ምሳሌ 10:1-32

  • ጥበበኛ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል (1)

  • ‘ትጉ እጆች ብልጽግና ያስገኛሉ’ (4)

  • “ከቃላት ብዛት ስህተት አይታጣም” (19)

  • “የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች” (22)

  • “ይሖዋን መፍራት ዕድሜን ያስረዝማል” (27)

10  የሰለሞን ምሳሌዎች።+ ጥበበኛ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤+ሞኝ ልጅ ግን እናቱን ያሳዝናል።   በክፋት የተገኘ ሀብት ምንም ፋይዳ የለውም፤ጽድቅ ግን ከሞት ይታደጋል።+   ይሖዋ ጻድቅ ሰው እንዲራብ* አያደርግም፤+የክፉዎችን ምኞት ግን ያጨናግፋል።   ሥራ የፈቱ እጆች ያደኸያሉ፤+ትጉ እጆች ግን ብልጽግና ያስገኛሉ።+   ጥልቅ ማስተዋል ያለው ልጅ እህሉን በበጋ ይሰበስባል፤አሳፋሪ ልጅ ግን በመከር ወቅት ለጥ ብሎ ይተኛል።+   በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፤+የክፉዎች አፍ ግን የዓመፅ ዕቅዳቸውን ይሰውራል።   የጻድቅ መታሰቢያ* በረከት ያስገኛል፤+የክፉዎች ስም ግን ይጠፋል።*+   ጥበበኛ ልብ ያለው ሰው መመሪያዎችን* ይቀበላል፤+በሞኝነት የሚናገር ሰው ግን ጥፋት ይደርስበታል።+   ንጹሕ አቋሙን* ጠብቆ የሚሄድ ያለስጋት ይመላለሳል፤+መንገዱን ጠማማ የሚያደርግ ግን ይጋለጣል።+ 10  በተንኮል የሚጣቀስ ሐዘን ያመጣል፤+በሞኝነት የሚናገር ሰውም ጥፋት ይደርስበታል።+ 11  የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ነው፤+የክፉዎች አፍ ግን የዓመፅ ዕቅዳቸውን ይሰውራል።+ 12  ጥላቻ ጭቅጭቅ ያስነሳል፤ፍቅር ግን በደልን ሁሉ ይሸፍናል።+ 13  አስተዋይ በሆነ ሰው ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፤+በትር ግን ማስተዋል* ለጎደለው ሰው ጀርባ ነው።+ 14  ጥበበኞች እውቀትን እንደ ውድ ሀብት ያከማቻሉ፤+የሞኝ ሰው አፍ ግን ጥፋት ይጋብዛል።+ 15  የባለጸጋ ሀብት* የተመሸገ ከተማው ነው። ድሆችን የሚያጠፋቸው ድህነታቸው ነው።+ 16  የጻድቅ ሰው ሥራ ወደ ሕይወት ይመራል፤የክፉ ሰው ፍሬ ግን ወደ ኃጢአት ይመራል።+ 17  ተግሣጽን የሚቀበል ለሌሎች የሕይወት መንገድ ይሆናል፤*ወቀሳን ችላ የሚል ግን ሌሎች መንገድ እንዲስቱ ያደርጋል። 18  ጥላቻውን የሚሸፋፍን ሰው ሐሰት ይናገራል፤+ተንኮል ያዘለ ወሬ* የሚያስፋፋ ሰውም ሞኝ ነው። 19  ከቃላት ብዛት ስህተት አይታጣም፤+ከንፈሩን የሚገታ ግን ልባም ሰው ነው።+ 20  የጻድቅ አንደበት ጥራት ያለው ብር ነው፤+የክፉ ሰው ልብ ግን እርባና የለውም። 21  የጻድቅ ከንፈሮች ብዙዎችን ይመግባሉ፤*+ሞኞች ግን ማስተዋል ስለሚጎድላቸው ይሞታሉ።+ 22  የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤+እሱም ከበረከቱ ጋር ሥቃይን* አይጨምርም። 23  አሳፋሪ ምግባር መፈጸም ለሞኝ ሰው እንደ ጨዋታ ነው፤ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰው ግን ጥበበኛ ነው።+ 24  ክፉ ሰው የፈራው ነገር ይደርስበታል፤ጻድቅ ግን የተመኘውን ያገኛል።+ 25  አውሎ ነፋስ ሲያልፍ ክፉ ሰው ተጠርጎ ይወሰዳል፤+ጻድቅ ግን ለዘላለም እንደሚኖር መሠረት ነው።+ 26  ኮምጣጤ ጥርስን፣ ጭስም ዓይንን እንደሚጎዳ፣ሰነፍም ለሚልከው ሰው* እንዲሁ ነው። 27  ይሖዋን መፍራት ዕድሜን ያስረዝማል፤+የክፉዎች ዕድሜ ግን በአጭሩ ይቀጫል።+ 28  የጻድቃን ተስፋ ደስታ ያስገኛል፤+የክፉዎች ተስፋ ግን መና ይቀራል።+ 29  የይሖዋ መንገድ፣ ያለነቀፋ ለሚመላለስ ሰው መሸሸጊያ ነው፤+ለክፉ አድራጊዎች ግን መጥፊያቸው ነው።+ 30  ጻድቅ ሰው ምንም ነገር አይጥለውም፤+ክፉዎች ግን በምድር ላይ መኖራቸውን አይቀጥሉም።+ 31  የጻድቅ አፍ ጥበብን ያፈልቃል፤*ጠማማ ምላስ ግን ትቆረጣለች። 32  የጻድቅ ሰው ከንፈሮች ደስ የሚያሰኘው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃሉ፤የክፉዎች አፍ ግን ጠማማ ነው።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የጻድቁ ነፍስ እንድትራብ።”
ወይም “ጻድቅ ሰው ያተረፈው ስም።”
ቃል በቃል “ይበሰብሳል።”
ቃል በቃል “ትእዛዛትን።”
ምሳሌ 2:7 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ቃል በቃል “ልብ።”
ወይም “ውድ ንብረት።”
“ወደ ሕይወት በሚወስድ መንገድ ላይ ነው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “አሉባልታ።”
ወይም “ይመራሉ።”
ወይም “ሐዘንን፤ መከራን።”
ወይም “ለአሠሪው።”
ወይም “የጥበብን ፍሬ ያፈራል።”