ዳንኤል 2:1-49

  • ንጉሥ ናቡከደነጾር የሚረብሽ ሕልም አየ (1-4)

  • ሕልሙን ሊፈታ የሚችል ጥበበኛ ሰው ጠፋ (5-13)

  • ዳንኤል የአምላክን እርዳታ ጠየቀ (14-18)

  • ሚስጥሩን ስለገለጠለት አምላክን አወደሰ (19-23)

  • ዳንኤል ሕልሙን ለንጉሡ ነገረው (24-35)

  • የሕልሙ ፍቺ (36-45)

    • ምስሉን የሚያደቅ ድንጋይ (44, 45)

  • ንጉሡ ዳንኤልን አከበረው (46-49)

2  ናቡከደነጾር በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ሕልሞችን አለመ፤ መንፈሱም እጅግ ከመታወኩ የተነሳ+ እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም።  ስለዚህ ንጉሡ ሕልሞቹን እንዲነግሩት አስማተኞቹ ካህናት፣ ጠንቋዮቹ፣ መተተኞቹና ከለዳውያኑ* እንዲጠሩ አዘዘ። በዚህም መሠረት ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ።+  ከዚያም ንጉሡ “ሕልም አልሜ ነበር፤ ሕልሙ ምን እንደሆነ ማወቅ ስለፈለግኩ መንፈሴ ታውኳል” አላቸው።  ከለዳውያኑም በአረማይክ ቋንቋ*+ ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር። ያየኸውን ሕልም ለአገልጋዮችህ ንገረን፤ እኛም ትርጉሙን እናሳውቅሃለን።”  ንጉሡም ለከለዳውያኑ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የመጨረሻ ውሳኔዬ ይህ ነው፦ ሕልሙን ከነትርጉሙ የማታሳውቁኝ ከሆነ ሰውነታችሁ ይቆራረጣል፤ ቤቶቻችሁም የሕዝብ መጸዳጃ* ይሆናሉ።  ሕልሙንና ትርጉሙን ብታሳውቁኝ ግን ስጦታ፣ ሽልማትና ታላቅ ክብር እሰጣችኋለሁ።+ ስለዚህ ሕልሙንና ትርጉሙን አሳውቁኝ።”  እነሱም በድጋሚ መልሰው “ንጉሡ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገረን፤ እኛም ትርጉሙን እንናገራለን” አሉት።  ንጉሡም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የመጨረሻ ውሳኔዬን ስላወቃችሁ ጊዜ ለማራዘም እየሞከራችሁ እንደሆነ በሚገባ ተረድቻለሁ።  ሕልሙን የማታሳውቁኝ ከሆነ ሁላችሁም የሚጠብቃችሁ ቅጣት አንድ ነው። እናንተ ግን ሁኔታው እስኪለወጥ ድረስ፣ የሆነ ውሸትና ማታለያ ልትነግሩኝ ተስማምታችኋል። ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ እኔም ትርጉሙን ልታብራሩ እንደምትችሉ በዚህ አውቃለሁ።” 10  ከለዳውያኑም ለንጉሡ እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ንጉሡ የሚጠይቀውን ነገር መፈጸም የሚችል አንድም ሰው በምድር ላይ የለም፤ የትኛውም ታላቅ ንጉሥ ወይም ገዢ፣ ከማንኛውም አስማተኛ ካህን ወይም ጠንቋይ ወይም ከለዳዊ እንዲህ ዓይነት ነገር ጠይቆ አያውቅም። 11  ንጉሡ እየጠየቀ ያለው ነገር በጣም አስቸጋሪ ነው፤ በሰዎች መካከል* ከማይኖሩት አማልክት በስተቀር ይህን ለንጉሡ ሊገልጽለት የሚችል የለም።” 12  በዚህ ጊዜ ንጉሡ በቁጣ ቱግ አለ፤ በባቢሎን ያሉት ጥበበኛ ሰዎች ሁሉ እንዲገደሉም አዘዘ።+ 13  ትእዛዙ ሲወጣና ጠቢባኑ ሊገደሉ ሲሉ ዳንኤልንና ጓደኞቹንም ለመግደል ይፈልጓቸው ጀመር። 14  በዚህ ጊዜ ዳንኤል በባቢሎን የሚገኙትን ጥበበኛ ሰዎች ለመግደል የወጣውን የንጉሡን የክብር ዘብ አለቃ አርዮክን በጥበብና በዘዴ አናገረው። 15  የንጉሡ ባለሥልጣን የሆነውን አርዮክን “ንጉሡ እንዲህ ያለ ከባድ ትእዛዝ ያወጣው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። አርዮክም ጉዳዩን ለዳንኤል ገለጸለት።+ 16  ዳንኤልም ወደ ንጉሡ ገብቶ የሕልሙን ትርጉም ለእሱ የሚያስታውቅበት ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው። 17  ከዚያም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደ፤ ጉዳዩንም ለጓደኞቹ ለሃናንያህ፣ ለሚሳኤልና ለአዛርያስ ነገራቸው። 18  ደግሞም ዳንኤልንና ጓደኞቹን ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይገድሏቸው የሰማይ አምላክ ምሕረት እንዲያሳያቸውና ሚስጥሩን እንዲገልጥላቸው ይጸልዩ ዘንድ ነገራቸው። 19  ከዚያም ሚስጥሩ በሌሊት ለዳንኤል በራእይ ተገለጠለት።+ በመሆኑም ዳንኤል የሰማይን አምላክ አወደሰ። 20  ዳንኤልም እንዲህ አለ፦ “የአምላክ ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወደስ፤ጥበብና ኃይል የእሱ ብቻ ነውና።+ 21  እሱ ጊዜያትንና ወቅቶችን ይለውጣል፤+ነገሥታትን ያስወግዳል፤ ደግሞም ያስቀምጣል፤+ለጥበበኞች ጥበብን፣ ለአስተዋዮችም እውቀትን ይሰጣል።+ 22  ጥልቅ የሆኑትንና የተሰወሩትን ነገሮች ይገልጣል፤+በጨለማ ውስጥ ያለውን ያውቃል፤+ብርሃንም ከእሱ ጋር ይኖራል።+ 23  የአባቶቼ አምላክ ሆይ፣ ለአንተ ምስጋናና ውዳሴ አቀርባለሁ፤ምክንያቱም ጥበብንና ኃይልን ሰጥተኸኛል። አሁን ደግሞ ከአንተ የጠየቅነውን ነገር አሳውቀኸኛል፤ንጉሡ ያሳሰበውን ጉዳይ አሳውቀኸናል።”+ 24  ከዚያም ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን እንዲያጠፋ ንጉሡ ወደ ሾመው ወደ አርዮክ ሄዶ+ “ከባቢሎን ጠቢባን መካከል አንዳቸውንም አትግደል። በንጉሡ ፊት አቅርበኝ፤ እኔም የሕልሙን ትርጉም ለንጉሡ አሳውቃለሁ” አለው። 25  አርዮክም ዳንኤልን ወዲያውኑ በንጉሡ ፊት አቅርቦ “ከይሁዳ ግዞተኞች መካከል የሕልሙን ትርጉም ለንጉሡ ማሳወቅ የሚችል ሰው አግኝቻለሁ”+ አለው። 26  ንጉሡም ብልጣሶር የተባለውን ዳንኤልን+ “ያየሁትን ሕልምና ትርጉሙን በእርግጥ ልትነግረኝ ትችላለህ?” አለው።+ 27  ዳንኤልም ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ከጠቢባኑ፣ ከጠንቋዮቹ፣ አስማተኛ ከሆኑት ካህናት ወይም ከኮከብ ቆጣሪዎቹ መካከል ንጉሡ የጠየቀውን ሚስጥር መግለጥ የሚችል የለም።+ 28  ይሁንና ሚስጥርን የሚገልጥ አምላክ በሰማያት አለ፤+ እሱም በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነጾር አሳውቆታል። በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለህ ያየኸው ሕልምና የተመለከትካቸው ራእዮች እነዚህ ናቸው፦ 29  “ንጉሥ ሆይ፣ በአልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ታስብ ነበር፤ ሚስጥርን የሚገልጠውም አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አሳውቆሃል። 30  ይህ ሚስጥር ለእኔ የተገለጠልኝ ከሰው ሁሉ የላቀ ጥበብ ስላለኝ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ በልብህ ታስባቸው የነበሩትን ነገሮች ታውቅ ዘንድ የሕልሙ ትርጉም ለንጉሡ እንዲገለጥ ነው።+ 31  “ንጉሥ ሆይ፣ በትኩረት እየተመለከትክ ሳለ አንድ ግዙፍ ምስል* አየህ። ግዙፍ የሆነውና እጅግ የሚያብረቀርቀው ይህ ምስል በፊትህ ቆሞ ነበር፤ መልኩም በጣም የሚያስፈራ ነበር። 32  የምስሉ ራስ ከጥሩ ወርቅ፣+ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣+ ሆዱና ጭኖቹ ከመዳብ፣+ 33  ቅልጥሞቹ ከብረት የተሠሩ+ ሲሆን እግሮቹ ከፊሉ ብረት፣ ከፊሉ ደግሞ ሸክላ* ነበሩ።+ 34  አንተም አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች ሲመታቸውና ሲያደቅቃቸው አየህ።+ 35  በዚህ ጊዜ ብረቱ፣ ሸክላው፣ መዳቡ፣ ብሩና ወርቁ ሁሉም በአንድነት ተሰባበሩ፤ በበጋ ወቅት በአውድማ ላይ እንደሚቀር ገለባም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራርጎ ወሰዳቸው። ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ትልቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሁሉ ሞላ። 36  “ሕልሙ ይህ ነው፤ አሁን ደግሞ ትርጉሙን ለንጉሡ እናሳውቃለን። 37  ንጉሥ ሆይ፣ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትን፣ ኃይልን፣ ብርታትንና ክብርን ሰጥቶሃል፤+ 38  ደግሞም በየትኛውም ቦታ የሚኖሩትን ሰዎችም ሆነ የዱር እንስሳትና የሰማይ ወፎች በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በሁሉም ላይ ገዢ አድርጎሃል፤+ የወርቁ ራስ አንተ ራስህ ነህ።+ 39  “ይሁንና ከአንተ በኋላ፣ ከአንተ ያነሰ ሌላ መንግሥት ይነሳል፤+ ከዚያም መላውን ምድር የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የመዳብ መንግሥት ይነሳል።+ 40  “አራተኛው መንግሥት ደግሞ እንደ ብረት የጠነከረ ይሆናል።+ ብረት ሁሉንም ነገር እንደሚሰባብርና እንደሚፈጭ ሁሉ፣ እሱም እንደሚያደቅ ብረት እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ይሰባብራቸዋል፤ ደግሞም ያደቅቃቸዋል።+ 41  “እግሮቹና ጣቶቹ ከፊሉ ሸክላ፣ ከፊሉ ደግሞ ብረት ሆነው እንዳየህ ሁሉ መንግሥቱም የተከፋፈለ ይሆናል፤ ሆኖም ብረቱና የሸክላ ጭቃው ተደባልቆ እንዳየህ ሁሉ በተወሰነ መጠን የብረት ጥንካሬ ይኖረዋል። 42  የእግሮቹ ጣቶች ከፊሉ ብረት፣ ከፊሉ ሸክላ እንደሆኑ ሁሉ ይህም መንግሥት በከፊል ብርቱ፣ በከፊል ደግሞ ደካማ ይሆናል። 43  ብረቱና የሸክላ ጭቃው ተደባልቀው እንዳየህ ሁሉ እነሱም ከሕዝቡ* ጋር ይደባለቃሉ፤ ሆኖም ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይዋሃድ ሁሉ እነሱም አንዱ ከሌላው ጋር አይጣበቁም። 44  “በእነዚያ ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይጠፋ+ መንግሥት ያቋቁማል።+ ይህም መንግሥት ለሌላ ሕዝብ አይሰጥም።+ እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤+ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል፤+ 45  አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ከተራራው ተፈንቅሎ ብረቱን፣ መዳቡን፣ ሸክላውን፣ ብሩንና ወርቁን ሲያደቅ እንዳየህ ሁሉ እንዲሁ ይሆናል።+ ታላቁ አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ለንጉሡ አሳውቆታል።+ ሕልሙ እውነት፣ ትርጉሙም አስተማማኝ ነው።” 46  ከዚያም ንጉሥ ናቡከደነጾር በዳንኤል ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፋ፤ ዳንኤልንም እጅግ አከበረው። ደግሞም ስጦታና ዕጣን እንዲቀርብለት አዘዘ። 47  ንጉሡም ዳንኤልን እንዲህ አለው፦ “በእርግጥም አምላካችሁ የአማልክት አምላክና የነገሥታት ጌታ እንዲሁም ሚስጥርን የሚገልጥ ነው፤ ምክንያቱም አንተ ይህን ሚስጥር መግለጥ ችለሃል።”+ 48  ከዚያም ንጉሡ ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ብዙ የከበሩ ስጦታዎችም ሰጠው፤ የመላው ባቢሎን አውራጃ ገዢና የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ዋና አስተዳዳሪ አደረገው።+ 49  ዳንኤልም ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን+ በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርጎ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን በንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያገለግል ነበር።

የግርጌ ማስታወሻዎች

በሟርትና በኮከብ ቆጠራ የተካኑ ሰዎችን ያቀፈ ቡድንን ያመለክታል።
ከዳን 2:4ለ እስከ 7:28 ድረስ በመጀመሪያ የተጻፈው በአረማይክ ነበር።
“ቆሻሻ መጣያ፤ የፋንድያ ክምር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ከሥጋ ጋር።”
ወይም “ሐውልት።”
ወይም “የተተኮሰ (ቅርጽ የወጣለት) ሸክላ።”
ወይም “ከሰው ዘር።” ተራውን ሕዝብ ያመለክታል።