ምሳሌ 20:1-30

  • የወይን ጠጅ ፌዘኛ ያደርጋል (1)

  • ‘ሰነፍ በክረምት አያርስም’ (4)

  • የሰው ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውኃ ነው (5)

  • በችኮላ ስእለት ከመሳል ተቆጠብ (25)

  • “የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው” (29)

20  የወይን ጠጅ ፌዘኛ፣+ የሚያሰክር መጠጥም ሥርዓት አልበኛ ያደርጋል፤+በዚህ ምክንያት ከትክክለኛው መንገድ የሚወጣ ሁሉ ጥበበኛ አይደለም።+   ንጉሥ የሚፈጥረው ሽብር* እንደ አንበሳ* ግሳት ነው፤+የእሱን ቁጣ የሚያነሳሳ ሁሉ ሕይወቱን ለአደጋ ያጋልጣል።+   ሰው ከጠብ መራቁ ያስከብረዋል፤+ሞኝ የሆነ ሁሉ ግን ጥል ውስጥ ይዘፈቃል።+   ሰነፍ ሰው በክረምት አያርስም፤በመሆኑም በመከር ወራት ባዶውን ሲቀር ይለምናል።*+   በሰው ልብ ውስጥ ያለ ሐሳብ* እንደ ጥልቅ ውኃ ነው፤አስተዋይ ሰው ግን ቀድቶ ያወጣዋል።   ብዙ ሰዎች ስለ ራሳቸው ታማኝ ፍቅር ያወራሉ፤ይሁንና ታማኝ የሆነን ሰው ማን ሊያገኘው ይችላል?   ጻድቅ ንጹሕ አቋሙን* ጠብቆ ይመላለሳል።+ ከእሱ በኋላ የሚመጡት ልጆቹ ደስተኞች ናቸው።+   ንጉሥ ለመፍረድ በዙፋን ላይ ሲቀመጥ፣+ክፋትን ሁሉ በዓይኖቹ ያበጥራል።+   “ልቤን አንጽቻለሁ፤+ከኃጢአቴም ነጽቻለሁ” ሊል የሚችል ማን ነው?+ 10  አባይ ሚዛንና የሐሰት መለኪያ፣*ሁለቱም በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ናቸው።+ 11  ሕፃን እንኳ ባሕርይው ንጹሕና ትክክል መሆኑበአድራጎቱ ይታወቃል።+ 12  የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዓይንን፣ሁለቱንም የሠራው ይሖዋ ነው።+ 13  እንቅልፍ አትውደድ፤ አለዚያ ድሃ ትሆናለህ።+ ዓይንህን ግለጥ፤ የተትረፈረፈ ምግብም ታገኛለህ።+ 14  ዕቃ የሚገዛ ሰው “የማይረባ ነው፣ የማይረባ ነው!” ይላል፤ከሄደ በኋላ ግን በራሱ ይኩራራል።+ 15  ወርቅ አለ፤ ዛጎልም* ተትረፍርፏል፤እውቀትን የሚናገሩ ከንፈሮች ግን ውድ ናቸው።+ 16  አንድ ሰው ለማያውቀው ሰው ዋስ ከሆነ ልብሱን ውሰድበት፤+ይህን ያደረገው ለባዕድ ሴት* ብሎ ከሆነ መያዣውን ውሰድ።+ 17  ሰው በማጭበርበር ያገኘው ምግብ ያስደስተዋል፤በኋላ ግን አፉን ኮረት ይሞላዋል።+ 18  መመካከር* ሲኖር የታቀደው ነገር ይሳካል፤*+ለውጊያም ስትወጣ ጥበብ ያለበት አመራር ተቀበል።+ 19  ስም የሚያጠፋ ሰው እየዞረ የሌሎችን ሚስጥር ይገልጣል፤+ማማት ከሚወድ ሰው* ጋር አትወዳጅ። 20  አባቱንና እናቱን የሚረግም ሁሉጨለማ ሲሆን መብራቱ ይጠፋበታል።+ 21  በመጀመሪያ በስግብግብነት የተገኘ ውርስ፣የኋላ ኋላ በረከት አይሆንም።+ 22  “ቆይ፣ ብድሬን ባልመልስ!” አትበል።+ ይሖዋን ተስፋ አድርግ፤+ እሱም ያድንሃል።+ 23  አባይ ሚዛን* በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው፤ለማጭበርበር የሚያገለግሉ መለኪያዎችንም መጠቀም ጥሩ አይደለም። 24  ይሖዋ የሰውን አካሄድ ይመራል፤+ሰው የገዛ መንገዱን* እንዴት ማስተዋል ይችላል? 25  ሰው ቸኩሎ “የተቀደሰ ነው!”+ ቢልና ከተሳለ በኋላ ስእለቱን መልሶ ማጤን ቢጀምር ወጥመድ ይሆንበታል።+ 26  ጥበበኛ ንጉሥ ክፉ ሰዎችን ያበጥራል፤+የመውቂያ መንኮራኩርም* በላያቸው ያስኬዳል።+ 27  የሰው እስትንፋስ የይሖዋ መብራት ነው፤ውስጣዊ ማንነቱን በሚገባ ይመረምራል። 28  ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት ንጉሥን ይጠብቃሉ፤+በታማኝ ፍቅርም ዙፋኑን ያጸናል።+ 29  የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው፤+የአረጋውያንም ግርማ ሽበታቸው ነው።+ 30  ሰንበርና ቁስል ክፋትን ያስወግዳል፤*+ግርፋትም የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ያጠራል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የንጉሥ አስፈሪነት።”
ወይም “ደቦል አንበሳ።”
“በመከር ወራት ይፈልጋል፤ ግን አያገኝም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ዕቅድ።” ቃል በቃል “ምክር።”
ምሳሌ 2:7 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “ሁለት ዓይነት የድንጋይ ሚዛንና ሁለት ዓይነት መስፈሪያ።”
ወይም “ለባዕድ።”
ወይም “ምክር።”
ወይም “ይጸናል።”
ወይም “በከንፈሮቹ ከሚያባብል ሰው።”
ወይም “ሁለት ዓይነት የድንጋይ ሚዛን።”
ወይም “የሚሄድበትን መንገድ።”
ተሽከርካሪ እግር።
ወይም “ያነጻል።”