ዳንኤል 7:1-28

  • የአራቱ አራዊት ራእይ (1-8)

    • እብሪተኛ የሆነ ትንሽ ቀንድ ብቅ አለ (8)

  • ከዘመናት በፊት የነበረው አምላክ ችሎት ተቀመጠ (9-14)

    • የሰው ልጅ ንግሥና ተሰጠው (13, 14)

  • የራእዩ ትርጉም ለዳንኤል ተገለጸለት (15-28)

    • አራቱ አራዊት አራት ነገሥታት ናቸው (17)

    • ቅዱሳኑ መንግሥት ይቀበላሉ (18)

    • አሥር ቀንዶች ወይም ነገሥታት ይነሳሉ (24)

7  የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛር+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በአልጋው ላይ ተኝቶ ሳለ ሕልምና ራእዮች አየ።+ ከዚያም ያየውን ሕልም ጻፈ፤+ ጉዳዩንም በዝርዝር አሰፈረ።  ዳንኤልም እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “በሌሊት ባየኋቸው ራእዮች ላይ አራቱ የሰማያት ነፋሳት የተንጣለለውን ባሕር ሲያናውጡት ተመለከትኩ።+  አራት ግዙፍ አራዊትም+ ከባሕር ውስጥ ወጡ፤ እያንዳንዳቸውም አንዱ ከሌላው የተለዩ ነበሩ።  “የመጀመሪያው አንበሳ ይመስል ነበር፤+ የንስር ክንፎችም ነበሩት።+ እኔም እየተመለከትኩ ሳለ ክንፎቹ ተነቃቀሉ፤ ከምድር እንዲነሳና ልክ እንደ ሰው በሁለት እግሩ እንዲቆም ተደረገ፤ የሰውም ልብ ተሰጠው።  “እነሆ፣ ሁለተኛው አውሬ ድብ ይመስል ነበር።+ በአንድ ጎኑም ተነስቶ ነበር፤ በአፉም ውስጥ በጥርሶቹ መካከል ሦስት የጎድን አጥንቶች ይዞ ነበር፤ ‘ተነስተህ ብዙ ሥጋ ብላ’ ተባለ።+  “ከዚህም በኋላ አየሁ፤ እነሆ ነብር የሚመስል ሌላ አውሬ ነበር፤+ ሆኖም ጀርባው ላይ አራት የወፍ ክንፎች ነበሩት። አውሬውም አራት ራሶች ነበሩት፤+ የመግዛት ሥልጣንም ተሰጠው።  “ከዚህ በኋላ በሌሊት ባየኋቸው ራእዮች ላይ የሚያስፈራ፣ የሚያስደነግጥና ለየት ያለ ጥንካሬ ያለው አራተኛ አውሬ ተመለከትኩ፤ ትላልቅ የብረት ጥርሶችም ነበሩት። ይበላና ያደቅ እንዲሁም የቀረውን በእግሮቹ ይረጋግጥ ነበር።+ ከእሱ በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየ ሲሆን አሥር ቀንዶች ነበሩት።  ቀንዶቹን እየተመለከትኩ ሳለ፣ እነሆ ሌላ ትንሽ ቀንድ በመካከላቸው ወጣ፤+ ከመጀመሪያዎቹ ቀንዶች መካከል ሦስቱ በፊቱ ተነቃቀሉ። እነሆ፣ በዚህ ቀንድ ላይ የሰው ዓይኖች የሚመስሉ ዓይኖች ነበሩ፤ በእብሪት* የሚናገርም አፍ ነበረው።+  “እኔም እየተመለከትኩ ሳለ ዙፋኖች ተዘጋጁ፤ ከዘመናት በፊት የነበረውም+ ተቀመጠ።+ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ፣+ የራሱም ፀጉር እንደጠራ ሱፍ ነበር። ዙፋኑ የእሳት ነበልባል፣ መንኮራኩሮቹም የሚነድ እሳት ነበሩ።+ 10  ከፊቱ የእሳት ጅረት ይፈልቅና ይፈስ ነበር።+ ሺህ ጊዜ ሺዎች ያገለግሉት ነበር፤ እልፍ ጊዜ እልፍም* በፊቱ ቆመው ነበር።+ ችሎቱ+ ተሰየመ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። 11  “በዚህ ጊዜ ቀንዱ ከሚናገረው የእብሪት* ቃል የተነሳ መመልከቴን ቀጠልኩ፤+ እኔም እየተመለከትኩ ሳለ አውሬው ተገደለ፤ አካሉም ወደሚንበለበል እሳት ተጥሎ እንዲጠፋ ተደረገ። 12  የቀሩት አራዊት+ ግን የገዢነት ሥልጣናቸውን ተቀሙ፤ ሆኖም ለተወሰነ ጊዜና ወቅት ዕድሜያቸው ተራዘመ። 13  “በሌሊት የተገለጡልኝን ራእዮች ማየቴን ቀጠልኩ፤ እነሆ የሰው ልጅ+ የሚመስል ከሰማያት ደመና ጋር መጣ፤ ከዘመናት በፊት ወደነበረውም+ እንዲገባ ተፈቀደለት፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። 14  ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያገለግሉት የገዢነት ሥልጣን፣+ ክብርና+ መንግሥት ተሰጠው።+ የገዢነት ሥልጣኑ የማያልፍና ዘላለማዊ፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።+ 15  “እኔ ዳንኤል ያየኋቸው ራእዮች ፍርሃት ስላሳደሩብኝ በውስጤ መንፈሴ ታወከ።+ 16  ከቆሙት መካከል ወደ አንዱ ቀርቤ የዚህ ሁሉ ትክክለኛ ትርጉም ምን እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም መለሰልኝ፤ ደግሞም የእነዚህን ነገሮች ትርጉም ገለጸልኝ። 17  “‘እነዚህ አራት ግዙፍ አራዊት+ ከምድር የሚነሱ አራት ነገሥታት ናቸው።+ 18  ይሁንና ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን፣+ መንግሥቱን ይቀበላሉ፤+ መንግሥቱን ለዘላለም፣ አዎ ለዘላለም ዓለም ይወርሳሉ።’+ 19  “ከዚያም ከሌሎቹ ሁሉ የተለየ ስለሆነው ስለ አራተኛው አውሬ ይበልጥ ማወቅ ፈለግኩ፤ የብረት ጥርሶችና የመዳብ ጥፍሮች ያሉት እጅግ አስፈሪ አውሬ ነበር፤ ይበላና ያደቅ እንዲሁም የቀረውን በእግሩ ይረጋግጥ ነበር፤+ 20  ደግሞም በራሱ ላይ ስለነበሩት አሥር ቀንዶች+ እንዲሁም በኋላ ስለወጣውና ሦስቱ በፊቱ እንዲወድቁ ስላደረገው ስለ ሌላኛው ቀንድ+ ይኸውም ዓይኖችና በእብሪት* የሚናገር አፍ ስላሉት እንዲሁም ከሌሎቹ ስለበለጠው ቀንድ ማወቅ ፈለግኩ። 21  “እየተመለከትኩ ሳለ ይህ ቀንድ በቅዱሳኑ ላይ ጦርነት ከፈተ፤ በእነሱም ላይ አየለባቸው፤+ 22  ይህም የሆነው ከዘመናት በፊት የነበረው+ እስኪመጣና ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን አገልጋዮች+ እስኪፈረድላቸው ድረስ ነበር፤ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወርሱበት የተወሰነው ዘመን መጣ።+ 23  “እሱም እንዲህ አለ፦ ‘አራተኛው አውሬ በምድር ላይ የሚነሳ አራተኛ መንግሥት ነው። ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፤ መላዋን ምድር ያወድማል፣ ይረግጣል እንዲሁም ያደቃል።+ 24  አሥሩ ቀንዶች ከዚህ መንግሥት የሚነሱ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነሱም በኋላ ሌላ ይነሳል፤ እሱም ከመጀመሪያዎቹ የተለየ ይሆናል፤ ሦስት ነገሥታትንም ያዋርዳል።+ 25  በልዑሉ አምላክ ላይ የተቃውሞ ቃል ይናገራል፤+ ከሁሉ በላቀው አምላክ ቅዱሳንም ላይ ያለማቋረጥ ችግር ያደርስባቸዋል። ዘመናትንና ሕግን ለመለወጥ ያስባል፤ እነሱም ለዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ* በእጁ አልፈው ይሰጣሉ።+ 26  ይሁንና ችሎቱ ተሰየመ፤ የገዢነት ሥልጣኑንም ቀሙት፤ ከዚያም አስወገዱት፤ ፈጽሞም አጠፉት።+ 27  “‘ከሰማያት በታች ያለ መንግሥት፣ የገዢነት ሥልጣንና የመንግሥታት ግርማ በሙሉ ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን ለሆኑት ሰዎች ተሰጠ።+ መንግሥታቸው ዘላለማዊ መንግሥት ነው፤+ መንግሥታትም ሁሉ ያገለግሏቸዋል፤ ደግሞም ይታዘዟቸዋል።’ 28  “የነገሩ ፍጻሜ ይህ ነው። እኔም ዳንኤል ሳስበው የነበረው ነገር በጣም አስፈራኝ፤ ፊቴም ገረጣ፤* ነገሩን ግን በልቤ ያዝኩት።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በጉራ።”
ወይም “አንድ መቶ ሚሊዮን።”
ወይም “የጉራ።”
ወይም “በጉራ።”
ሦስት ዘመን ተኩልን ያመለክታል።
ወይም “ፊቴም ተለዋወጠ።”