ኢሳይያስ 33:1-24

  • ጻድቃን የሚያገኙት ፍትሕና የሚጠብቃቸው ተስፋ (1-24)

    • ይሖዋ ዳኛ፣ ሕግ ሰጪና ንጉሥ ነው (22)

    • “ታምሜአለሁ” የሚል አይኖርም (24)

33  አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፣+ክህደት ሳይፈጸምብህ ክህደት የምትፈጽም ወዮልህ! ማጥፋትህን እንዳጠናቀክ አንተም ትጠፋለህ።+ ክህደት መፈጸምህን እንዳበቃህ ትካዳለህ።   ይሖዋ ሆይ፣ ሞገስ አሳየን።+ በአንተ ተስፋ አድርገናል። በየማለዳው በክንድህ ደግፈን፤*+አዎ፣ በጭንቅ ጊዜ አዳኛችን ሁን።+   የድምፅህን ነጎድጓድ ሲሰሙ ሕዝቦች ይሸሻሉ። በምትነሳበት ጊዜ ብሔራት ይበታተናሉ።+   የማይጠግቡ አንበጦች በሚሰበሰቡበት ጊዜ እንደሚሆነው ከእናንተም የሚወሰደው ምርኮ እንዲሁ ይሰበሰባል፤ሰዎች እንደ አንበጣ መንጋ ምርኮውን ይቀራመቱታል።   ይሖዋ ከፍ ከፍ ይላል፤በከፍታ ቦታ ይኖራልና። ጽዮንን በፍትሕና በጽድቅ ይሞላል።   እሱ የዘመንህ መተማመኛ ነው፤የመዳን፣+ የጥበብና የእውቀት ብዛት እንዲሁም ይሖዋን መፍራት፣+ይህ የእሱ ውድ ሀብት ነው።   እነሆ፣ ጀግኖቻቸው በጎዳና ላይ ይጮኻሉ፤የሰላም መልእክተኞቹም አምርረው ያለቅሳሉ።   አውራ ጎዳናዎቹ ጭር ብለዋል፤በመንገድ ላይ የሚጓዝ ሰው የለም። እሱ* ቃል ኪዳኑን አፍርሷል፤ከተሞቹን ንቋል፤ሟች ለሆነው ሰው ደንታ የለውም።+   ምድሪቱ አዘነች፤* ጠወለገችም። ሊባኖስ ተዋረደ፤+ እንዲሁም በሰበሰ። ሳሮን እንደ በረሃ ሆነች፤ባሳንና ቀርሜሎስም ቅጠላቸውን አረገፉ።+ 10  “አሁን እነሳለሁ” ይላል ይሖዋ፤“አሁን ራሴን ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤+አሁን ራሴን አከብራለሁ። 11  ደረቅ ሣር ትፀንሳላችሁ፤ ገለባንም ትወልዳላችሁ። የገዛ መንፈሳችሁም እንደ እሳት ይበላችኋል።+ 12  ሕዝቦችም እንደተቃጠለ ኖራ ይሆናሉ። እንደተቆረጠ እሾህ በእሳት ይጋያሉ።+ 13  እናንተ በሩቅ ያላችሁ፣ የማደርገውን ስሙ! እናንተም በቅርብ ያላችሁ፣ ለኃይሌ እውቅና ስጡ! 14  በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች እጅግ ፈሩ፤+ከሃዲዎቹም ብርክ ያዛቸው፦ ‘ከእኛ መካከል የሚባላ እሳት ባለበት ቦታ መኖር የሚችል ማን ነው?+ ከእኛስ መካከል ከማይጠፋ የእሳት ነበልባል ጋር መኖር የሚችል ማን ነው?’ 15  ዘወትር በጽድቅ የሚመላለስ፣+ቅን+ የሆነውን ነገር የሚናገር፣በማታለልና በማጭበርበር የሚገኝን ጥቅም የሚጠላ፣ጉቦ ከመቀበል እጁን የሚሰበስብ፣+ደም ለማፍሰስ የሚጠነሰስን ሴራ ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍንእንዲሁም ክፉ የሆነውን ላለማየት ዓይኑን የሚጨፍን ሰው፣ 16  በከፍታ ቦታዎች ይኖራል፤ዓለታማ ምሽጎች አስተማማኝ መጠጊያው ይሆናሉ፤ምግቡም ይቀርብለታል፤የውኃ አቅርቦትም ፈጽሞ አይቋረጥበትም።”+ 17  ዓይኖችህ ንጉሡን ግርማ ተላብሶ ያዩታል፤በሩቅ ያለችውን ምድር ያያሉ። 18  ሽብር የነበረበትን ወቅት በልብህ ታስታውሳለህ፦* “ጸሐፊው የት አለ? ግብር የመዘነው የት አለ?+ ማማዎቹንስ የቆጠረው የት አለ?” 19  የማይገባ ቋንቋ የሚናገረውንና*ለመረዳት የሚያስቸግር ተብታባ አንደበት ያለውን+ጋጠወጥ ሕዝብ ከእንግዲህ አታይም። 20  በዓሎቻችንን+ የምናከብርባትን ከተማ ጽዮንን ተመልከት! ጸጥታ የሰፈነባት መኖሪያ፣የማትነቃነቅ ድንኳን+ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን ዓይኖችህ ያያሉ። የድንኳን ካስማዎቿ ፈጽሞ አይነቀሉም፤ከገመዶቿም አንዱ እንኳ አይበጠስም። 21  ይልቁንም ግርማ ሞገስ የተላበሰው ይሖዋበዚያ ስፍራ እንደ ወንዞችና እንደ ሰፋፊ ቦዮች ሆኖ ይጠብቀናል፤በእነሱም ላይ ጠላት የሚያሰልፋቸው ባለ መቅዘፊያ ጀልባዎችም ሆኑትላልቅ መርከቦች አያልፉም። 22  ይሖዋ ዳኛችን ነው፤+ይሖዋ ሕግ ሰጪያችን ነው፤+ይሖዋ ንጉሣችን ነው፤+የሚያድነን እሱ ነው።+ 23  ገመዶችህ ይላላሉ፤የመርከቡን ምሰሶ አጽንተው ማቆምም ሆነ ሸራውን ወጥረው መያዝ አይችሉም። በዚያን ጊዜ ብዛት ያለው ምርኮ ይከፋፈላል፤አንካሶችም እንኳ ብዙ የሚበዘበዝ ነገር ያገኛሉ።+ 24  በዚያም የሚቀመጥ* ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” አይልም።+ በምድሪቱ ላይ የሚቀመጡ በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ብርታት ሁነን።”
ጠላትን ያመለክታል።
“ደረቀች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ታሰላስላለህ።”
ቃል በቃል “ቋንቋው ጥልቅ የሆነውንና።”
ወይም “የሚኖር።”