ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 2:1-18

  • ‘ከወትሮው የበለጠ ትኩረት ስጡ’ (1-4)

  • “ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዛህለት” (5-9)

  • ኢየሱስና ወንድሞቹ (10-18)

    • ‘ለመዳን የሚያበቃ ዋና ወኪል’ (10)

    • መሐሪ የሆነ ሊቀ ካህናት (17)

2  ቀስ በቀስ እንዳንወሰድ+ ለሰማናቸው ነገሮች ከወትሮው የበለጠ ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።+  በመላእክት አማካኝነት የተነገረው ቃል+ የጸና መሆኑ ከተረጋገጠ እንዲሁም ማንኛውም አለመታዘዝና መተላለፍ ከፍትሕ ጋር የሚስማማ ቅጣት የሚያስከትል ከሆነ+  እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንል እንዴት ከቅጣት ልናመልጥ እንችላለን?+ ይህ መዳን መጀመሪያ ጌታችን የተናገረው+ ሲሆን እሱን የሰሙት ሰዎችም ለእኛ አረጋግጠውልናል፤  አምላክም በምልክቶች፣ በድንቅ ነገሮች፣ በተለያዩ ተአምራትና+ ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን በማደል መሥክሯል።+  ይህን የምንናገርለትን መጪውን ዓለም+ያስገዛው ለመላእክት አይደለምና።  ነገር ግን አንድ ምሥክር፣ አንድ ቦታ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ወይስ ትንከባከበው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?+  ከመላእክት ጥቂት አሳነስከው፤ የክብርና የሞገስ ዘውድ ደፋህለት፤ እንዲሁም በእጆችህ ሥራ ላይ ሾምከው።  ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዛህለት።”+ አምላክ ሁሉንም ነገር ለእሱ ስላስገዛ፣+ ያላስገዛለት ምንም ነገር የለም።+ ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ነገር ተገዝቶለት አናይም።+  ነገር ግን ከመላእክት በጥቂቱ እንዲያንስ ተደርጎ የነበረው ኢየሱስ+ እስከ ሞት ድረስ መከራ በመቀበሉ+ አሁን የክብርና የሞገስ ዘውድ ደፍቶ እናየዋለን፤ እሱ በአምላክ ጸጋ ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን ቀምሷል።+ 10  ሁሉ ነገር የሚኖረው ለአምላክ ነው፤ የሚኖረውም በእሱ አማካኝነት ነው። ስለዚህ አምላክ ብዙ ልጆችን ክብር ለማጎናጸፍ+ ሲል ለመዳን የሚያበቃቸውን “ዋና ወኪል”+ በመከራ አማካኝነት ፍጹም ማድረጉ የተገባ ነበር።+ 11  የሚቀድሰውም ሆነ የሚቀደሱት ሰዎች፣+ ሁሉም ከአንድ አባት የመጡ ናቸውና፤+ ከዚህም የተነሳ እነሱን ወንድሞች ብሎ ለመጥራት አያፍርም፤+ 12  ምክንያቱም “ስምህን ለወንድሞቼ አሳውቃለሁ፤ በጉባኤ መካከልም በመዝሙር አወድስሃለሁ” ይላል።+ 13  ደግሞም “እኔ እምነቴን በእሱ ላይ እጥላለሁ” ይላል።+ እንደገናም “እነሆ! እኔና ይሖዋ* የሰጠኝ ልጆች” ይላል።+ 14  ስለዚህ እነዚህ “ልጆች” ሥጋና ደም ስለሆኑ እሱም ሥጋና ደም ሆነ፤+ ይህም የሆነው ለሞት የመዳረግ አቅም ያለውን+ ዲያብሎስን በሞቱ አማካኝነት እንዳልነበረ ያደርገው ዘንድ ነው፤+ 15  እንዲሁም ሞትን በመፍራታቸው በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ በባርነት ቀንበር የተያዙትን ሁሉ ነፃ እንዲያወጣ ነው።+ 16  እሱ እየረዳ ያለው መላእክትን እንዳልሆነ የታወቀ ነውና፤ ከዚህ ይልቅ እየረዳ ያለው የአብርሃምን ዘር ነው።+ 17  ስለሆነም ለሕዝቡ ኃጢአት የማስተሰረያ መሥዋዕት ለማቅረብ*+ በአምላክ አገልግሎት መሐሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ይሆን ዘንድ በሁሉ ረገድ እንደ “ወንድሞቹ” መሆን አስፈለገው።+ 18  በተፈተነ ጊዜ እሱ ራሱ መከራ ስለደረሰበት+ በፈተና ላይ ላሉት ሊደርስላቸው ይችላል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተሰረይ።”