የማቴዎስ ወንጌል 19:1-30

  • ጋብቻና ፍቺ (1-9)

  • የነጠላነት ስጦታ (10-12)

  • ኢየሱስ ልጆችን ባረከ (13-15)

  • ሀብታም የሆነ አንድ ወጣት ያቀረበው ጥያቄ (16-24)

  • ለመንግሥቱ ሲባል መሥዋዕትነት መክፈል (25-30)

19  ኢየሱስ ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ከገሊላ ወጥቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳሉት የይሁዳ ድንበሮች መጣ።+  እጅግ ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ እሱም በዚያ ፈወሳቸው።  ፈሪሳውያንም ወደ እሱ መጥተው ሊፈትኑት በማሰብ “አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን እንዲፈታ ሕግ ይፈቅድለታል?” ሲሉ ጠየቁት።+  እሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም?+  ‘ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም?+  በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን* ማንም ሰው አይለያየው።”+  እነሱም “ታዲያ ሙሴ የፍቺ የምሥክር ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት ያዘዘው ለምንድን ነው?” አሉት።+  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሴ የልባችሁን ደንዳናነት አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ+ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም።+  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፆታ ብልግና* ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።”+ 10  ደቀ መዛሙርቱም “በባልና በሚስት መካከል ያለው ሁኔታ እንዲህ ከሆነስ አለማግባት ይመረጣል” አሉት። 11  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ስጦታው ያላቸው ካልሆኑ በስተቀር ይህን ሁሉም ሰው ሊቀበለው አይችልም።+ 12  ምክንያቱም ጃንደረባ ሆነው የሚወለዱ አሉ፤ ሰው የሰለባቸው ጃንደረቦችም አሉ፤ እንዲሁም ለመንግሥተ ሰማያት ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ ያደረጉ ጃንደረቦችም አሉ። ይህን ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው።”+ 13  ከዚያም ኢየሱስ እጁን እንዲጭንባቸውና* እንዲጸልይላቸው ትናንሽ ልጆችን ወደ እሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው።+ 14  ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ልጆቹን ተዉአቸው፤ ወደ እኔ እንዳይመጡ አትከልክሏቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉት ነውና” አለ።+ 15  እጁንም ከጫነባቸው* በኋላ ከዚያ ስፍራ ተነስቶ ሄደ። 16  ከዚያም አንድ ወጣት ወደ እሱ መጥቶ “መምህር፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ጥሩ ነገር ማድረግ ይኖርብኛል?” አለው።+ 17  እሱም “ስለ ጥሩ ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? ጥሩ የሆነው አምላክ ብቻ ነው።+ ሆኖም ሕይወት ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ዘወትር ትእዛዛቱን ጠብቅ” አለው።+ 18  እሱም “የትኞቹን?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “አትግደል፣+ አታመንዝር፣+ አትስረቅ፣+ በሐሰት አትመሥክር፣+ 19  አባትህንና እናትህን አክብር+ እንዲሁም ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ።”+ 20  ወጣቱም “እነዚህን ሁሉ ስጠብቅ ኖሬአለሁ፤ ታዲያ አሁን የሚጎድለኝ ነገር ምንድን ነው?” አለው። 21  ኢየሱስም “ፍጹም* መሆን ከፈለግክ ሂድና ንብረትህን ሸጠህ ገንዘቡን ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤+ ደግሞም መጥተህ ተከታዬ ሁን” አለው።+ 22  ወጣቱም ይህን ሲሰማ ብዙ ንብረት ስለነበረው እያዘነ ሄደ።+ 23  ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሀብታም ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት እጅግ አስቸጋሪ ይሆንበታል።+ 24  ዳግመኛም እላችኋለሁ፣ ሀብታም ሰው ወደ አምላክ መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀልላል።”+ 25  ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በጣም ተገርመው “በዚህ ዓይነትማ ማን ሊድን ይችላል?” አሉ።+ 26  ኢየሱስም ትኩር ብሎ እያያቸው “ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን ሁሉ ነገር ይቻላል” አላቸው።+ 27  ከዚያም ጴጥሮስ መልሶ “እነሆ፣ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ የምናገኘው ምን ይሆን?” አለው።+ 28  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሉም ነገር አዲስ በሚሆንበት ጊዜ* የሰው ልጅ፣ ክብራማ በሆነው ዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ እኔን የተከተላችሁኝ እናንተ በ12 ዙፋኖች ላይ ተቀምጣችሁ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ትፈርዳላችሁ።+ 29  እንዲሁም ስለ ስሜ ሲል ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለም ሕይወትም ይወርሳል።+ 30  “ሆኖም ፊተኞች የሆኑ ብዙዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑ ደግሞ ፊተኞች ይሆናሉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በአንድ ቀንበር ያጣመደውን።”
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ኢየሱስ እንዲባርካቸውና።”
ወይም “ከባረካቸው።”
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ወይም “ሙሉ።”
ወይም “በዳግም ፍጥረት።”