የማቴዎስ ወንጌል 4:1-25

  • ዲያብሎስ ኢየሱስን ፈተነው (1-11)

  • ኢየሱስ በገሊላ መስበክ ጀመረ (12-17)

  • የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ተጠሩ (18-22)

  • ኢየሱስ ሰበከ፣ አስተማረ እንዲሁም ፈወሰ (23-25)

4  ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፣ ዲያብሎስ+ ይፈትነው+ ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ መራው።  እሱም 40 ቀንና 40 ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ።  ፈታኙም+ ቀርቦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው።  እሱ ግን “‘ሰው ከይሖዋ* አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰ።+  ከዚያም ዲያብሎስ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ+ ከወሰደው በኋላ በቤተ መቅደሱ አናት* ላይ አቁሞ+  እንዲህ አለው፦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ራስህን ወደ ታች ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዛል።’ እንዲሁም ‘እግርህን እንቅፋት እንዳይመታው በእጃቸው ያነሱሃል።’”+  ኢየሱስም “‘አምላክህን ይሖዋን* አትፈታተነው’ ተብሎም ተጽፏል” አለው።+  እንደገናም ዲያብሎስ በጣም ረጅም ወደሆነ ተራራ ወስዶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን አሳየው።+  ከዚያም “አንድ ጊዜ ተደፍተህ ብታመልከኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። 10  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! ‘ይሖዋ* አምላክህን ብቻ አምልክ፤+ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’+ ተብሎ ተጽፏልና” አለው። 11  ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤+ እነሆም፣ መላእክት መጥተው ያገለግሉት ጀመር።+ 12  ኢየሱስ፣ ዮሐንስ እንደታሰረ+ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ሄደ።+ 13  ከዚያም ከናዝሬት ወጥቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አውራጃዎች፣ በባሕሩ* አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም+ መጥቶ መኖር ጀመረ፤ 14  ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው የሚከተለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፦ 15  “ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ወደ ባሕሩ* በሚወስደው መንገድ አጠገብ ያላችሁ የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድርና የአሕዛብ ገሊላ ሆይ! 16  በጨለማ ውስጥ ያሉ ሰዎች ታላቅ ብርሃን አዩ፤ ሞት በሰዎች ላይ ባጠላበት ምድር ላሉም ብርሃን+ ወጣላቸው።”+ 17  ከዚያን ጊዜ አንስቶ ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” እያለ ይሰብክ ጀመር።+ 18  በገሊላ ባሕር* አጠገብ ሲሄድ ሁለቱን ወንድማማቾች ማለትም ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን+ እና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው፤ እነሱም ዓሣ አጥማጆች+ ስለነበሩ መረባቸውን ወደ ባሕሩ እየጣሉ ነበር። 19  እሱም “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰው አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው።+ 20  እነሱም ወዲያውኑ መረቦቻቸውን ትተው ተከተሉት።+ 21  ከዚያ እልፍ እንዳለ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾችን ማለትም የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን አያቸው።+ እነሱም ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በጀልባ ላይ ሆነው መረቦቻቸውን እየጠገኑ ነበር፤ ኢየሱስም ጠራቸው።+ 22  እነሱም ወዲያውኑ ጀልባዋንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት። 23  ከዚያም በምኩራቦቻቸው+ እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ+ በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።+ 24  ስለ እሱም የተወራው ወሬ በመላዋ ሶርያ ተዳረሰ፤ ሰዎችም በተለያየ በሽታና ከባድ ሕመም የሚሠቃዩትን፣+ ጋኔን የያዛቸውን፣+ የሚጥል በሽታ ያለባቸውንና+ ሽባዎችን ሁሉ ወደ እሱ አመጡ፤ እሱም ፈወሳቸው። 25  ከዚህም የተነሳ ከገሊላ፣ ከዲካፖሊስ፣* ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በቤተ መቅደሱ ጣሪያ ዙሪያ ያለ ግንብ፤ ጫፍ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ገሊላ ባሕርን ያመለክታል።
ሜድትራንያን ባሕር ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ግን ገሊላ ባሕር ነው ይላሉ።
በመሠረቱ ባሕር ሳይሆን ሐይቅ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጌንሴሬጥ ሐይቅ፣ ገሊላ ባሕር እንዲሁም ጥብርያዶስ ባሕር ተብሎ ተጠርቷል።
ወይም “አሥሩ ከተሞች ከሚገኙበት ክልል።”