ኢሳይያስ 35:1-10

  • ምድር ገነት ትሆናለች (1-7)

    • ዓይነ ስውራን ያያሉ፤ መስማት የተሳናቸውም ይሰማሉ (5)

  • የተዋጁት የሚጓዙበት “የቅድስና ጎዳና” (8-10)

35  ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ሐሴት ያደርጋል፤+በረሃማው ቦታም ደስ ይለዋል፤ እንደ ሳሮን አበባም * ያብባል።+   በእርግጥ ያብባል፤+ሐሴት ያደርጋል፤ በደስታም እልል ይላል። የሊባኖስ ክብር ይሰጠዋል፤+የቀርሜሎስንና+ የሳሮንን+ ግርማ ይለብሳል። የይሖዋን ክብር፣ የአምላካችንንም ግርማ ያያሉ።   የደከሙትን እጆች አበርቱ፤የሚብረከረኩትንም ጉልበቶች አጽኑ።+   በጭንቀት የተዋጠ ልብ ላላቸው እንዲህ በሏቸው፦ “በርቱ፤ አትፍሩ። እነሆ፣ አምላካችሁ ሊበቀል ይመጣል፤አምላክ ብድራት ሊከፍል ይመጣል።+ እሱ መጥቶ ያድናችኋል።”+   በዚያን ጊዜ የዓይነ ስውራን ዓይን ይገለጣል፤+መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጆሮም ይከፈታል።+   በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤+የዱዳም ምላስ በደስታ እልል ይላል።+ በምድረ በዳ ውኃ ይፈልቃልና፤በበረሃማ ሜዳም ጅረት ይፈስሳል።   በሐሩር የተቃጠለው ምድር ቄጠማ የሞላበት ኩሬ፣የተጠማውም ምድር የውኃ ምንጭ ይሆናል።+ ቀበሮዎች ይኖሩበት የነበረው ጎሬ+ለምለም ሣር፣ ሸምበቆና ደንገል ይበቅልበታል።   በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፤+ደግሞም “የቅድስና ጎዳና” ተብሎ ይጠራል። ንጹሕ ያልሆነ ሰው አይጓዝበትም።+ ጎዳናው፣ በመንገዱ ላይ ለሚሄዱት ብቻ ይሆናል፤ሞኞችም አይሄዱበትም።   በዚያ አንበሳ አይኖርም፤አዳኝ አራዊትም ወደዚያ አይወጡም። አንዳቸውም በዚያ አይገኙም፤+የተቤዡት ብቻ በዚያ ይሄዳሉ።+ 10  ይሖዋ የዋጃቸው ይመለሳሉ፤+ ወደ ጽዮንም በእልልታ ይመጣሉ።+ ፍጻሜ የሌለው ደስታን እንደ አክሊል ይጎናጸፋሉ።+ ደስታንና ሐሴትን ያገኛሉ፤ሐዘንና ሲቃም ከዚያ ይርቃሉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ሳፍሮንም።”