የማቴዎስ ወንጌል 24:1-51

  • የክርስቶስ መገኘት ምልክት (1-51)

    • ጦርነት፣ የምግብ እጥረት፣ የምድር ነውጥ (7)

    • ምሥራቹ ይሰበካል (14)

    • “ታላቅ መከራ” (21, 22)

    • የሰው ልጅ ምልክት (30)

    • የበለስ ዛፍ (32-34)

    • እንደ ኖኅ ዘመን (37-39)

    • “ነቅታችሁ ጠብቁ” (42-44)

    • ታማኙ ባሪያና ክፉው ባሪያ (45-51)

24  ኢየሱስ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ እየሄደ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ የቤተ መቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ወደ እሱ ቀረቡ።  እሱም መልሶ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም” አላቸው።+  በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እሱ መጥተው “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና*+ የዚህ ሥርዓት* መደምደሚያ+ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት።  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ማንም እንዳያሳስታችሁ ተጠንቀቁ፤+  ብዙዎች ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ።+  ጦርነትና የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ። በዚህ ጊዜ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው።+  “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳልና፤+ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና+ የምድር ነውጥ ይከሰታል።+  እነዚህ ነገሮች ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።  “በዚያን ጊዜ ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣+ ይገድሏችኋል+ እንዲሁም በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።+ 10  በተጨማሪም ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ አንዱ ሌላውን አሳልፎ ይሰጣል፤ እርስ በርሳቸውም ይጠላላሉ። 11  ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ፤+ 12  ክፋት* እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል። 13  እስከ መጨረሻው የጸና* ግን ይድናል።+ 14  ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤+ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል። 15  “ስለዚህ ነቢዩ ዳንኤል በተናገረው መሠረት ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’ በተቀደሰ ስፍራ ቆሞ ስታዩ+ አንባቢው ያስተውል፤ 16  በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ።+ 17  በጣሪያ* ላይ ያለ ሰው ዕቃውን ከቤቱ ለመውሰድ አይውረድ፤ 18  በእርሻም ያለ መደረቢያውን ለመውሰድ አይመለስ። 19  በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! 20  ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት* ቀን እንዳይሆን ዘወትር ጸልዩ፤ 21  ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን+ ታላቅ መከራ+ ይከሰታል። 22  እንዲያውም ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ሁሉ ባልዳነ ነበር፤ ሆኖም ለተመረጡት ሲባል ቀኖቹ ያጥራሉ።+ 23  “በዚያን ጊዜ ማንም ‘እነሆ፣ ክርስቶስ ይኸውላችሁ’+ ወይም ‘ያውላችሁ’ ቢላችሁ አትመኑ።+ 24  ምክንያቱም ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤+ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክቶችና አስደናቂ ነገሮች ያደርጋሉ።+ 25  እንግዲህ አስቀድሜ አስጠንቅቄያችኋለሁ። 26  ስለዚህ ሰዎች ‘እነሆ፣ በምድረ በዳ ነው’ ቢሏችሁ ወደዚያ አትውጡ፤ ‘እነሆ፣ ቤት ውስጥ በውስጠኛው ክፍል ይገኛል’ ቢሏችሁ አትመኑ።+ 27  መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚያበራ ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም* እንዲሁ ይሆናል።+ 28  በድን ባለበት ሁሉ ንስሮች ይሰበሰባሉ።+ 29  “በእነዚያ ቀናት ከሚኖረው መከራ በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ትጨልማለች፤+ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይላትም ይናወጣሉ።+ 30  ከዚያም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፤ የምድር ወገኖችም ሁሉ በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ፤+ የሰው ልጅም+ በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል።+ 31  እሱም መላእክቱን በታላቅ የመለከት ድምፅ ይልካል፤ እነሱም ከአራቱ ነፋሳት፣* ከአንዱ የሰማይ ዳርቻ እስከ ሌላው የሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።+ 32  “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ* እንደቀረበ ታውቃላችሁ።+ 33  በተመሳሳይ እናንተም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።+ 34  እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም። 35  ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም።+ 36  “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣+ ማንም አያውቅም።+ 37  በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ+ የሰው ልጅ መገኘትም* እንደዚሁ ይሆናል።+ 38  ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን+ ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ 39  የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤+ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል። 40  በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ቦታ ይሠራሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው እዚያው ይተዋል። 41  ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ እዚያው ትተዋለች።+ 42  ስለዚህ ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።+ 43  “ነገር ግን ይህን እወቁ፦ አንድ ሰው ሌባ+ በየትኛው ክፍለ ሌሊት* እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ነቅቶ በጠበቀና ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር።+ 44  ስለዚህ እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።+ 45  “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም* ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?+ 46  ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው!+ 47  እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል። 48  “ነገር ግን ያ ክፉ ባሪያ በልቡ ‘ጌታዬ ይዘገያል’ ብሎ ቢያስብ+ 49  ደግሞም ባልንጀሮቹ የሆኑትን ባሪያዎች መደብደብ ቢጀምር እንዲሁም ከሰካራሞች ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ 50  የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቀው ቀንና ባላሰበው ሰዓት ይመጣል፤+ 51  ከባድ ቅጣት ይቀጣዋል፤* ዕጣውንም ከግብዞች ጋር ያደርገዋል። በዚያም ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “ሕገ ወጥነት።”
ወይም “የሚጸና።”
በዚያ ወቅት የሚሠሩት አብዛኞቹ ቤቶች ጠፍጣፋ ጣሪያ የነበራቸው ሲሆን ሰዎች በጣሪያው ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውኑ ነበር።
ሥራ 1:12 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ከሰሜን፣ ከምሥራቅ፣ ከደቡብና ከምዕራብ አቅጣጫ የሚነፍሱ ነፋሳትን ያመለክታል።
በጳለስጢና ምድር ዕፀዋት የሚለመልሙት በበጋ ነው።
ወይም “ሌሊት በስንት ሰዓት።”
ወይም “ጥበበኛ።”
ወይም “ለሁለት ይቆርጠዋል።”