ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ 10:1-39

  • የእንስሳት መሥዋዕት ኃጢአትን ማስወገድ አይችልም (1-4)

    • ሕጉ ጥላ ነው (1)

  • ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የቀረበ የክርስቶስ መሥዋዕት (5-18)

  • “ወደ ሕይወት የሚመራ አዲስ መንገድ” (19-25)

    • “መሰብሰባችንን ቸል አንበል” (24, 25)

  • ሆን ብሎ በኃጢአት ጎዳና ከመመላለስ መራቅ (26-31)

  • የተስፋው ቃል ሲፈጸም ለማየት መጽናት (32-39)

10  ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ+ ነው እንጂ የእነዚህ ነገሮች እውነተኛ አካል አይደለም፤ ስለዚህ ሕጉ ከዓመት ዓመት እነዚያኑ መሥዋዕቶች በማቅረብ አምላክን የሚያመልኩትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው አይችልም።*+  ቢችልማ ኖሮ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረም? ምክንያቱም ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡት ሰዎች አንዴ ከነጹ በኋላ ሕሊናቸው በጥፋተኝነት ስሜት አይወቅሳቸውም ነበር።  ይሁንና እነዚህ መሥዋዕቶች ከዓመት ዓመት ኃጢአት እንዲታወስ ያደርጋሉ፤+  የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ማስወገድ አይችልምና።  ስለዚህ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ አለ፦ “‘መሥዋዕትንና መባን አልፈለግክም፤ ከዚህ ይልቅ አካል አዘጋጀህልኝ።  ሙሉ በሙሉ በሚቃጠል መባና ለኃጢአት በሚቀርብ መባ ደስ አልተሰኘህም።’+  በዚህ ጊዜ ‘እነሆ፣ አምላክ ሆይ፣ (ስለ እኔ በመጽሐፍ ጥቅልል እንደተጻፈ) ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ’ አልኩ።”+  በመጀመሪያ እንዲህ አለ፦ “መሥዋዕትን፣ መባን፣ ሙሉ በሙሉ የሚቃጠል መባንና ለኃጢአት የሚቀርብ መባን አልፈለግክም፤ እንዲሁም ደስ አልተሰኘህበትም።” እነዚህ መሥዋዕቶች ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት የሚቀርቡ ናቸው።  ከዚያም “እነሆ፣ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” አለ።+ ሁለተኛውን ለማቋቋም የመጀመሪያውን ያስወግዳል። 10  በዚህ “ፈቃድ”+ መሠረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖ በቀረበው የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አማካኝነት ተቀድሰናል።+ 11  በተጨማሪም እያንዳንዱ ካህን ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብና*+ ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የማይችሉትን+ እነዚያኑ መሥዋዕቶች በየጊዜው ለማቅረብ+ ዕለት ዕለት በቦታው ይገኛል። 12  ይህ ሰው ግን ስለ ኃጢአት ለሁልጊዜ የሚሆን አንድ መሥዋዕት አቅርቦ በአምላክ ቀኝ ተቀምጧል፤+ 13  ከዚያን ጊዜ አንስቶ ጠላቶቹ የእግሩ መርገጫ እስኪደረጉ ድረስ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።+ 14  እነዚያን የሚቀደሱትን ለሁልጊዜ ፍጹማን ያደረጋቸው አንድ መሥዋዕት በማቅረብ ነውና።+ 15  ከዚህ በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስም ስለ እኛ ይመሠክራል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላልና፦ 16  “‘ከዚያ ጊዜ በኋላ ከእነሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው’ ይላል ይሖዋ።* ‘ሕግጋቴን በልባቸው ውስጥ አኖራለሁ፤ በአእምሯቸውም ላይ እጽፋቸዋለሁ።’”+ 17  በመቀጠልም “ኃጢአታቸውንና የዓመፅ ድርጊታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስታውስም” ይላል።+ 18  እንግዲህ እነዚህ ይቅር ከተባሉ፣ ከዚህ በኋላ ለኃጢአት መባ ማቅረብ አያስፈልግም። 19  ስለዚህ ወንድሞች፣ በኢየሱስ ደም አማካኝነት ወደ ቅዱሱ ስፍራ በሚወስደው መንገድ ለመግባት የሚያስችል ድፍረት* አግኝተናል፤+ 20  እሱ የከፈተልን* ይህ መንገድ ወደ ሕይወት የሚመራ አዲስ መንገድ ነው። ይህን ያደረገው በመጋረጃው+ ማለትም በሥጋው በኩል በማለፍ ነው፤ 21  በተጨማሪም በአምላክ ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን+ 22  ከክፉ ሕሊና ለመንጻት+ ልባችንን ተረጭተን እንዲሁም ሰውነታችንን በንጹሕ ውኃ ታጥበን+ በቅን ልቦና እና በሙሉ እምነት ወደ አምላክ እንቅረብ። 23  የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ስለሆነ ተስፋችንን በይፋ ለማወጅ የሚያስችለንን አጋጣሚ ያላንዳች ማወላወል አጥብቀን እንያዝ።+ 24  እንዲሁም እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት* እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤*+ 25  አንዳንዶች ልማድ እንዳደረጉት መሰብሰባችንን* ቸል አንበል፤+ ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ እንበረታታ፤+ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።+ 26  የእውነትን ትክክለኛ እውቀት ካገኘን በኋላ ሆን ብለን በኃጢአት ጎዳና ብንመላለስ+ ለኃጢአታችን የሚቀርብ ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤+ 27  ከዚህ ይልቅ አስፈሪ ፍርድ ይጠብቀናል፤ አምላክን የሚቃወሙትን የሚበላ የሚነድ ቁጣም ይኖራል።+ 28  የሙሴን ሕግ የጣሰ ማንኛውም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሠከሩበት ያለርኅራኄ ይገደል ነበር።+ 29  ታዲያ የአምላክን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የቃል ኪዳኑን ደም+ እንደ ተራ ነገር የቆጠረና የጸጋን መንፈስ በንቀት ያጥላላ ሰው ምን ያህል የከፋ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?+ 30  “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቀዋለንና። ደግሞም “ይሖዋ* ሕዝቡን ይዳኛል።”+ 31  በሕያው አምላክ እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር ነው። 32  ይሁን እንጂ ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ+ በመከራ ውስጥ በከፍተኛ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀድሞውን ጊዜ ዘወትር አስታውሱ። 33  በአደባባይ ለነቀፋና ለመከራ የተጋለጣችሁባቸው* ጊዜያት ነበሩ፤ ደግሞም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰባቸውን ሰዎች መከራ የተጋራችሁባቸው* ጊዜያት ነበሩ። 34  እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ዘላቂ የሆነ ንብረት እንዳላችሁ ስለምታውቁ+ በእስር ላይ ላሉት ራራችሁላቸው፤ እንዲሁም ንብረታችሁ ሲዘረፍ ሁኔታውን በደስታ ተቀበላችሁ።+ 35  እንግዲህ ትልቅ ወሮታ የሚያስገኘውን በድፍረት የመናገር ነፃነታችሁን አሽቀንጥራችሁ አትጣሉት።+ 36  የአምላክን ፈቃድ ከፈጸማችሁ በኋላ የተስፋው ቃል ሲፈጸም ማየት እንድትችሉ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።+ 37  ምክንያቱም “ለጥቂት ጊዜ ነው”+ እንጂ “የሚመጣው እሱ ይመጣል፤ ደግሞም አይዘገይም።”+ 38  “ሆኖም ጻድቅ አገልጋዬ በእምነት ይኖራል”፤+ ደግሞም “ወደኋላ ቢያፈገፍግ በእሱ ደስ አልሰኝም።”*+ 39  እንግዲህ እኛ በሕይወት የሚያኖር* እምነት እንዳላቸው ሰዎች ነን እንጂ ወደ ጥፋት እንደሚያፈገፍጉ ሰዎች አይደለንም።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ስለዚህ ሰዎች . . . ሊያደርጓቸው አይችሉም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሕዝባዊ አገልግሎት ለመስጠትና።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “የመተማመን ስሜት።”
ቃል በቃል “የመረቀልን።”
ወይም “እናስብ።”
ወይም “አንዳችን ሌላውን ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መቀስቀስ ወይም ማነሳሳት።”
ለአምልኮ መሰብሰብን ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ቲያትር ላይ የቀረባችሁ ያህል የተጋለጣችሁባቸው።”
ወይም “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከደረሰባቸው ሰዎች ጎን የቆማችሁባቸው።”
ወይም “ነፍሴ በእሱ ደስ አትሰኝም።”
ወይም “ነፍስን ጠብቆ የሚያኖር።”