የያዕቆብ ደብዳቤ 2:1-26

  • አድልዎ ማድረግ ኃጢአት ነው (1-13)

    • ፍቅር፣ ንጉሣዊ ሕግ (8)

  • ‘እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው’ (14-26)

    • አጋንንት ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ (19)

    • አብርሃም የይሖዋ ወዳጅ ተባለ (23)

2  ወንድሞቼ ሆይ፣ በአንድ በኩል ክብር በተጎናጸፈው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ ሆናችሁ በሌላ በኩል ደግሞ አድልዎ ታደርጋላችሁ?+  በጣቶቹ ላይ የወርቅ ቀለበቶች ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ስብሰባችሁ ቢመጣና ያደፈ ልብስ የለበሰ ድሃ ሰውም እንደዚሁ ወደ ስብሰባው ቢገባ  ያማረ ልብስ ለለበሰው ሰው አክብሮት በማሳየት “እዚህ የተሻለው ቦታ ላይ ተቀመጥ” ድሃውን ደግሞ “አንተ እዚያ ቁም” ወይም “እዚህ ከእግሬ ማሳረፊያ በታች ተቀመጥ” ትሉታላችሁ?+  እንዲህ የምትሉ ከሆነ በመካከላችሁ የመደብ ልዩነት እንዲኖር ማድረጋችሁ አይደለም?+ ደግሞስ ክፉ ፍርድ የምትፈርዱ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለም?+  የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ስሙ። አምላክ በእምነት ባለጸጋ እንዲሆኑና+ እሱን ለሚወዱ ቃል የገባውን መንግሥት እንዲወርሱ ከዓለም አመለካከት አንጻር ድሆች የሆኑትን አልመረጠም?+  እናንተ ግን ድሃውን ሰው አዋረዳችሁ። እናንተን የሚጨቁኗችሁና+ ጎትተው ፍርድ ቤት የሚያቀርቧችሁ ሀብታሞች አይደሉም?  እናንተ የተጠራችሁበትን መልካም ስም የሚሳደቡት እነሱ አይደሉም?  እንግዲያው በቅዱስ መጽሐፉ መሠረት “ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ”+ የሚለውን ንጉሣዊ ሕግ ተግባራዊ የምታደርጉ ከሆነ መልካም እያደረጋችሁ ነው።  ማዳላታችሁን የማትተዉ ከሆነ+ ግን ኃጢአት እየሠራችሁ ነው፤ ሕጉም ሕግ ተላላፊዎች ናችሁ ብሎ ይፈርድባችኋል።*+ 10  አንድ ሰው ሕጉን ሁሉ የሚጠብቅ ሆኖ ሳለ አንዱን ትእዛዝ ሳይጠብቅ ቢቀር ሁሉንም እንደጣሰ ይቆጠራል።+ 11  “አታመንዝር”+ ያለው እሱ “አትግደል”+ የሚል ትእዛዝም ሰጥቷልና። እንግዲህ ምንዝር ባትፈጽምም እንኳ ከገደልክ ሕግ ተላላፊ ሆነሃል። 12  ነፃ በሆኑ ግለሰቦች ሕግ* የሚዳኙ ሰዎች በሚናገሩበት መንገድ መናገራችሁንና እነሱ እንደሚያደርጉት ማድረጋችሁን ቀጥሉ።+ 13  ምሕረት የማያደርግ ሰው ያለምሕረት ይፈረድበታልና።+ ምሕረት በፍርድ ላይ ድል ይቀዳጃል። 14  ወንድሞቼ ሆይ፣ አንድ ሰው እምነት አለኝ ቢል ነገር ግን እምነቱ በሥራ የተደገፈ ባይሆን ምን ጥቅም ይኖረዋል?+ እምነቱ ሊያድነው ይችላል?+ 15  አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የሚለብሱት ቢያጡና* ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን በቂ ምግብ ባያገኙ 16  ሆኖም ከመካከላችሁ አንዱ “በሰላም ሂዱ፤ ይሙቃችሁ፤ ጥገቡም” ቢላቸው ለሰውነታቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ግን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል?+ 17  ስለዚህ በሥራ ያልተደገፈ እምነትም በራሱ የሞተ ነው።+ 18  ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ ይላል፦ “አንተ እምነት አለህ፤ እኔ ደግሞ ሥራ አለኝ። እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔ ደግሞ እምነቴን በሥራ አሳይሃለሁ።” 19  አንድ አምላክ እንዳለ ታምናለህ አይደል? ማመንህ መልካም ነው። ይሁንና አጋንንትም ያምናሉ፤ በፍርሃትም ይንቀጠቀጣሉ።+ 20  አንተ ከንቱ ሰው፣ እምነት ያለሥራ እንደማይጠቅም ማረጋገጥ ትፈልጋለህ? 21  አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ ካቀረበ በኋላ የጸደቀው በሥራ አይደለም?+ 22  እምነቱ ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበረና ሥራው እምነቱን ፍጹም እንዳደረገው ትገነዘባለህ፤+ 23  ደግሞም “አብርሃም በይሖዋ* አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት”+ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ተፈጸመ፤ እሱም የይሖዋ* ወዳጅ ለመባል በቃ።+ 24  እንግዲህ ሰው የሚጸድቀው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራም ጭምር እንደሆነ ትገነዘባላችሁ። 25  ዝሙት አዳሪዋ ረዓብም መልእክተኞቹን በጥሩ ሁኔታ ተቀብላ ካስተናገደቻቸውና በሌላ መንገድ ከላከቻቸው በኋላ በሥራ አልጸደቀችም?+ 26  በእርግጥም አካል ያለመንፈስ* የሞተ እንደሆነ ሁሉ+ እምነትም ያለሥራ የሞተ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ወይም “ይወቅሳችኋል።”
ቃል በቃል “በነፃነት ሕግ።”
ቃል በቃል “ቢራቆቱና።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “እስትንፋስ።”