕቆብ፣+ ኬፋና* ዮሐንስ የተሰጠኝን ጸጋ በተረዱ ጊዜ+ እነሱ ወደተገረዙት እኛ ደግሞ ወደ አሕዛብ እንድንሄድ ለእኔና ለበርናባስ+ ቀኝ እጃቸውን በመስጠት አጋርነታቸውን* ገለጹልን። 10  ይሁንና ድሆችን ማሰባችንን እንዳናቋርጥ አደራ አሉን፤ እኔም ብሆን ይህን ለመፈጸም ትጋት የተሞላበት ጥረት ሳደርግ ነበር።+ 11  ይሁን እንጂ ኬፋ*+ ወደ አንጾኪያ+ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምኩት፤* ምክንያቱም ግልጽ የሆነ ስህተት ሠርቶ* ነበር። 12  የተወሰኑ ሰዎች ከያዕቆብ+ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት ከአሕዛብ ወገን ከሆኑ ሰዎች ጋር ይበላ ነበር፤+ እነሱ ከመጡ በኋላ ግን ከተገረዙት ወገን የሆኑትን በመፍራት ይህን ማድረጉን አቁሞ ራሱን ከአሕዛብ አገለለ።+ 13  የቀሩት አይሁዳውያንም በዚህ የግብዝነት ድርጊት* ከእሱ ጋር ተባበሩ፤ በርናባስም እንኳ በእነሱ የግብዝነት ድርጊት* ተሸንፎ ነበር። 14  ሆኖም ከምሥራቹ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ እየተጓዙ እንዳልሆኑ ባየሁ ጊዜ+ ኬፋን* በሁሉም ፊት እንዲህ አልኩት፦ “አንተ አይሁዳዊ ሆነህ ሳለህ እንደ አይሁዳውያን ሳይሆን እንደ አሕዛብ የምትኖር ከሆነ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች እንደ አይሁዳውያን ልማድ እንዲኖሩ እንዴት ልታስገድዳቸው ትችላለህ?”+ 15  በትውልዳችን አይሁዳውያን እንጂ ከአሕዛብ ወገን እንደሆኑት ኃጢአተኞች ያልሆንነው እኛ፣ 16  አንድ ሰው የሚጸድቀው ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን+ ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን።+ ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በክርስቶስ በማመን እንድንጸድቅ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፤ ምክንያቱም ሕግን በመጠበቅ መጽደቅ የሚችል ሰው* የለም።+ 17  እኛ በክርስቶስ አማካኝነት መጽደቅ በመፈለጋችን እንደ ኃጢአተኞች ተደርገን ከታየን፣ ታዲያ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነው ማለት ነው? በጭራሽ! 18  በአንድ ወቅት እኔው ራሴ ያፈረስኳቸውን እነዚያኑ ነገሮች መልሼ የምገነባ ከሆነ ሕግ ተላላፊ መሆኔን አሳያለሁ ማለት ነው። 19  ለአምላክ ሕያው መሆን እችል ዘንድ በሕጉ በኩል ለሕጉ ሞቻለሁና።*+ 20  እኔ አሁን ከክርስቶስ ጋር በእንጨት ላይ ተቸንክሬአለሁ።+ ከዚህ በኋላ የምኖረው እኔ ሳልሆን+ ከእኔ ጋር አንድ ሆኖ የሚኖረው ክርስቶስ ነው። አሁን በሥጋ የምኖረውን ሕይወት የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው+ በአምላክ ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።+ 21  የአምላክን ጸጋ+ ወደ ጎን ገሸሽ አላደርግም፤* ጽድቅ የሚገኘው በሕግ አማካኝነት ከሆነማ ክርስቶስ የሞተው እንዲያው በከንቱ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ለአንድ ሰዓት።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “ትብብራቸውን።”
ወይም “ሊወገዝ ይገባው።”
ወይም “ተጋፈጥኩት።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ወይም “የማስመሰል ድርጊት።”
ወይም “የማስመሰል ድርጊት።”
ጴጥሮስ ተብሎም ይጠራል።
ቃል በቃል “ሥጋ።”
ወይም “ከሕጉ ነፃ ወጥቻለሁና።”
ወይም “አሽቀንጥሬ አልጥልም።”